Get Mystery Box with random crypto!

የሚጠይቅ ሰው አለ?!፣ የሚለምን ሰው አለ?!፣ ወደ ጌታው የሚመለስ (ተውበት) የሚያደርግ ሰው አለ | 🎤 ሸምሱ ጉልታ (አቡ ሀመዊየህ) ✍

የሚጠይቅ ሰው አለ?!፣ የሚለምን ሰው አለ?!፣ ወደ ጌታው የሚመለስ (ተውበት) የሚያደርግ ሰው አለን?!።
—————
እያለ ይጠይቃል የዓለማቱ ጌታ ብቸኛው አዛኙ! አምላካችን አላህ።

አቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) የአላህ መልእክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል አለ:- «ጌታችን አላህ (ልቅና ይገባውና) ከለሊቱ መጨረሻ አንድ ሶስተኛው ሲቀረው በሁሉም ሌሊት ወደ ዱኒያዋ ሰማይ ይወርዳል፣ እንዲህም ይላል:- ማን ነው የሚለምነኝ እሺ እንድለው?!፣ ማነው ሚጠይቀኝ የጠየቀውን መልካም ነገር እንድሰጠው?፣ ማንነው ምህረትን የሚለምነኝ እንድምረው?!።» [ሙስሊም 758 ላይ ዘግበውታል።]

ከጃቢር (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ የአላህ መልእክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ አለ:- «በሌሊቱ ክፍል ጊዜ አንዲት ሰኣት አለች፣ (በዚያች ሰኣትም) ሙስሊም የሆነ ሰው ከዱኒያና ከአኼራ በላጭ (መልካም) የሆነን ነገር አላህን አይጠይቅም የጠየቀውን ነገር ቢሰጠው እንጂ፣ ያቺ ሰኣትም በሁሉም ሌሊት አለች።» [ሙስሊም 757 ላይ ዘግበውታል።]

ከዐምር ኢብኑ ዐበሳ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ አለ:- «ጌታ (አላህ) ከባሪያዎቹ ቅርብ የሚሆንበት ወቅት ከሌሊቱ አንድ ሶስተኛ መጨረሻ ነው። በዚያች ሰዓት አላህን ከሚያወሱ ሰዎች ውስጥ መሆን ከቻልክ ሁን!።» [ሸይኽ አልባኒ በሚሽካት 1229 ላይ ሶሂህ ያሉት ሲሆን ሸይኽ ሙቅቢልም በሶሂህ ሙስነዳቸው 2/91 ላይ ሶሂህ ነው ብለውታል።]

ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ (ረሂመሁላህ) እንዲህ አሉ:- ሰዎች በሌሊቱ የመጨረሻው አንድ ሶስተኛ ጊዜ በሌሎች ጊዜያት ሊገኝ በማይችል መልኩ ልባቸው ይለሰልሳል፣ ወደ አላህ ይቃረባል፣ ይህ ወደ ዱኒያዋ ሰማይ ለመውረዱ የገጠመ ነው። የሚጠይቅ ሰው አለ?!፣ የሚለምን ሰው አለ?!፣ ወደ ጌታው የሚመለስ (ተውበት) የሚያደርግ ሰው አለን?!፣ የሚለውም ለዚሁ ነው።” [መጅሙዕ አል-ፈታዋ 5/130 - 131]

ማንቂያ!:-
እነዚህ እና መሰል በሌሊቱ መጨረሻ አካባቢ የአላህን ወደ ቅርቢቷ ሰማይ መውረዱን የሚጠቁሙ ሀዲሶች የአላህን ከፍጥረቱ ሁሉ በላይ ከዐርሹ ከፍ ማለቱን ከሚገልፁ የማስረጃ አይነቶች አንዱ ናቸው!።

እንዲያው አሕባሾችና አሻዒራዎች የተለያዩ ማስረጃዎችን ከትክክለኛው ትርጓሜያቸው ለመጠምዘዝ ቢሞክሩ ይህን (የአላህን ለዱኒያ ቅርብ ወደሆነችዋ ሰማይ መውረዱን) እንዴት አድርገው አጣመው ይተረጉሙት ይሆን?!

አያፍሩም እኮ፣ ከሰማይ የሚወርደው መላኢካ ነው ይሉን ይሆናል፣ እኛም ጥያቄ አለን:- ማን ነው የሚለምነኝ እሺ እንድለው?!፣ ማነው ሚጠይቀኝ የጠየቀውን መልካም ነገር እንድሰጠው?፣ ማንነው ምህረትን የሚለምነኝ እንድምረው?! እያለ የሚጠይቀው መላኢካ ነውን?! እንላቸዋለን። አዎን ካሉን፣ ከአንድ አላህ በስተቀር የሚለመንና ምህረት የሚጠየቅ አለን?! እንላቸዋለን።

ይህ ደግሞ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው!! ከአንድ አላህ በስተቀር ምህረት የሚጠየቅና ጭንቅ ውስጥ ሲኮን ፈጥኖ ደራሽ ከቶ ከየት ተገኝቶ?!

የሰው ልጅ እንደመሆኑ ሁሉም ደረጃው ይለያይ እንጂ በተያየ ጉዳይ ይጨነቃል፣ ተሳስቶ ጌታውንም ያምፃል። በመሆኑም በተለያየ ጉዳይ የተጨነቀና ተሳስቶ ጌታውን አላህን ያመፀ ሁሉ በሌሊት ተነስቶ አዛኙንና ሩህሩህ የሆነውን ፈጥኖ ደራሹን አላህን "አቤት እኔ አለሁ፣ ማረኝ! ጉዳዬን ሁሉ አስተካክልልኝ" ይበል!!
ኢብን ሽፋ (t.me/IbnShifa)

የተለያዩ ት/ቶችን ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችን #join በማድርግ ይቀላቀሉ
https://telegram.me/IbnShifa
https://telegram.me/IbnShifa