Get Mystery Box with random crypto!

በትናትናው የአብን መግለጫ ዙሪያ የኔ የተለየ አስተያየት...! ትናንት አብን ያወጣውን መግለጫ ተ | ዘሪሁን ገሠሠ

በትናትናው የአብን መግለጫ ዙሪያ የኔ የተለየ አስተያየት...!

ትናንት አብን ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ እጅግ የተጋነኑ ተቃውሞዎችን አስተውያለሁ፡፡ ሁሉም ትችትና ተቃውሞዎች " ከዚያስ …?" ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ሆነው አላገኘኃቸውም፡፡ በመሆኑም እኔ እንደግለሰብ ከተንሸራሸሩት ተቃውሞዎች የተለየ ሀሳብ ስላለኝ ፥ በአመክንዮ ልምግታችሁ ወድጃለሁ፡፡ ከተሳሳትኩ በጨዋ ደንብ በምክንያትና በውጤት የተደገፈ ሀሳብ በመሰንዘር ለምታርሙኝ በሩ ክፍት ነው፡፡

የአብንን መግለጫ አንድ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ ማለት ካለበትና ከሚጠበቅበት የሀሳብ አበርክቶት ብሎም ከፖለቲካዊ ተግባቦት አኳያ በጥቅሉ ከገመገምነው ፥ የመግለጫው ሀሳብ ፈፅሞ ስህተት ነው ብዬ አላምንም፡፡

ነገርግን በግሌ ፥ " አብን ህዝቡን ሊያታግልም ሆነ ትግሉን ሊመራ የሚችለው በቅድሚያ ያሉበትን ድርጅታዊ ተግዳሮቶች ፈትቶ ፥ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ በሁለት እግሩ መቆም ሲችል በመሆኑ ፥ ትኩረትና ርብርቡ ግንቦት 6 ለማድረግ በወሰነው ጉባኤ ላይ መሆን ነበረበት" ብዬ ስለማምን ብሎም " የፖለቲካ ብልሽቱ የፈጠራቸው ተቋማት ላይ ያሉት የገነገኑ ችግሮች ፥ በተቋማቱ ላይ አስተማማኝ እምነት ለማሳደር የሚያስችሉ ባለመሆናቸው" ፤ ተቀዳሚ አስተያየቴ "አብን በዚህ ጉዳይ አስተያየት ሳይሰጥ ዝም ብሎ ቢያልፈው የተሻለ ነው!" የሚል ነው፡፡

ከዚያ ውጭ ሁሉም ክልሎች በተለይ ኦሮሚያ ፥ ከፍተኛ ርብርብ አድርገው አብዛኛዎቹ ልዩ ሀይሎች ፎርም ሞልተው ፥ ወደመከላከያ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ኦነግ ሸኔም ከድርድሩ በኃላ ወደመከላከያ ይግባ ይባላል፡፡ የአማራ ክልል ደግሞ ሰላሳ ፐርሰንቱን እንኳ በቅጡ አልተቆጣጠረውም፡፡

አብን እንደአንድ ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅት ፥ አስቀድሞ በምክንያት " ልዩ ሀይሉ መፍረስ የለበትም!" ብሎ ተከራከረ ፥ ታገለ ፤ አስጠነቀቀ፡፡ ነገርግን መንግሥት "አይቻልም!" ብሎ በውሳኔው ገፋበት፡፡ ህዝባችንም የህይወት መስዋዕትነት እስከመክፈል የደረሰ ትግል አድርጓል ፤ ነገርግን ልዩ ሀይሉ ከመበተን ውጪ ተቋማዊ ሆኖ እንደቀደመው የሚቀጥልበትን እድል መፍጠር ወይም መቀየር አልተቻለውም፡፡

በመሆኑም " ይህ ትጥቅ ይዞ የተበተነ ሀይል የት ይግባ ?" የሚለው መመለስ ያለበት ተቀዳሚ ጥያቄ ሆኖ አፍጥጦ መጣ፡፡ እኔ ከዚህ በፊት እንደግለሰብ "ልዩ ሀይሉ ግንባር ይዞና ተደራጅቶ ይታገል ፥ አለበለዚያ ('መንግሥት ትጥቅ ይዞ እንዲቀመጥ ይፈቅዳል አይፈቅድም) የሚለው ሌላ ጥያቄ ሆኖ ፤ በየቤቱ ገብቶ ይቀመጥና ከህዝብ ጋር ይታገል " ብያለሁ፡፡ አሁንም በግሌ ብጠይቁኝ ያንኑ ልደግም እችል ይሆናል፡፡

አብን እንደድርጅት ግን " ሌሎቹ እያደረጉ እንዳሉት የፌደራል ተቋማቱን ይቀላቀል!" ማለት እንጂ "አማፂ ቡድን ይሁን!" ብሎ ምክረ ሀሳብ እንዲይዝ መጠበቅ ምናልባትም የዋህነት ካልሆነ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ የመወሰንና የማስገደድ አቅምም የለውም፡፡

ቆይ እሺ ከመቶ ሺህ በላይ ልዩ ሀይል ውስጥ ሰላሳ ሺው እንኳ በክልሉ ሀንድል ካልተደረገ ፤ ወይ ገዢ ምድር ይዞ በሌላ እዝና ስያሜ የሚታገል ህዝባዊ ፎርስ ካልሆነ ፤ በየከተማው ትጥቅ ይዞ ተበትኖ በምን አግባብ ይኑር ? አይደለም ለአስር ሺዎች ለአስር ልዩ ሀይል ደመወዝ መክፈል የሚችል አደረጃጀትና ቁርጠኝነቱስ አለንን ? ሌላው ቀርቶ ይህ ሀይል ሲራብስ ....?

"መንግስት ነኝ" የሚለው አካልስ ፥ ይህን ተበትኖ ያለን የታጠቀ ሀይል በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ይፈቅድለታልን ? ይህ ሀይል አሁን ባለበት ሁኔታ ለህዝባችን ሰላምና ደህንነት አስተዋፅኦ ማበርከት ይችላልስ ወይ ? ይህ ትጥቅ ይዞ የተበተነ ሀይል በዚህ መልኩ መጓዙ ለራሱ ደህንነትና ህልውና አያሰጋውም ወይ ?

በየአካባቢው ትናንትን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተበታተኑት ልዩ ሀይል ወንድሞቻችን የጥቃት ተጋላጭ ሆነው በተናጠል እየሞቱ ነው፡፡ ይህ ለህዝቡም ሆነ ለእነሱ ይጠቅማቸዋልን ? ህዝባዊ መስዋትነትስ ነውን ?

እኚህን ጥያቄዎች ለራሳችን ከመለስን ፥ "የመከላከያ ሰራዊቱም ሆነ የፌዴራል ፖሊስ ተቋማት" የምናነሳባቸው ግድፈቶችን ባልቀረፉበትም ሁኔታ ቢሆን ፥ የሰው ሀይላቸውን እያጠናከሩ ወደፊት መቀጠላቸው እስካልቀረ ድረስ ፥ ይህ ተበትኖ የሚገኝ ሀይል ወደእነዚህ ተቋማት ቢገባ የተሻለ ህዝባዊና ሀገራዊ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል ሳናመነታ እንረዳለን!

ተቋማዊ የሆነ አቋምም ፥ ሊሆን የሚችለው ይህኑ ነው፡፡ እንደግለሰብ ግን ሌላ አማራጭ ልናቀርብ እንችል ይሆናል! ተፈፃሚና የሚቻል ከሆነ...!

ያሰብነውና ያቀድነው ካልሆነ ግን ህዝባችን በየተቋማቱ ምንም ድርሽ እንዳይል አድርገን ከሁለት አንድ ያጣ ሆኖ ፥ በቀጣይ ምን እንደሚሆን አስባችሁታልን ?

ትችትና አስተያየታችን ሚዛን ይኑረው! ነባራዊ እውነታውን የተረዳ ይሁን! ሌላው ሆይ ሆይ ለህዝቡ ፈፅሞ አይጠቅመውም! ራሳሳችን ባቀበልነው አለንጋም እየተገረፍን መሆናችንን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

የምንታገለው ለህዝባችን ጥቅምና ፍላጎት ከሆነ " ከዚያስ…?" ብለን ራሳችንን በመጠየቅ ፥ አማራጭ መፍትሔ ማቅረብ በማንችልበት ጉዳይ ላይ በጭፍን ከመቃወም መቆጠብ ብሎም ከተለዋዋጩ የፖለቲካ ኡደት ጋር አብሮ የሚሄድ ፣ አቅምን ያገናዘበና የተተነተነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ማራመድ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ መልኩ የማይነገረውን ሁሉ ለማንሳት የወደድኩት ፥ የኛ የሳይበር ሰራዊት ሁሉ ነገር በአደባባይ ተሰጥቶ ቢነገርም ለመቀበል ስለማይፈቅድ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ትምምን ቢኖርና ብንታደልኮ ፥ ትክክለኛ የተደራጀና በጋራ ኮዙ ላይ የተግባባ የፖለቲካ ማህበረሰብ ፥ የራሱ ፖለቲከኛ በአደባባይ ለፖለቲካል ኮሚዩኒኬሽን በተቃራኒ እንኳ ቢሆን በሚይዘው አቋምና ንግግር በጥቅሻ ተግባብቶ ፥ በውስጥ ግን የሚፈለገው ነገር በጋራ የሚፈፀምበትን አውድ መፍጠር የሚችል ነበር፡፡

በጥቅሉ የአማራ ህዝብ አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ ፥ አይደለም ለሰው ለአምላክ እንኳ አሰልቺና አድካሚ ሆኗል ! ሁሉም የሚናገርበትና የሚፈርድበት ፥ በተናጠል የሚጮህበት ፥ ሁሉም በየእጁ አቅጣጫና መስመር የሚያመላክትበት ፥ መደማመጥ ፣ መተማመን ፣ መከባበርና መተባበር የራቀው የትርምስ ማዕከል ሆኗል ! ከዚህ መውጣት የምንችለው በቅድሚያ እያንዳንዳችን ራሳችንን መመልከትና ማረም ስንችል ነው ! መደማመጥ ፣ መከባበርና መተባበር መገለጫ ምግባራችን ሲሆን ብቻ ነው!

በግሌ ምናልባት ከእንግዲህ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ፤ በአማራም ሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምንም የምልበት አቅም እየተሟጠጠ በመምጣቱ ፥ ይህን ህዝብ " እሱ ይሁንህ !" ከማለት ባሻገር ብዙ ላልል እችላለሁ !

በሀሳብ ሊያርሙኝ ፥ ሊሞግቱኝ ለሚችሉ ወንድም እህቶች በሩ ክፍት ነው!

ትችትና አስተያየታችን ሚዛን ይኑረው!

ይኸው ነው!