Get Mystery Box with random crypto!

ከዚህ ባለፈ ግን የሀይማኖት ከፖለቲካ ተለይቶ መታየት አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራሉ። ‹‹ያ መሆኑም | ዘሪሁን ገሠሠ

ከዚህ ባለፈ ግን የሀይማኖት ከፖለቲካ ተለይቶ መታየት አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራሉ። ‹‹ያ መሆኑም ሀይማኖትን ተጋላጭና ደካማ አያደርገውም።›› የሚሉት ደግሞ ፕሮፌሰር ሙባረክ ናቸው። " እንደውም ከታሪክ መረዳት የሚቻለው ሀይማኖት በማንኛውም ጊዜ የፖለቲካን እርዳታ መጠየቅ ራሱ የለበትም!" ሲሉ በጥናታቸው ጠቅሰዋል። ምክንያቱን ሲያስረዱ ደግሞ " ኃይማኖት የፖለቲካን እርዳታ ከጠየቀ፣ ፖለቲካ ሀይማኖትን ሊጠቀምበትና ያለምንም ማንገራገር እጁን እንዲከትበት መፍቀድ ነው!" ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ሰሎሞን ጌጡ የተባሉ ፀሐፊ ‹ሀይማኖት እና ፖለቲካ› በሚል ርዕስ ባስነበቡት አንድ ጽሑፍ ደግሞ ፥ የታሪክ ተመራማሪውን ሐሳብ የሚደግፉ ነጥቦችን አንስተዋል። ሁለቱ አካላት እንደ ተቋም ስላላቸው ግንኙነት በሚያስረዱበት በዚህ ጽሑፍ፣ ‹‹መቼም ቢሆን በየትኛውም አገርና ሕዝብ ውስጥ ሀይማኖትና ፖለቲካ ሳይገናኙ ለየቅል ተጉዘው አያውቁም፡፡›› በማለት ፥ የግንኙነቱ ዓይነትና ደረጃ ግን ሊለያይ እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

‹‹ሀይማኖትና ፖለቲካ ተጓዳኝ የሆነ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው። የመንግሥትና ሀይማኖት መለያየት የሚለው የዴሞክራሲ ስርአት መርሆ የሚገልጽልን በዴሞክራሲ ስርአት ውስጥ መንግሥታዊ ሀይማኖት እንደሌለና ግለሰቦች የፈለጉትን እምነት የመከተል መብት እንዳላቸው ነው። እንጂ ፖለቲካና ሀይማኖት የተለያዩ እንደሆኑ ማሳያ አይደለም።›› ሲሉ ይሞግታሉ።

የኢትዮጵያስ የቀደመ ታሪክ ምን ይመስል ነበር ?

ኢትዮጵያ ውስጥም ‹ስዩመ እግዚአብሔር› ተብለው የሚመሩ እንደነበሩ፣ ከላይ ከፈጣሪ ተመርጠው፣ እርሱ የቀባቸው ቅቡዓን ብቻ ናቸው መምራት ያለባቸው የሚል እሳቤ እንዳለ ውሂበእግዜር ያነሳሉ። በሌላ በኩል ‹የለም! ይህ ምድራዊ ነው፣ የምድሩን ዴሞክራሲ በሚባል ስርዓት ነው መመራት ያለበት እንጂ ሰማያዊው ለምድሩ አስፈላጊ አይደለም› የሚል ክርክርም አለ ብለዋል።

ሰሎሞን በበኩላቸው በጽሑፋቸው እንዳካተቱት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም በፊውዳሉ ስርአት ሀይማኖትና ፖለቲካ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ነበሩ ማለት ይቻላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እርሳቸውም ይህን ጽሑፍ ባስነበቡበት ዓመት (2012) የነበረውና ያለውን የሀይማኖትና ፖለቲካ ግንኙነት ታድያ፣ ‹‹እንዳለመታደል ሆኖ ተመጋጋቢ የሆነ ለሁለንተናዊ ሰላም የሚረዳ የተአቅቦ የሁለትዮሽ ግንኙነት ሳይሆን፤ የፖለቲካው ፍፁም የበላይነት ያለበትና የሀይማኖት ተቋማትን የሚደፈጥጥ ብሎም የሚበዘብዝ በመሆኑ እጅግ አደገኛና ማኅበረሰቡን እና አገሪቷን ውስብስብ ወደሆነ ማጥ ውስጥ ሊከት የሚችል ነው።›› ሲሉ ገልጸዉታል።

ይህ እየሆነ የነበረበትን/ያለበትን መንገድ ሲያስረዱ ፤ አንደኛው ምክንያት የፖለቲካ ዓላማ ነው ይላሉ። ይህም የሀይማኖት ተቋማትና የሀይማኖት አባቶች ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም የመንግሥትን ፕሮፓጋንዳና እሳቤ በቀላሉ በሕዝብ ላይ ለመጫን እና ለማስረጽ ነው። ይህም ሁለት መንገድ አለው ሲሉ የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሰው ተከታዩን ሀሳብ ያነሳሉ፡፡

‹‹የመጀመሪያው ብራያን ተርነር ነው፤ በ2013 ባቀረበው ጥናት እንደጠቀሰው ከፊል ሴኩላራይዜሽን (Partial Secularization) የሚባል ያለ ሲሆን፤ ይህ ማለት መንግሥት በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት እንቅፋት ይሆኑኛል የሚላቸውን አስተሳሰቦችን/አስተምህሮዎችን የሚያጠፋበትና በአዲስ የሚያዘምንበት መንገድ ነው። ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በሰራዊት በቀለ ጥናት ላይ እንደሰፈረው (2018) መንግሥት በእጅ አዙር የሀይማኖት ተቋሙን የሚቆጣጠርበት እና የኔ የሚላቸውን ግለሰቦች/ የሀይማኖት አባቶች በመሾም የፈለገውን የሚፈጽምበት እና ጣልቃ የሚገባበት መንገድ ነው።›› በማለት ያስቀምጣሉ፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ምን እየሆነ ነው?

ካለሳለፍናቸው ወደ5 የሚሆኑ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ አጀንዳ ሆነው ግጭት ከሚነሳባቸው ጉዳዮች መካከል፣ ለሰዎች ስሜት ቅርብ የሆኑ የሀይማኖት እና የብሔር ጉዳይ ተጠቃሽ ናቸው። በቅርቡም በሀገራችን በሀይማኖትና በብሔር ተኮር ግጭቶች የደረሱ እልቂቶችንና ጉዳቶችን ብሎም ከሰሞኑ እንኳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዙሪያ የተፈጠረውን ጣልቃገብነትና ተያይዞ የመጣውን ሀገራዊ ውጥረት በአስረጂነት ማንሳት ይቻላል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ውሂበእግዜር " እነዚህ ሁሉ ጥፋቶች የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ውጤት ናቸው!" በሚለው ሀሳብ ይስማማሉ። ‹‹[ክስተቱ] የሀይማኖት ግጭት አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሀይማኖት ግጭት ሳይሆን ሀይማኖትን እንደ መሣሪያ የሚጠቀም የፖለቲካ ዓላማ ያለው ግጭት ነው።›› ሲሉም ይገልፁታል፡፡

" እንደውም ኢትዮጵያ የሀይማኖት መቻቻል ያለባት ብቸኛ አገር ናት" የሚሉት ምሁሩ ፤ << የአብርሀም ነን የሚሉትን ኹለቱን ትልልቅ ሀይማኖቶች ማለትም ክርስትና እና እስልምና የያዘች ፥ የእነዚህ ተቋማት ግንኙነትም የተገነባባት፣ የመጀመሪያው ሂጅራ የተካሄደባት፣ ክርስትናም ቀድሞ የመጣባት አገር ናት፡፡፡፡>> ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ቀጠል አድርገውም ‹‹ቀደምት የሚባሉት የሀይማኖት ተቋማት ለዘመናት የቆዩባት አገር ላይ ሀይማኖታዊ ግጭት አለ ብዬ ለመናገር ይከብደኛል። ሀይማኖቶቹን የሚጠቀሙ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው ያስቸገሩት።›› በማለት ዕይታቸውን ገልፀዋል ፡፡

ነባራዊውን የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተም << ከዚህ ጋር በተያያዘ በብዙ መልኩ የመንግሥት የማስፈጸም አቅም አለ እየተባለ የሚወራው ከወሬ የዘለለ አይደለም! >>ይላሉ፡፡ ይልቁንም ማንኛውም ሰው በኢትዮጵያ ባመነበት የማምለክ መብቱ ግን የተከበረ ሲሆን ፥ አንዱ በሌላው መብት ጣልቃ ሳይገባ ፥ የየእምነቱን ስርአት ሲፈጽም ሌላውን በማይነካ መንገድ መሆን አለበት! >> ሲሉ የሀይማኖት ብዘሀነታችንን ውበታችን እንደሆነ ለማስቀጠል የሚያስችለውን የመፍትሔ መንገድ ይጠቁማሉ፡፡

በእሳቸው መረዳት ልክ በአሁኑ ሰዓት ያለውንም ችግር ሲገልፁት ‹‹አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር እየፈጠረ ያለው ከዚህ በፊት ተጨቁኛለሁ፣ ከባድ ችግር ነበረብኝ፣ ሀይማኖታዊ ቦታ አልነበረኝም የሚል የፕሮቴስታንት ትርክት አለ። ያም በአገሪቱ እንቅስቃሴ ውሰጥ ገናና ሆኜ መታየት አለብኝ የሚል እንቅስቃሴ በጣም አደገኛ ነው፣ ትክክልም አይደለም። መታረም አለበት። ሁሉም የራሱ ቦታ አለው፤ በራሱ የአምልኮ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡ ይህን ወደ መንግሥታዊ ስርዓት ለመቀየር የሚደረግ እንቅስቃሴ አገሪቱን አደጋ ላይ ይጥላል። >> ብለዋል፡፡

በተጨማሪም << በሌላ በኩል ከሱዳን የሚነሳው ‹የኢስላሚክ ወንድማማችነት› አራምጅ አለ። ‘በሀይማኖታዊ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ሥልጣን እቆናጠጣለሁ’ የሚል አስተሳሰብ ያለው ይህ አክራሪ ኢስላማዊ እንቅስቃሴም ለአገሪቱ አደጋ ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ አገሪቱ ውስጥ ‘ነባርና ብቸኛ እኔ ነኝ ፤ ከእኔ ውጪ ሌላ መደረግ የለበትም!’ የሚል የኦርቶዶክስ አክራሪ እንቅስቃሴም አደገኛ ነው።›› ሲሉ እይታቸውን አስረድተዋል፡፡

ወደፊት እንዴት መጓዝ አለብን?