Get Mystery Box with random crypto!

ፖለቲካና ሀይማኖት ምን እና ምን ናቸው? የሀይማኖት እና የፖለቲካን የግንኙነትና የማይታለፉ መስመ | ዘሪሁን ገሠሠ

ፖለቲካና ሀይማኖት ምን እና ምን ናቸው?

የሀይማኖት እና የፖለቲካን የግንኙነትና የማይታለፉ መስመሮች በቅጡ ያለመረዳታችን ፥ በ20ኛው ክ/ዘመን ላይ የሚገኙ ኃላቀርና ማሰብ የማይችሉ ህዝቦች ወደምንባልበት አሳፋሪ የታሪክ አዘቅት ውስጥ ይዘፍቀናል ብዬ አምናለሁ፡፡

እውነት ለመናገር! "ሴኩላሪዝም" የሚለው ዘመናዊ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ ከመምጣቱ ቀደምት ባለው የአለም ታሪክ ውስጥ ፥ ፖለቲካውን የሚዘውሩትም ሆኑ የሀገረ መንግስታት ጥንስስ የሚጠነሰሰው በተለያዩ ሀይማኖቶችና ተቋማቶቻቸው ዙሪያ ነበረ፡፡ የሀገር ምስረታ ታሪክ ሲነሳ የሆነ ሀይማኖት መጠቀሱም ከዚሁ የመጣ ነው፡፡ በአጭሩ ሀይማኖቶች ፖለቲካውን የበላይ ሆነው ሲመሩባቸው የነበሩ አያሌ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያም በዚህ ታሪክ ውስጥ ያለፈች ቀደምት ሀገር ነች፡፡

ምንም እንኳ (በተለይ ካለፉት 5 አመታት ወዲህ) በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችና የተለያዩ ክስተቶች፣ እኛ ኢትዮጵያውያንን ስለራሳችን ያለንንና የነበረንን በጎ ግንዛቤ ጥርጣሬና ጥያቄ ምልክት ውስጥ እየከተቱን ቢሆንም ፤ ሀይማኖቶች የሀገረ-መንግስቱን ፖለቲካ በመሩበትም ሆነ ይተግበርም አይተግበርም "የሴኩላሪዝም አስተሳሰብ" ከመጣ ወዲህ ፥ የኢትዮጵያ ህዝብ የሀይማኖት ብዘሀነቱን ከነውበቱ ጠብቆ ፥ ተዋዶና ተጋምዶ በመኖር በአለም ሀገራት ታሪክ ከቀዳሚዎቹ የሚጠቀስ ሆኖ ኖሯል ፥ እየኖረም ነው ፥ ወደፊትም የሚኖር ይሆናል፡፡

ራሳችንን ተጠይቃዊ በሆነ መልኩ እንድንፈትሽ ፥ ነባራዊ የሀገራችን ሁኔታ እንረዳ ዘንድ ፤ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር ፈረደ እንዲሁም ፓኪስታናዊ የታሪክ ተመራማሪና ምሁር ፕ/ር ሙባረክ አሊን ጨምሮ በዘርፉ ጥናቶች ያደረጉ ምሁራንን ሀሳብ በማካተት ዘ - ማለዳ የድህረ-ገፅ መፅሔት ከወራት በፊት ካወጣችው ፅሁፍ ቀንጨብ አድርጌ ፥ ለአቀራረብ አመቺ በሆነ መልኩ ላጋራችሁ ወደደሁ! ሀሳቦቹ ለንባብ ቢንዛዙም ጠቃሚና ሁለንተናችንን የሚያሳዩ ቁምነገሮች ይዘዋል ብዬ ስለማምን ፥ በትእግስት አንብባችሁ ለሌሎች እንድታጋሩ እጠይቃለሁ!

ፖለቲካና ሀይማኖት ምን እና ምን ናቸው?

" የእምነት ተቋም እና አገረ መንግሥት ወይም በዚህ አውድ ሀይማኖት እና ፖለቲካ፣ ሕዝብ የጋራቸው ነው!" ሲሉ በማውሳት ሀሳባቸውን የሚገልፁት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ውሂበ እግዜር ፈረደ ፤ በዓለም ታሪክ ሂደት የአገረ መንግሥት አመሠራረት ከቤተ እምነት ውስጥ እንደነበርና በተለይም የፊውዳል ስርአት በነበረባቸው አገራት ይህ ይስተዋል የነበረ ሲሆን በዛም ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ሳይቀር የካቶሊክ ቤተክርስትያን ፖለቲካውን ይመራው እንደነበር በዋቢነት በመጥቀስ ሀሳባቸውን ይገልፃሉ፡፡

‹‹በሕዝቡ ዘንድ ለረጅም ጊዜ መሪ ወይም ገዢ ከላይ [ከሰማይ] ነው እንጂ ምድራዊ ኃይል ገዢ መሪ መሆን አይችልም የሚል አሳቤ ነበር፡፡›› ያሉት ውሂበእግዜር፥ ከዛ በኋላ ቀስ በቀስ የሴኩላሪዝም ጽንሰ ሐሳብ፣ በተለይም የማርክሲስት ሐሳብ ሲመጣ ዕይታዎች ተቀይረዋል። በዚህ መሠረት የሰማዩና የምድሩ መንግሥት የተለያዩ ናቸው። ሰማያዊውን የሚመራ ሀይማኖታዊ ሕግ አለ፥ ሕዝቡን የሚመራ ደግሞ መንግሥት የሚባል ተቋም አለ የሚል መረዳት ላይ መደረሱን አውስተዋል።

ከዚህ በኋላም ሁለቱ የተለያዩ ተቋማት ናቸውና አንዱ በሌላው ጣልቃ አይገባም የሚል ደረጃ ላይ ተደረሰ። ነገር ግን እነዚህ ኹለት ግዙፍ ተቋማት አሁንም በመካከላቸው ያለና የጋራቸው የሆነ ሕዝብ አለ። ኹለቱም የሚያገለግሉት ይህን ሕዝብ ሲሆን ፥ የሕዝብ ደኅንነት እና ሰላም የሚያሳስባቸው ጉዳያቸው ነው። ያም ሆኖ ግን ‘በሴኩላሪዝም› ሲስማሙ፣ በመካከላቸው አንዱ በሌላው ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚል ድንበር ፈጥረው በዛ ተዋስነዋል።

‹‹የሕዝብ ደኅንነት የጋራቸው ነው። ሁለቱም ይመለከታቸዋል፣ በዚህ ላይ በጋራ ይሠራሉ። ይህ ማለት ግን መንግሥት በእምነት ጉዳይ ጣልቃ ይገባል ማለት አይደለም።›› ሲሉ ውሂበእግዜር ያስረዳሉ።

ሆኖም ግን አሁንም ትግል አለ ብለዋል። የግል ዕይታቸውን ሲያጋሩም፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያለውን ሙግት ጠቅሰዋል። ‹‹ፍትሃዊው የሚሆነውና ይህን ዓለም ማስተዳደር ያለበት ሰማያዊ ኃይል ነው ወይስ ምድራዊ ኃይል ነው የሚለው ክርክር ረጅም ጊዜ የቆየ ነው፣ አሁንም ያከራክራል።›› ብለዋል።

ፕ/ር ሙባረክ አሊ ፓኪስታናዊ የታሪክ ተመራማሪና ምሁር ናቸው። "ታሪክ ሲጻፍ አንጻሩ ከብዙኀኑ ሕዝብ የሚነሳ መሆን አለበት" በሚል ዕይታቸው እና በዛ ቅኝት በጻፏቸው በርካታ መጽሐፍት እውቅናን አግኝተዋል። እኚህ ሰው ‹ሀይማኖት እና ፖለቲካ፤ ግንኙነት፣ ልዩነትና ግጭት› በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፤ ሀይማኖትና ፖለቲካ እኔ ለቅደም፣ እኔ ልምራ ሲባባሉ የሚፈጥረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ሀይማኖት የፖለቲካ የበላይነቱን ካገኘ፣ ግቡ መለኮታዊ ስርዓትን ማስፈን ነው። እናም ሥልጣን ያገኘው በመለኮታዊ ኃይል መሆኑን በመግለጽ፣ ዓላማው ቅዱስ እንደሆነና ሕዝቡንም በመንፈሳዊ መርህ ነው መመራት ያለበት ይላል።

በአንጻሩ ፖለቲካ የበላይነትን ባገኘበት አውድ ደግሞ ፥ ሕግ ይቀይራል፣ ፖሊሲና ስርዓት ይወጣል። በዚህም ፖለቲካው ‹የእኔ ግብ የማኅበረሰብ ፍላጎትና ጥያቄን ማሟላት ነው።› በማለት መመሪያውንም ከዓለም ስርአት አንጻር ይቀርጻል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ፕሮፌሰር ሙባረክ የታሪክ አስረጂዎችን በዋቢነት እየጠቀሱ ሲያስረዱ ፤ " ከሀይማኖትና ከፖለቲካ ጋር የተገናኙ ሦስት አካሄዶች አሉ" ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንደኛው ፖለቲካና ሀይማኖት በጋራ የሚሠሩበት ነው። በዚህም ኹለቱም ተባብረው የፖለቲካ ኃይልን ጠቅልለው ይይዛሉ።

በሁለተኛው ደግሞ ፖለቲካ የበላይነቱን የሚይዝበትና እንደውም ሃይማኖትን ለራሱ ጥቅም የሚያውልበት ነው። በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደግሞ በሁለቱ መካከል የሚፈጠር መለያየት ነው። በዚህም ሀሁለቱ አካላት እንደ ተቀናቃኝ ይሆናሉ።

ታድያ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ይህን ነጥብ ሰብሰብ ሲያደርጉት፣ " በሀይማኖትና በፖለቲካ መካከል ትስስር ሲፈጠር ፍጹም የሆነ አምባገነን ስርዓት ይፈጠራል!" ባይ ናቸው። በአንጻሩ ሁለቱ የተጋጩ እንደሆነ ደግሞ ሁለቱም ሰዎችንና ያላቸውን ሀብት በመጠቀም እርስ በእርስ ለመፎካከርና ኃይል ለማግኘት ይጥራሉ። በዚህም የተነሳ የሚጠቀሙበትን ሰው/ሕዝብ ከማኅበራዊ ሕይወት መስመር ያናጥቡታል።

ከሁለቱ በተለየ ግን ሀይማኖት በፖለቲካ ተጽእኖ ስር ሲወድቅ፣ ማኅበረሰባዊ ፍልስፍና ፣ ሥነጽሑፍ እንዲሁም መሠል የወል ጉዳዮች ላይ አስተዋጽኦ ያበረክታል ይላሉ። እርሳቸው "የሀይማኖት አቅም ሲቀንስ ወይም ገመዱ ላላ ሲል የሰዎች ነጻነት ይጨምራል።" የሚልም እምነት አላቸው፡፡

ይህ በሌላ አገላለጽ ሀይማኖት ዘመን አመጣሽ የሆኑ እሳቤዎችንና አካሄዶችን የሚቀበል ባለመሆኑ ወይም ከብዙው የዴሞክራሲና መሰል ፖለቲካዊ ጽንሰ ሐሳቦች ጋር ስለሚጋጭና አብዛኞቹንም ለመቀበል ስለሚቸገር፣ ከፖለቲካው ገለል እንዲል ይመከራል እንደማለት ነው፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ ውሂበእግዜር በበኩላቸው፣ "በዓለማችን አሁንም ሀይማኖታዊ አገር የመገንባት ጥረቶች አሉ!" የሚል መከራከሪያ ነጥቦቹን አንስተው ያስረዳሉ፡፡