Get Mystery Box with random crypto!

በአርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ የሚኖሩ ወገኖቻችን ፥ ዛሬም ከጨፍጫፊው ቡድን ጋር ተፋጠው ፥ የድረሱልን | ዘሪሁን ገሠሠ

በአርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ የሚኖሩ ወገኖቻችን ፥ ዛሬም ከጨፍጫፊው ቡድን ጋር ተፋጠው ፥ የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ይገኛሉ!

በአርሲ የተለያዩ አካባቢዎች ላለፉት ወራት ያለእረፍት በመፈፀም ላይ ያለውና ብዙዎችን የቀጠፈው ጭፍጨፋና ማሳደድ አሁንም ቀጥሎ ዜጎች እያንዳንዷን ደቂቃ በስጋትና በጭንቀት ውስጥ ለማሳለፍ ተገደዋል፡፡

በአርሲ ዞን ጀጁ ወረዳ መርቲ ቀበሌ ቆስጣ የሚባል ሰፈር ትናንት ህዳር 20/2015 ዓ.ም ከቀኑ 5:00-7:00 ሰዓት ድረስ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በከባድ መሳሪያዎች የታገዘ ጥቃት የከፈተው የኦነግ የሽብር ቡድን ፥ አካባቢውን ተቆጣጥሮ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ዘረፋና ድብደባ በመፈፀም ብሎም " ለውጊያ የደረሱ ልጆቻችሁን ስጡን" በማለት ህዝቡን ሲያሸብር ውሎ ወደሌሎች ቀበሌዎች ሲያመራ ፥ ከግማሽ ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ ሰፍሮ የሚገኘው የመንግሥት ሰራዊት በዝምታ ከመመልከት ውጭ ዜጎችን ሊታደግ አለመቻሉ ፥ ለጥቃት የተዳረገው ህዝብ ተስፋ ቆርጦ ከአካባቢው እንዲሰደድ እያደረገው መሆኑ ተገልጿል ፡፡

ቡድኑ በዚህ ሰአት በዚሁ ዞን ጀጁ ወረዳ መርቲ ቀበሌ እና በአዋሳኞቹ ተስፋ ህይወት ፣ አጫሞ ፣ አዲስ ሂወት ፣ መንበሪ ሂወት የሚባሉት ቀበሌዎች ላይ ባለሀብትና ገንዘብ አላቸው ተብለው የሚታመኑ ነዋሪዎችን ፥ በየቤቱ እየገባ በመዝረፍና በማሸበር ላይ የሚገኝ ሲሆን ነዋሪዎቹ በከፍተኛ ፍርሃት እና ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ባለፉት ሳምንታት በእነዚህ ቀበሌዎች ህፃናትና ሴቶችን ጨምሮ በርካቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉና ማፈናቀሉ የሚታወስ ነው፡፡