Get Mystery Box with random crypto!

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ 6 ቀበሌዎች በአሁኑ ሰአት በኦነግ ሸኔ ከበባ | ዘሪሁን ገሠሠ

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ 6 ቀበሌዎች በአሁኑ ሰአት በኦነግ ሸኔ ከበባ ውስጥ ሆነው የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ይገኛሉ!

" እልቂት ከመፈፀሙ በፊት በአስቸኳይ የሚደርስልን አካል ካለ ይታደገን! >> _ ነዋሪዎች

በየጊዜው የእልቂት አድማሱን እያሰፋ የዜጎችን ህልውና ስጋት ውስጥ ጥሎ የሚገኘው "ኦነግ-ሸኔ" በሚል የዳቦ ስም የሚጠራው የሽብር ሀይል ፥ በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸውና በየጊዜው ዘረፋና ግድያ ከሚፈፅምባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች መካከል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ አንዷ ነች፡፡

ይህ ቡድን በወረዳው ካሉ ወደ40 የሚጠጉ ቀበሌዎች መካከል እስከአሁን በይፋ የማይንቀሳቀስባቸው 6ት ቀበሌዎች ብቻ ሲሆኑ ፥ በእነዚህ ቀበሌዎች በብዛት የሚኖሩት አማራዎች ላለፉት 16 ወራት የእርሻ ስራቸውን ትተው ቀን ከሌት ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ከዚህ ቡድን ጋር እየተፋለሙ እንደሚገኙ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡

ቡድኑ ከሰሞኑ እነዚህን ቀበሌዎች አፀዳለሁ ብሎ በሁሉም አቅጣጫዎች በከባድ መሳሪያዎች የታገዘ ጥቃት እየሰነዘረ እንደሚገኝ የተናገሩት የአይን እማኞች ፥ ቡድኑ በትናንትናው እለት ምሽት አጥናፉ በተሰኘች ቀበሌ ዘልቆ በመግባት በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በከፈተው ድንገተኛ ጥቃት 3 የአንድ ቤተሰብ አባላትን ገድሎ ሁለት በከባድ ሁኔታ አቁስሎ ወደ15 የቀንድ ከብቶቻቸውን መውሰዱን ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ሠአት "አሮጂ" ከተሰኘችው ቀበሌ ላይ ሰፍሮ የሚገኘው የኦነግ ሰራዊት " ለሌቱን ጭፍጨፋ እንደሚፈፅም መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ከስድስቱ ቀበሌዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በእግር ተጉዘው ወደአጎራባቿ የደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ዳርጌ ከተማ እየተሰደዱ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

"ጥቂት ሆነን በኃላ ቀር መሳሪያ ፥ እስከአፍንጫው ዘመናዊ መሳሪያዎች ከታጠቀው ሀይል ጋር ለ16 ወራት ተናንቀን ቆየን፡፡ አሁን ግን ከአቅም በላይ ሆኖብናል ! " የሚለውና በዚህ ሰአት ከቡድኑ ጋር እየተፋለመ ያለው የመረጃ ምንጬ ፥ " ምናልባት እንደዜጋ የሚቆጥረን የመንግሥት አካል ካለ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከመፈፀሙ በፊት ይድረስልን !" ሲል ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ ገልፇል፡፡

በስፍራው የተወሰነ የክልሉ ልዩ ሀይል ሰራዊት ቢኖርም " ትእዛዝ አልተሰጠንም !" በማለት አንዳችም እርምጃ ከመውሰድና ራሳቸውን ለማዳን እየተፋለሙ ያሉትን አርሶአደሮች ከማገዝ መቆጠቡን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

" ምናልባት ለሊቱን የሚፈጠረው አይታወቅምና መንግሥት በአፋጣኝ ይድረስልን" የሚሉት የመረጃ ምንጮቼ ፥ "የሽብር ቡድኑ ስናይፐር ፣ መትረየስና ዲሽቃ የመሳሰሉትን የርቀት መሳሪያዎች የታጠቀ በመሆኑ በቀላሉ ማጥቃት በሚችልበት ቦታ ሁኖ በከበባ ውስጥ ነን" ሲሉ አሳስበዋል ፡፡

መረጃውን #ሼር በማድረግ ለተጨነቁት ወገኖቻችን ድምፅ እንሁናቸው!