Get Mystery Box with random crypto!

ኢጎ የዘመናችን የሰዎች ማንነት ኢጎ ማለት ከሀሳባዊ ፣ አካላዊ እና ስሜታዊ ቅርፆች ጋር የሚደረ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ኢጎ የዘመናችን የሰዎች ማንነት


ኢጎ ማለት ከሀሳባዊ ፣ አካላዊ እና ስሜታዊ ቅርፆች ጋር የሚደረግ ቁርኝት ነው። በዘወትር አጠቃቀማችን "እኔ" ቀዳሚ ስህተትን ፣ ስለ ራስ የተሳሳተ አረዳድንና ሐሳዊ ማንነትን ያነገበ ነው። ይሄ ታዲያ ኢጎ ይባላል።

ኢጎ ሁልጊዜ ከቅርፅ ጋር ቁርኝት ሲሆን ፣ እራስን በሆነ ቅርፅ መፈለግ ፣ ፈልጎም ማጣት ነው። ብዙዎች አሁን ድረስ ከማያቋርጥ ፣ ተደጋጋሚና እርባና ቢስ የሀሳብ ጅረት ጋር ሙሉ በሙሉ የተቆራኙ ናቸው። ከሀሳባቸዉና ተከትሎ ከሚመጣዉ ስሜት ዉጪ እኔ የሚባል ነገር የላቸዉም። በመንፈሳዊነት አለመንቃት ትርጉሙም ይኸዉ ነው። በአእምሮአቸው ውስጥ የማያቋርጥ ድምፅ እንደሚመላለስ ስትነግራቸው ፣ ላለመቀበል ብስጭት ብለው "የምን ድምፅ?" ይሉሀል። በርግጥ ድምፁ የማይመለከቱትና የሚያስበው አእምሮአቸው ነው ፤ ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠራቸው አንድ አካል አድርገህ  ልትወስደው ትችላለህ።

❖ የኢጎ ይዘትና መዋቅር ፦ የኢጎ መነሻ አእምሮአችን ሲሆን ኢጎአዊ አእምሮአችን ሙሉ በሙሉ በትናንትናችን የተቃኘ ነው። ቅኝቱም በሁለት የተገመደ ሲሆን ይዘትንና መዋቅርን ያጠቃልላል። መጫወቻው ስለተወሰደበት በጥልቅ ስቃይ የሚያለቅሰውን ህፃን ጉዳይ ብንመለከት ፣ መጫወቻው ይዘትን ያመለክታል። በሌላ ይዘት ፣ በሌላ መጫወቻ ወይም እቃ ሊተካ ይችላል። የምትቆራኝበት ይዘት ፣ በአካባቢህ ፣ በአስተዳደግህ እና በዙሪያህ ባለው ባህል የተቃኘ ነው። የአንድን ሰው ማንነት ለማጠናከር ሲባል ከነገሮች ጋር የሚደረግ ያልተስተዋለ ቁርኝት ፣ በኢጎአዊ አእምሮአችን መዋቅር ላይ የተመሰረተ ነው። 

ኢጎን ህያው የሚያደርገው መሰረታዊ የአእምሮአችን መዋቅር  'መቆራኘት'  ነው። ለምሳሌ

ከቁሶች ጋር ቁርኝት ፦ በዚህ ቁሳዊ አለም አካላዊ ማንነታችን ይኖራልና እቃዎች አስፈላጊና ሊተዉ የማይችሉ የሕይወታችን ክፍሎች ናቸው። ነገር ግን ቁሶችን ለማንነታችን ማጠናከሪያ አልያም እራሳችንን በእነርሱ ውስጥ ለማግኘት ከሞከርን በእርግጥ ልናወድሳቸው አይቻለንም። የዘመናችን አንዱ በሽታ ንብረትን ማባዛት የሆነው ለዚህ ነው። የሆንከውን ህይወት ማጣጣም ሳትችል ስትቀር ፣ ህይወትህን በነገሮች ለመሙላት ትባክናለህ። የተወሰኑ የያዝካቸው ንብረቶችህ የተፈላጊነት ወይም የታላቅነት ስሜትን  በጥቂቱም ቢሆን ይጭሩብሀል? እነዚያን ነገሮች ስታጣ ነገሮቹ ካላቸው ሰዎች አንፃር ትንሽነት ይሰማሀል? ለማንነትህ ያለህን ዋጋ ለመጨመር ስትል ያሉህን ንብረቶች በየአጋጣሚው አውጥተህ ለማሳየት ትሞክራለህ?

ከአካልህ ጋር ቁርኝት ፦ ከቁሶች ውጭ ያለው ሌላው መሰረታዊ ቁርኝት ከ "የእኔ "አካል ጋር የምታደርገው ቁርኝት ነው። አካል ወንድ ወይም ሴት ነው። ስለዚህ ወንድ ወይም ሴት መሆን የብዙዎችን የማንነት ስሜት ለመፍጠር ጉልህ ድርሻ ይወስዳል።
በምዕራቡ አለም ደግሞ ማንነቴ ነው ብለህ ለምታስበው ስሜት ጉልህ ድርሻ የሚወስደው የአካልህ ሁኔታ ነው። ጥንካሬው ወይም ደካማነቱ ፣ ከሌሎች አንፃር ያለው ውበት ወይም አስቀያሚነት ነው። ለብዙዎች ለማንነታቸው ዋጋ ያለው ስሜት ፣ ካላቸው አካላዊ ጥንካሬ ፣ መልካም ገፅታ እና ውጫዊ ገፅታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ብዙዎች አካላቸው አስቀያሚ ወይም ጎዶሎ መስሎ ስለሚታያቸው የኮሰሰ የማንነት ስሜት ይሰማቸዋል።

ምንጭ ፦ አዲስ ምድር (ኤክሀርት ቶሌ)
ተርጓሚ ፦ ኦስማን መሐመድ
                 
                   ይቀጥላል

@Zephilosophy
@Zephilosophy