Get Mystery Box with random crypto!

ሰው ከእንስሳ በምን ይለያል? ምንጭ ፦ የፍልስፍና አፅናፍ ፀሀፊ    ፦ አለማየሁ ገላጋይ የሰው | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ሰው ከእንስሳ በምን ይለያል?

ምንጭ ፦ የፍልስፍና አፅናፍ
ፀሀፊ    ፦ አለማየሁ ገላጋይ

የሰው ልጅ ከእንስሳት ሁሉ የሚለይበት መሰረታዊ አፈጣጠር አለው የሚለውን አመለካከት መጠራጠር የጀመሩት አንዳንድ የቅርብ ጊዜ ፈላስፎች ናቸው፡፡ ከፕሌቶ አንስቶ እስከ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በተዋረድ የተዘረጋ የምዕራባውያን የእሳቤ ባህል ውስጥ ሰውና ሰው ብቻ ምክንያታዊ እንስሳ ነው በሚል ተደምድሞ ቆይቷል፡፡ ይሄ ሰውን ከእንስሳት ሁሉ የተለየ አድርጐ የሚያስቀምጠው ፍልስፍና ሰው ብቻ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን ከሚያስተምረው ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር የተስማማ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡

በእንግሊዛዊው የተፈጥሮ ሳይንስ ሊቅ ቻርልስ ዳርዊን ዘመን ተቃራኒው አመለካከት ብቅ ማለት ጀመረ፡፡ አመለካከቱ ከሳይንሱ ቤተሰብ ወጥቶ እስከ ልሂቃኑ ድረስ የተዛመተ ነበር᎓᎓ የዳርዊን አስተምህሮት ንድፈ ሀሳብ አንተም እንደምታውቀው የሰው ልጅ እና የዝንጀሮ የዘር ግንድ አንድ ነው ብሎ ደምድሟል፡፡ ድምዳሜው ወዴት እንደሚያመራ ግልፅ ነው፡፡ የሰው ልጅ ስር መሰረታዊ የዝግመተ ለውጥ ምርምር ሰው ከአጥቢ እንሰሳት ሁሉ የሚለየው በአስተሳሰብ ደረጃው ብቻ እንደሆነ ያስተምራል፡፡ የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪዎቹ ሰው ብቻ ምክንያታዊ እንስሳ ነው ለሚለው የቀድሞ ድምዳሜ ሌላ የምርምር መዳረሻቸውን ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ በሰውና በተቀሩት እንስሳት መካከል ያለው አስተሳሰብ አንድ ነው፡፡ ሰው ግን ላቅ ያለ የአስተሳሰብ ደረጃ አለው ይላሉ፡፡

የሰው ልጅ ሌሎች እንሰሳት የሌላቸው ኃይል እንዳለው ማረጋገጫ የሚሆነን አንዳንድ ምሳሌዎችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ የሰው ልጅ በአግባቡ የሚያከናውናቸው እንስሳት ግን ጨርሶ የማይሞክሩት ነገር አለ፡፡ እሱም
አንዳንድ የሚያበጃጃቸው ነገሮቹ ናቸው፡፡

እርግጥ ነው ንቦች ? ፎ እንደሚሰሩ አውቃለሁ:: ወፎች ጎጆአቸውን፤ ፍልፈሎች ጉድጓዳቸውን ያበጃሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የእንስሳቱ ተግባር በደመነፍሳዊ ግፊት የሚከናወኑ ናቸው᎓᎓ ወፎች ሁሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተቀባበሉ የሚሰሩት ያንኑ ተመሳሳይ ጎጆ ነው። ይሄ የሚያሳየን የወፍ ጐጆ የደመነፍስ ግፊት እንጂ በአስተሳሰብ መዳበርና በነፃነት የሚገኝ የጥበብ ውጤት አለመሆኑን ነው። ቤት መገንባት፣ ድልድይ ማበጀትና በመሳሰሉት ተግባራት ላይ የሰው ልጆች የፈጠራ ችሎታቸውን ያውላሉ፤ አንዱን ከሌላኛው ይመርጣሉ፤ በዚህም ሌሎች እንሰሳት የሌላቸው ትክክለኛ የጥበብ ተስዕጦ ባለቤት እንደሆኑ ይመሰክራሉ፡፡

የሰው ልጅ ብቻ ነው የማምረቻ ማሽኖችን የሚሰራው፡፡ ልብ በል ሰው የሚፈልገውን ነገር የሚሰራት ማምረቻ። ሌሎቹ እንሰሳት ባገኙት መሳሪያ ይጠቀሙ እንዳደሆን ነው እንጂ ጥሬ እቃውን ወዳለቀለት ምርት እየቀየረ በፍጥነት የሚስራ ሌላ ማሽን አይሰሩም፡፡ ይህም ሰውን ከሌሎች እንሰሳት ሁሉ የበለጠ ነገሮችን የማበጃጀት ልዩ ችሎታ እንዳለው የሚያመላክተን ምሳሌ ነው፡፡

እንስሳት ምክንያታዊነት እንዳላቸውም ጠቆም አድርገሃል፡፡ እኔ እንደሚገባኝ የተሻለ ትክክል የምንሆነው እንሰሳት ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ ከችግር የሚወጡበት ተፈጥሯዊ ግፊት እንዳላቸው የተናገርን እንደሆነ ነው፡፡ ወይም የሚፈልጉትን ለማግኘት እንደዚያው የተፈጥሯዊ ግፊት ዘዴ እንደሚዘይዱ ያሰብን እንደሆነ ነው፡፡ የእንስሳትን «አስተሳሰብ» ሁሉ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ልናየው ይገባል። የትኛውም እንስሳ ለማሰብ ቁጭ አይልም፡፡ ፈላስፎች ሆነ የሂሳብ ሊቶች የሚያከናውኑት ነገር ሁሉ ለህይወት ከሚያስፈልግ የተፈጥሮ ደመነፍሳዊ ግፊት ነፃ ነው፡፡

የሰው ልጅ አስተሳሰብ በዙሪያ ጥምጥም የሚከናወን ግራ ፈትልና ቋንቋ የተቀላቀለበት መሆኑ እንሰሳት ከሚጠቀሙበት ችግር መፍቻ የተለየ ያደርገዋል። በእርግጥ እንሰሳትም ስሜታቸውን የሚገላለጡበት የእርስ በእርስ መግባቢያ ድምፅ ያወጣሉ፡፡ ነገር ግን በሃሳብ መካፈል ደረጃ ተግባቦት ያላቸው እንስሳት የሉም፡፡ የነገሮችን ትክክለኛነት ለመተማመን የእሰጥ-አገባ ሙግት የሚገጥሙ እንሰሳት እስካሁን አልታዩም። ይሄንን ለማድረግ የሚችለው አመክኑያዊ እንስሳ ሰው ብቻ ነው::

እንዲህ ያሉ ብዙ መረጃዎችን መስጠት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሰው ከእንስሳት ሁሉ በላይ በተፈጥሮ የተቀባ መሆኑን የሚያመላክት አንድ ማስረጃ አቅርቤ ነገሬን በዚሁ በአቅብ ነው የመረጥኩት፡፡

በታሪካዊ ሂደት እራሱን እያጐለበተና ልምዱን እያዳበረ የመጣ እንስሳ ሰው ብቻ ነው᎓᎓ የተቀሩት እንስሳት በተፈጥሮ ሂደት በመቶ ሺህ ትውልድ ውስጥ የራሳቸውን የአካል ለውጥ አግኝተው ይሆን ይሆናል እንጂ የታሪካዊ ሂደት ለውጥ ተጠቃሚዎች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም በደመነፍስ ከሚወርሱት የአኗኗር ዘዬ ውጭ በትውልድ ቅብብል እያሳደጉ የመጡት እውቀት የላቸውም፡፡ ሰውን ያየን እንደሆን ልምዶቹንና ባህሎቹን ከአንዱ ትውልድ ወደሌላው በማሸጋገር ሀሳቦችንና ተቋማቶቹን በማሻሻል እያደረጀ እዚህ እንደደረሰ ከታሪኩ እንረዳለን፡፡

በእኔ ሐሳብ የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ እንደማንኛውም እንሰሳ ይሁን እንጂ በምክንያታዊነቱ ግን ከተርታዎቹ እንስሳት እራሱን ነጥሎ ልዩ ቦታ የተቀመጠ አስደናቂ ፍጡር ነው፡፡ በዚህና በሌላ ምክንያቶች የዳርዊንን የሰው ልጅ ዝግመተለውጣዊ ንድፈ ሐሳብ የምናጣጥልበትን አቋም እናገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ስለንድፈ ሐሳቦች መያዝ ያለብን አንድ እውነታ አለ፡፡ ንድፈ ሀሳቦች ሐቅን ፈልፍሎ ለማውጫ እንጂ ሐቅን ለንድፈሐሳብ ማዳበሪያ ብቻ መጠቀም እንደሌለብን ነውና፡፡

@Zephilosophy
@Zephilosophy