Get Mystery Box with random crypto!

በዘመነ ሳይንስ የፍልስፍና እጣ ፋንታ ምንድነው? ምንጭ ፦ የፍልስፍና አፅናፍ ፀሀፊ ፦ አለማየሁ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

በዘመነ ሳይንስ የፍልስፍና እጣ ፋንታ ምንድነው?

ምንጭ ፦ የፍልስፍና አፅናፍ
ፀሀፊ ፦ አለማየሁ ገላጋይ

እስኪ መጀመሪያ ሳይንስ ሊያደርግና ላያደርግ የሚችላቸውን ነገሮች ለይተን እናውጣ፡፡ የሳይንስ ማዕከላዊ ትኩረቱና ነጠላ ግቡ የማያወላዳ መረጃ ማግኘት ነው፡፡ ተመራማሪዎቹ በቁስ አካላዊና በማህበራዊ ጥናታቸው የሚታዩ ክስተቶችንና ለውጦችን ይመዘግባሉ ጠባያትን በትኩረት ይከታተላሉ፡፡ ህዋ ውስጥ ያለውን የፕላኔቶች እንቅስቃሴ በትክክል ለመረዳት ሙሉ ኃይላቸውን ይጠቀማሉ፣ የቁስ አካልን ውስጣዊ ሁናቴ የሰውነታችንን አሰራርና ማህበራዊ እንቅስቃሴን ሆነ ሰዋዊ ባህሪን በመመርመር እንዲህ ነው እንዲያ ነው ይላሉ።

የሳይንስ ዕውቀት አስፈላጊነቱ ምንድነው? እንግሊዛዊው ፈላስፋና ቀደምት ሳይንቲስት ፍራንሲስ ቤከን ይሄን ጥያቄ የሚመልሰው «ኃይል ይሰጠናል» በማለት ነው፡፡ ምን አይነት ኃይል? ሳይንስ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ያሉ አንዳንድ ቁስ አካላዊና ማህበራዊ ምስጢራትን መርምረን እንድናውቅ ማስቻሉን ነው «ኃይል» ሲል ቤከን የሚገልፀው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንዳንድ መጠቀሚያ ቁሳቁሶች በሳይንስ አማካኝነት መፈብረካቸው የሰው ልጅ ህይወትን አቅልለው ፍጥነት ጨምረውለታልና ቤከን «ኃይል» ቢለው ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ በምህንድስናው ሆነ በህክምናው ዘርፍ የተገኙ ዕውቀቶች ለጤናና ለኑሮ መሻሻል እንደ ዋነኛ መሸጋገሪያ ድልድይ ጠቅመዋል።

እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያሻው ከሳይንስ የሚገኘው «ኃይል» ለኑሮ ማሻሻያና ለህይወት ማቅለያ ብቻ እንደማይውል ነው፡፡ ሰው ሰውን መግደያና አካባቢውን ማጥፊያ፣ ሰላማዊ ህይወቱን ማደፍረሻ... አድርጐ ከሳይንስ ያገኘውን «ኃይል» ስራ ላይ ያውለዋል፡ በሌላ አገላለፅ እኛ ሰዎች ሳይንስ የሚሰጠንን «ኃይል» ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር እንጠቀምበታለን ማለት ነው፡፡ የጥፋት ይሁን የመልካም ነገር ፍላጐታችንን እውን እናደረግ ዘንድ ሳይንስ ነገሮችን ያመቻችልናል፣ ሳይንስ በራሱ ምንም አይነት የስነ ምግባር ልኬት የሌለበት ልቅ ዘርፍ ነው ማለት ነው፡፡ ሰው በሳይንስ የሚያስፈልገውን ብቻ ሳይሆን የማያስፈልገውና መጥፊያውንም ነገር
ያገኛል፡፡

እንግዲህ አስተያየትህ ትክክል ሆኖ ሳይንስ ፍልስፍናን ሊተካ ይችል የነበረው ከሳይንስ የምናገኘውን ኃይል ለጥሩ ነገር ብቻ የምናውለው ቢሆን ነበር። በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች ፍልስፍናን ከሳይንስ ጋር እያወዳደሩ ፍልስፍና አስፈላጊ እንደሆነ ያስባሉ፤ ምክንያታቸው ግልፅ ነው:: በፍልስፍና የዕለት ተዕለት መጠቀሚያ ቁሳቁስ ማምረት ስለማይቻል ነው:: በእኔ አስተያየት ፍልስፍና ከሳይንስ በተሻለ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ዘርፍ ነው፡፡ ምክንያቱም ሙሉ ትኩረቱን ትክክለኛ የህይወት አቅጣጫን ማፈላለግና መጠቆም ላይ በመጣሉ እንደ ሳይንስ ላይ ላዩን በማጫፈር ለመሸንገል አይሞክርምና ነው᎓᎓ ፍልስፍና ለህይወታችን አስፈላጊና የማይተካ ሚና አለው፡፡ ይሄንን ማሰሪያ ድምዳሜ እንዳብራራው ይፈቀድልኝ፡፡

ደስታ ምንድነው? የደስታ መገኛውስ? በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ያለን ኃላፊነት ምንድነው? እንዴት ያለ መንግስት ቢቋቋም ፍትህና ርትዕ ይሰፍናል? ምን አይነት ህገ መንግስት የህብረተሰቡን የጋራ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል? ነፃነት ምንድነው? የሰው ልጅ ነፃነት ውስጥ ምን አለው?... ለእነዚህና መሰል ጥያቄዎች በምንስጠው ምላሽ ማህበራዊ ደህንነታችንና የህይወት መስመራችን ይወሰናል፡፡ እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ደግሞ ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት በሳይንስ ሊሆን አይችልም:: አሁንም ሆነ ወደፊት ሳይንስ በእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ተሳትፎ እንደማይኖረው የተረጋገጠ ነው:: ጉዳዩ ሙሉ በሙሉ የፍልስፍና ብቻ ይሆናል፡፡ ጥያቄዎቹ በፍልስፍና ካልተነሱና ምላሽ ካልተሰጠባቸው ህይወታችን ዓለም ላይ ያለ አቅጣጫ መጠቆሚያ እንደሚንከላወስ መርከብ ይሆናል፡፡ ንፋስ በራሱ ወደፈለገበት የሚነዳው ኃይል አልባ መርከብ፡፡

የፍልስፍና ቅሪት ካለንና መርከባዊ ግዛቲቷ ጥቂት ኃይል ካመነጩች በፍፁም ከፍተኛ አደጋ ላይ ልንወድቅ አንችልም፡፡ ነገር ግን አንተም እንዳልከው በዚህ በአቶሚክ ዘመን በከፍተኛ ፍጥነትና ኃይል በሳይንስ የምንፈተለክ ከሆነ ትክክለኛውን  ከሐሰተኛው የህይወት መታጠፊያ በፍልስፍና ልንፈትሽ ይገባል፡፡ ያ ካልሆነ ምን ጊዜም አደጋው ፊት ለፊታችን የተጋረጠ ነው::

በእውነትና በሐሰት መካከል ያለውን ልዩነት የምንፈትሸው በፍልስፍና እንጂ በሳይንስ አይደለም፡፡ ከተፈጥሯችን ጋር የተስማማውን የኑሮ አቅጣጫን አብላልተን የምንደርስበት አሁንም በፍልስፍና እንጂ በሳይንስ አይደለም፡፡ ሳይንስ በቁስ አካል ላይ የሚያሳየውን ትጋት ፍልስፍና በህይወት አቅጣጫና በስነ ምግባር ላይ ያከናውነዋል:: እያንዳንዱ የእውቀት ዘርፍ ሌሎቹ የእውቀት ዘርፎች የማይደርሱበት የራሱ ጥያቄና ምላሽ አለው:: ለዚህ ነው በተለያየ መንገድ ሁሉም አይነት የእውቀት ዘርፍ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኘው፡፡

በእኔ ምልከታ በየትኛውም ባህል ሆነ ስልጣኔ ውስጥ እጅግ አስፈላጊውን የሰው ልጅ ጥያቄ በመመለስ የተካነው ፍልስፍና እንጂ ሳይንስ አይደለም፡፡ በእርግጠኝነት ለሳይንስ ከፍተኛ ትኩረት በሰጠን ቁጥር የዚያኑ ያህል ፍልስፍና በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያስፈልገን ግልፅ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም በሳይንስ የበለጠ «ኃይል» ባገኘን ቁጥር በፍልስፍና የበለጠ አቅጣጫ ጠቋሚ ያሻናልና ነው፡፡

@Zephilosophy
@Zephilosophy