Get Mystery Box with random crypto!

ሾፐንሀወር ምንጭ ፦ የፍልስፍና ሀሁ ፀሀፊ ፦ በላይ ደስታ የሾፐንሃወርን የትውልድ ቦታ አንዳን | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ሾፐንሀወር

ምንጭ ፦ የፍልስፍና ሀሁ
ፀሀፊ ፦ በላይ ደስታ

የሾፐንሃወርን የትውልድ ቦታ አንዳንዶቹ፣ ጀርመን ውስጥ ፍራንክፈርት በተባለ ቦታ የተወለደ መሆኑን ሲገልጹ፣ ሌሎቹ ደግሞ፣ በፖላንድ ዳንዚግ በተባለ ቦታ ከነጋዴ ቤተሰብ እ.ኤ.አ የካቲት 22 ቀን 1788 የተወለደ መሆኑን ይገልጻሉ። ሾፐንሀወር በህይወት ዘመኑ፣ ልጅም ሚስትም ሳይኖረው፤ ከነጋዴ አባቱ የወረሰውን ሀብት ነግዶ ለማብዛት ሳይጥር፣ ለፍልስፍናው ታማኝ ሆኖ በመኖር እ.ኤ.አ. መስከረም 21 ቀን 1860 ጀርመን ፍራንክፈርት በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ማረፉ ተዘግቧል፡፡

ሾፐንሃወር በፍልስፍና ዘመኑ፣ የፕላቶ እና የኢማኑኤል ካንት አምላኪ፣ እንዲሁም የጆርጅ ዊልሄልምና የፍሬድሪክ ሄግል ተቀናቃኝ ነበር። ሾፐንሃወር፤ ምንም እንኳን በሕይወት ዘመኑ በሰራቸው ሥራዎች ብዙም ትኩረት ባይሰጠውም፣ ህይወቱ ካለፈ በኋላ፣ በዘመኑ ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍና ሳይንስ እይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ተጽዕኖ ካሳደረባቸው ፈላስፎች መካከል፤ ፍሬድሪክ ኒቼ፣ ሪቻርድ ዋግነር፣ ሊዮ ቶልስቶይ፣ ሉድቪግ ዊትገንስቴይን፣ ኤርዊን ሽሮዲንገር፣ ጉስታቭ ማህለር፣ ጆሴፍ ካምቤል፣ አልበርት አንስታይን፣ ካርል ጁንግ፣ ቶማስ ማን፣ ጆርጅ ሉዊስ ቦርግስ እና ሳሙኤል ቤኬት እንደሚገኙበት ተጽፏል።

በሾፐንሀወር አስተሳሰብ፣ “የማናቸው ነገሮች ምንነት(ኢሴንስ)፣ ሰዎችንም ጨምሮ፣ እውቀታቸው፣ ምክንያታዊነታቸው ወይም መንፈሳቸው ሳይሆን ፈቃዳቸው ነው” ይል ነበር። ፈቃድ ሲል “ማናቸውንም ነገሮች፣ ከአለቶች ጀምሮ እስከ ሰው ልጅ ኅልው እንዲሆኑ የሚገፋቸውን ጉልበት ነው:: ይህ ጉልበት ምንም ምክንያት የለውም፣ ኅልው ለመሆኑም ምክንያት የለውም፣ ስለሆነም የሰው ልጅ ስቃይ ከዚህ ምክንያት የለሽ እውር ጉልበት ይመነጫል” ብሎ ሾፐንሀወር ያስተምር ነበር።

ሾፐንሀወር ለዚህ ስቃይ ማስታገሻ ይሆናል ብሎ የዘየደው ፈውስ፣ ሰዎች የተሻለ ንቃተህሊና እንዲኖራቸው መምከር ነበር፡፡ የተሻለ ንቃተ ህሊና እንዴት ይገኛል፣ ለሚለው የእርሱ መልስ “የሰው ልጅ ፍላጎቱን ማሟላትን እንዲክድ፣ ጊዜ ሰውቶ እራሱን እንዲመረምርና ምን ቢሰራ ከስቃዩ እንደሚያመልጥ በማሰብ ነው” ይላል። ሾፐንሀወር፣ ለስቃይ ማምለጫ ሊሆን ያስችላል ብሎ ከአዘዘው ተግባር ውስጥ፣ የኪነት ስራዎችን መስራትና የተሰሩትን ማድነቅ፣ በተላይ ሙዚቃ ላይ ማተኮርን ይጠቅሳል። ሙዚቃ፣ በሾፐንሀወር አስተሳሰብ፣ ለሰው ልጆች በሰላምና በፍቅር መኖር አንዱ ምክንያት ነው ብሎ ያምናል።

በፍልስፍና ታሪክ ውስጥ፣ እንደ ሾፐንሃወር ያለ ጨለምተኛ ፈላስፋ ያለ አይመስልም:: ለጨለምተኝነቱ ምክንያት ከአስተሳሰቡ ይመነጫል። ሾፐንሃወር እንዲህ ይላል ፤ “17 አመት ሲሆነኝ የህይወትን አሰቃቂ ገፅታ ለመጀመሪያ ግዜ ተመለከትኩ:: ወጣቱን ቡድሃ ከውብ ቤተመንግስቱ አስወጥተው ጫካ ያስገቡት በሽታ እና ስቃይ እርጅና እና ሞት እኔንም እንቅልፍ ነሱኝ:: እውነታው ይቺ አለም የተሰራችው ሁላችንን በሚወድ ደግ አምላክ ሳይሆን፤ ፍጡራንን ምድር አምጥቶ በስቃያቸው በሚዝናና ክፉ አምላክ መሆኑ ነው" በማለት ይገልጻል።

እንደ ሾፐንሀወር አገላለጽ፣ “ይህን ለአይን የሚያታክት ዝብርቅርቅ አለም፣ ከኋላ ሆኖ የሚዘውር፣ ባይናችን የማናየው አንድ ታላቅ ሃይል አለ:: ፍጡራንን ሁሉ በምድር ላይ የሚያንከራትተው፤ ምድርንም በፀሃይ ዙሪያ የሚያሽከረክረው ይኸው ሃይል ነው። ይህን ሃይል ለማየት፣ እስኪ አንዴ አይናችሁን ጨፍኑና ወደውስጣችሁ ተመልከቱ። ይሄንን ያዝ፣ ያንን አባር የሚል፣ ርካታ የለሽ፣ ዘወትር ወደፊት የሚገፋ፣ በሁላችንም ውስጥ የሚርመሰመስ ሃይል ታያላችሁ” ይላል።

“ይህ ደመነፍሳዊ ኃይል፣ ስለኔም ሆነ ስላንተ ግድ አይሰጠውም። ወደዚህ ምድር አምጥቶ በዚህ እና በዚያ ሂድ እያለ እያታለለ ጉልበታችን እስኪዝል ይጋልበናል፤ ጉልበታችን ሲደክም ሌላ ፈረስ እንድንተካለት ያረግና እኛን አሰናብቶ እሱ ግልቢያውን ይቀጥላል። ይህ ነው የሚባል መዳረሻ የለውም፤ ምኞቱ ዘላለም መጋለብ ነው፡፡ እኛ ሞኞቹ ግን ሀብት፣ ዝና፣ እውቀት ወይም ስልጣን ለመጨበጥ እየሮጥን ነው፤ ይቺን ወይም ያቺን ሴት ያፈቀርነው፣ ይሄን ጥለን ያንን ያባረርነው፣ በራሳችን ምርጫና ፍላጎት፣ ለራሳችን ጥቅም እና ደስታ ይመስላችኋል? ... ይቺ አለም የተፈጠረችው ለሰው ልጅ ደስታ አይደለም። ይህን ለመረዳት ልክ ሴክስ አርገን ስንጨርስ የሚሰማንን ቀፋፊ ስሜት ማየት ብቻ በቂ ነው::” እያለ ያለምን የእሽክርክሪት ህይወት ያማርራል፡፡

እንደ ሾፐንሀወር አስተሳስብ፣ “የተሻለው አኗኗር ይሄን ሃይል በጥንቃቄ ተረድቶ በሱ ላይ ማመፅ ነው” ይላል። “ይሄን ወይም ያንን አባረህ ስትይዝ ደስተኛ ትሆናለህ” ለሚለን ሃይል ጆሮ ሳንሰጥ ምንም ሳንፈልግ ምንም ሳናባርር በርጋታ መኖር። ችግሩ ግን እንዲህ ለመኖር ስንሞክር ድብርት እና ተስፋ መቁረጥ በራችንን ያንኳኳሉ። ለዚህ ደግሞ መፍትሔው በጥበብ እና በተፈጥሮ ውበት መደመም ነው” ይለናል፡፡

@Zephilosophy
@Zephilosophy