Get Mystery Box with random crypto!

ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት 'በኢትዮጵያ ልክ እድገት ያረጋግጣል ተብሎ የተተነበየ ሀገር የለም'? ኢ | ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal

ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት "በኢትዮጵያ ልክ እድገት ያረጋግጣል ተብሎ የተተነበየ ሀገር የለም"? ኢትዮጵያ ፋክት ቼክ ሰፋ ያለ ማጣራትን በዛሬዉ የጠ/ሚ አብይ የምክር ቤት ዉሎ ላይ አደርጓል

ጠ/ሚር አብይ አህመድ ዛሬ በፓርላማ ተገኝተው ከህዝብ እንደራሴዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ዳታዎችን ጠቅሰው ነበር።

ጠ/ሚሩ በዚሁ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት አምና፣ ማለትም እ.አ.አ በ 2022 6.4% እንደነበር፣ ዘንድሮ ቢያንስ 6.1% እንደሚያድግ እንዲሁም በቀጣዩ አመት ተመልሶ 6.4% ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ይሁንና ጠ/ሚር አብይ በዚሁ ንግግራቸው ላይ "በ Sub-Sahara (ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት) በኢትዮጵያ ልክ እድገት ያረጋግጣል ተብሎ የተተነበየ ሀገር የለም፣ በአለምም ፈጣን እድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ የ IMF ዳታ ላይ ዳሰሳ አድርጓል።

የ IMF ዳታ እንደሚያመለክተው ዘንድሮ (እ.አ.አ በ2023) ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ያሉት ከሰሀራ በታች ያሉት የአፍሪካ ሀገራት በቅደም ተከተል እነዚህ ናቸው:

1. ሴኔጋል- 8.3%
2. ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ- 6.3%
3. ርዋንዳ እና አይቬሪ ኮስት- 6.2%
4. ኢትዮጵያ እና ኒጀር- 6.1% ናቸው።

በቀጣዩ አመት ከፍ ያለ እድገት ያስመዘግባሉ የተባሉት ሀገራት ደግሞ:

1. ኒጀር- 13%
2. ሴኔጋል- 10.6%
3. ርዋንዳ- 7.5%
4. ሞዛምቢክ- 8.2%
5. አይቬሪ ኮስት- 6.6%
6. ኢትዮጵያ- 6.4% ናቸው።

ሪፖርቱን በዚህ ሊንክ ማግኘት ይቻላል: https://www.imf.org/en/Publications/REO/SSA/Issues/2023/04/14/regional-economic-outlook-for-sub-saharan-africa-april-2023

በዚህም መሰረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ "በኢትዮጵያ ልክ እድገት ያረጋግጣል ተብሎ የተተነበየ ሀገር የለም" የሚለው ንግግር የተሳሳተ መሆኑን ማየት ይቻላል።

በተጨማሪም ኢንተርኔት በፈረንሳይ እንዲቋረጥ ተደርጓል ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዉ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በፈረንሳይ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ ስለመወሱ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚዲያን በተመለከተ ማብራሪያ በሰጡበት ንግግራቸው “በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ ሰሞኑን ሰምታችኋል ፈረንሳይ ችግር ነበር፣ በአውሮፓ ምድር በፈረንሳይ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ ተወስኗል። የአፍሪካ የተለመደ ነው…” ሲሉ ተደምጠዋል።

ሆኖም ኢትዮዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈረንሳይ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ ተወስኗል በማለት የተናገሩት የተሳሳተ መሆኑን አረጋግጧል።

ነገሩ እንዲህ ነበር:
በፈረንሳይ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ስምንና አርማ በመጠቀም የተጻፈ አንድ ደብዳቤ ባሳለፍነው ዕሁድ በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጨ። ደብዳቤው በሀገሪቱ ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በኢንተርኔት ላይ እቀባ መጣሉን የሚገልጽ ነበር።

ሆኖም የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ወዲያኑ ባወጣው መግለጫ የተሰራጨው ደብዳቤም ሆነ በኢንተርኔት ላይ እቀባ እንዲጣል ውሳኔ ተላልፏል የሚለው መረጃ ሀሠተኛ መሆኑን አስታውቋል።

ኤፒን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ የመረጃ አጣሪ ተቋማትም የመረጃውን ሀሠተኝነት በተመለከተ ዘገባ ሰርተዋል።

በተጨማሪም ፕሬዝደንት ማክሮን ከአንድ ቀን በፊት ከከንቲባዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በኢንተርኔት ላይ እቀባ አለመደረጉን አረጋግጠዋል። ሆኖም ነገሮች ሲረጋጉ ኢንተርኔትን ማቋረጥን የተመለከቱ ደንቦች ሊወጡ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።

Via ኢትዮ ፋክት ቼክ
#ዳጉ_ጆርናል