Get Mystery Box with random crypto!

ሐሙስ ማለዳ! ግንቦት 10/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሐሙስ ማለዳ! ግንቦት 10/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በትግራይ ክልል የሦስት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ትናንት መቀሌ ገብተዋል። አምባሳደሩ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ጋር በሰላም ስምምነቱ አፈጻጸምና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ እንደተወያዩ የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። አምባሳደሩ ወደ ሽሬና አዲግራት ጭምር በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን እንደሚጎበኙ ዘገባው አመልክቷል።

2፤ ገንዘብ ሚንስቴር በተያዘው በጀት ዓመት ከውጭ ምንጮች ለማግኘት የታቀደው 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ እስካሁን እንዳልተገኘ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት መናገሩን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። ሚንስትር አሕመድ ሽዴ በሪፖርታቸው፣ ከታክስ፣ ታክስ ነክ ካልኾኑና ከውጭ አጋሮች ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ 446 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ሚንስትሩ፣ መንግሥት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሰበሰበው ጠቅላላ ገቢ የዕቅዱን 63 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ እንደኾነ ገልጸዋል ተብሏል።

3፤ በደቡብ ክልል ጋሞ እና ደቡብ ኦሞን ጨምሮ በተወሰኑ ዞኖች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ሳቢያ 18 ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማስታወቁን ቪኦኤ ዘግቧል። 919 የክልሉ ነዋሪዎች ደሞ በበሽታው መያዛቸውን ኢንስቲትዩቱ መናገሩን ዘገባው አመልክቷል። ጤና ሚንስቴር በበኩሉ፣ ወረርሽኙ በአራት ክልሎች እንደተከሰተ ገልጦ፣ ከአንድ ዓመት በላይ ለኾኑ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች በመላ አገሪቱ ክትባት ለመስጠት ማቀዱን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጧል። ሚንስቴሩ የክትባት ዘመቻውን ማክሰኞ'ለት በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በናጸማይ ወረዳ አስጀምሬያለኹ ብሏል።

4፤ የኢትዮጵያ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን የላፕሴት የጋራ ፕሮጀክት የሚንስትሮች ስብሰባ ትናንት ጁባ ውስጥ ተጀምሯል። ለሦስት ቀናት የሚቆየው የሚንስትሮች ስብሰባ መሪ ቃል፣ የላፕሴት የጋራ ፕሮጀክትን አፈጻጸም ማፋጠን" የሚል መኾኑን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ስብሰባው የላፕሴት ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን የሚያስችል ሰነድ ያዘጋጃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚንስቴሩ ገልጧል። ኢትዮጵያ በስብሰባው እየተሳተፈች ያለችው፣ የገንዘብ ሚንስትር ደዔታ እዮብ ተካልኝ በመሩት ልዑካን ቡድን ነው።

5፤ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጀኔራል ደጋሎ ልዩ መልዕክተኛ የሱፍ እዛትን ተቀብለው እንዳነጋገሩ የፕሬዝዳንት ኪር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ጀኔራል ደጋሎ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቶችን ለማክበርና ግጭት ለማቆም ዝግጁ መኾናቸውንና የኢጋድ የሰላም ጥረትን እንደሚደግፉ ልዩ መልዕክተኛው ለፕሬዝዳንቱ እንደገለጡላቸው ተገልጧል። የሱዳን ጦር ሠራዊት አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን ባለፈው ሳምንት ልዩ መልዕክተኛቸውን ወደ ፕሬዝዳንት ኪር ልከው ነበር።

6፤ የዩክሬን የእህል ምርት በጥቁር ባሕር በኩል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ የሚያስችለው የዩክሬንና ሩሲያ ስምምነት ትናንት ምሽት ላይ ለሁለት ተጨማሪ ወራት መራዘሙን የውጭ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል። ባለፈው መጋቢት ለሁለት ወራት ብቻ የተራዘመው ስምምነቱ ቀነ ገደቡ ዛሬ ያበቃ ነበር። የስምምነቱ መራዘም በተለይ ለአፍሪካ አገራት ትልቅ እፎይታ እንደኾነ ተገልጧል። ሩሲያ ለውጭ ገበያ በምታቀርበው ማዳበሪያና እህል ምርት ላይ የተጋረጡ ዓለማቀፍ መሰናክሎች ካልተወገዱ፣ ከስምምነቱ እንደምትወጣ ስታስጠነቅቅ መቆየቷ ይታወሳል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja