Get Mystery Box with random crypto!

ሐሙስ ጠዋት! ግንቦት 3/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሐሙስ ጠዋት! ግንቦት 3/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር በአሜሪካ ሎዛንጅለስ ከተማ ከሚኖሩ የኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን ዲያስፖራ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር እንደሚወያዩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። አምባሳደር ሐመር፣ ከትናንት ጀምሮ እስከ ግንቦት 12 በከተማዋ በሚኖራቸው ቆይታ፣ ከአማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬይና ሱማሊያ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ባጠቃላይ ከኢትዮዊያን አሜሪካዊያን ጋር እንደሚወያዩ መስሪያ ቤቱ ገልጧል። የአምባሳደር ሐመርና የኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያኑ ውይይት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሃት መካከል ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰው ሰላም ስምምነት አፈጻጸ፣ በሌሎች የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲኹም የኢትዮጵያዊያን ሴቶችን አቅም በመገንባት ዙሪያ ያተኮረ እንደሚኾን መረጃው አመልክቷል።

2፤ በአዲስ አበባ በርካታ ትምህርት ቤቶች ከ20 እስከ 100 ፐርሰንት የሚደርስ የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ለማድረግ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረባቸውን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። የከተማዋ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ግን፣ የትኛውም ትምህርት ቤት ከተማሪ ወላጆች ጋር ስምምነት ላይ ሳይደርስ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችል ማስጠንቀቁን ዘገባው ጠቅሷል። በከተማዋ ከሚገኙት 1 ሺህ 558 ትምህርት ቤቶች መካከል፣ በቀጣዩ ዓመት የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ለማድረግ መወሰናቸውን ለባለሥልጣኑ ያሳወቁት፣ 1 ሺህ 257 ትምህርት ቤቶች እንደኾኑ ባለሥልጣኑ መናገሩን ዜና ምንጩ አመልክቷል።

3፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት በሱዳኑ ግጭት መጀመርያ ቀናት በፕሬዝዳንታዊ ጽሕፈት ቤቱ ላይ በፈጸመው ጥቃት የአገሪቱን ወታደራዊ መሪ ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃንን ለመግደል ወይም እጃቸውን ለመያዝ ተቃርቦ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል። ጀኔራል ቡርሃንም ክላሽንኮቭ አንስተው እንደተዋጉና በጥቂት ቀናቶች ውጊያ ከ30 በላይ የጀኔራል ቡርሃን የግል ጠባቂዎች እንደተገደሉ ከግል ጠባቂዎቻቸው መስማቱን ዜና ምንጩ ጠቅሷል። የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ተዋጊዎች ባኹኑ ወቅት የአገር ውስጥ ጉዳይ፣ የፖሊስ መስሪያ ቤቱን እና ሌሎች ተቋማትን ሕንጻዎች ተቆጣጥረውና የካርቱም መውጫና መግቢያ መንገዶች ላይ ኬላዎችን አቁመው ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ሮይተርስ ጨምሮ ዘግቧል።

4፤ የዲሞክራሲያዊት ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሽስኬዴ በምሥራቃዊ ኮንጎ የሠፈረውን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ጦር አፈጻጸም ክፉኛ መተቸታቸውን የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘግቧል። በቀጠናዊው ጦር እና በኮንጎ አማጺያን መካከል "መቻቻል ይታያል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ባሁኑ ወቅት የቀጠናው ጦር እና አማጺው "ኤም-23" ባንድ ላይ እየኖሩ ነው ማለት ይቻላል ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የቀጠናው ጦር በሰኔ ከኮንጎ ሊወጣ እንደሚችልም ፕሬዝዳንቱ ፍንጭ ሰጥተዋል ተብሏል። ካለፈው ኅዳር እስከ መጋቢት፣ ኬንያ፣ ቡሩንዲ፣ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን ከአገሪቱ መንግሥት ጋር ወግነው አማጺዎችን ለመውጋት በምሥራቅ ኮንጎ ወታደሮቻቸውን ማስፈራቸው ይታወሳል። የደቡባዊ አፍሪካ ቀጠናዊ ማኅበረሰብ መሪዎች የቀጠናውን ጦር ለተመሳሳይ ተልዕኮ በምሥራቅ ኮንጎ ለማስፈር ሰሞኑን መወሰናቸው ይታወሳል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                  
@emsmereja