Get Mystery Box with random crypto!

ረቡዕ ማለዳ! ሚያዝያ 18/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ኢጋድ የኢትዮጵያ መንግሥትና | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ረቡዕ ማለዳ! ሚያዝያ 18/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ኢጋድ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተወካዮች ታንዛኒያ ዛንዚባር ውስጥ ንግግር መጀመራቸውን መግለጡን ሮይተርስ ዘግቧል። ኢጋድ የኹለቱ ወገኖች ንግግር ወደ ፖለቲካዊ ስምምነት ያመራል ብሎ እንደሚጠብቅ ቃል አቀባዩ ኑር መሐመድ ሼክ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ሮይተርስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክሎ የሚደራደረውን ቡድን የሚመሩት የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን መኾናቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምቻለሁ ብሏል።

2፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን ጋር ትናንት በመቀሌ ጽሕፈት ቤታቸው መወያየታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። ጌታቸው ውይይቱ ፌደራል መንግሥትና ሕወሃት በደረሱበት ሰላም ስምምነት አፈጻጸም፣ በፍትህ፣ በወንጀል ተጠያቂነት፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት መሰናክሎችና አሜሪካ በመልሶ ግንባታ መስክ ሊኖራት በሚገባ ሚና ዙሪያ እንደነበር ገልጸዋል።

3፤ ከ1 ሺህ 600 ቱርካዊያን ዜጎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በአውቶብስ መጓጓዛቸውን ከዲፕሎማቲክ ምንጮች መስማቱን የቱርኩ አናዶሉ ዜና ወኪል ዘግቧል። ቱርካዊያኑ ወደ መተማ እና ከዚያም ወደ ጎንደር የተጓጓዙት በአውቶብስ መኾኑን የጠቀሰው ዘገባው፣ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን መጓጓዛቸውን መስማቱን ጠቅሷል። ቱርካዊያኑን በኢትዮጵያ በኩል ከሱዳን የማስወጣቱ ተልዕኮ እንደቀጠለ መኾኑንም ዘገባው አመልክቷል።

4፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ትናንት ምሽት በሱዳን ግጭት ዙሪያ ምክክር አካሂዷል። የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ የሱዳኑ ግጭት ወደ ጎረቤት አገራት ሊዛመት እንደሚችል እና የሱዳን ጎሳዎችና የታጠቁ ኃይሎችም በግጭቱ ጎራ ለይተው ለመዋጋት እየተዘጋጁ መኾኑን በማስጠንቀቅ፣ ሁለቱ የአገሪቱ ተፋላሚ ወገኖች ባስቸኳይ ውጊያውን እንዲያቆሙ ጥሪ አድርገዋል። በተመድ የሱዳን ተወካይ አል ሐሪት ሞሐመድም በግጭቱ ላይ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ የሰጡ ሲኾን፣ ሱዳን በግጭቱ ዙሪያ የውጫ ጣልቃ ገብነቶችን እንደማትቀበል ገልጸዋል።

5፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አውሮፓ ኅብረት በጣለው ማዕቀብ ሳቢያ ከወራት በፊት ላትቪያ ውስጥ የተወረሰ የሩሲያ ማዳበሪያን ወደ ኬንያ እየተጓጓዝ መኾኑን ሮይተርስ ዘግቧል። ወደ ኬንያ መጓጓዝ የጀመረው የመጀመሪያው ዙር 200 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ መኾኑን ዘገባው አመልክቷል። ላትቪያ ማዳበሪያውን ወደ ኬንያ የላከችው፣ የምትወርሰውን የሩሲያ ማዳበሪያ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በኢኮኖሚያቸው ላይ ጉዳት ላደረሰባቸው አገራት በነጻ እንዲከፋፈል በወሰነችው መሠረት እንደኾነ ተገልጧል።

6፤ የደቡብ አፍሪካ ገዥ ፓርቲ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግሬስ ደቡብ አፍሪካ ከዓለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንድትወጣ መወሰኑን ፕሬዝዳንት ሴሪል ራማፎዛ መናገራቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ዓለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በርካታ የዩክሬን ሕጻናትን በግዳጅ ወደ ሩሲያ ወስደዋል በማለት ባለፈው መጋቢት የእስር ማዘዣ እንዳወጣባቸው ይታወሳል። የፍርድ ቤቱ መመስረቻ ስምምነት ፈራሚ የኾነችው ደቡብ አፍሪካ በመጭው ነሐሴ በምታዘጋጀው የብሪክስ አገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን የሚገኙ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካም የፍርድ መመስረቻ ስምምነት ፈራሚ እንደመኾኗ ፕሬዝዳንት ፑቲንን አስራ ለፍርድ ቤቱ የማስረከብ ግዴታ አለባት።

7፤ የሱማሌላንድ ራስ ገዝ መንግሥት ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ማስገባቱን የሱማሌላንድ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የራስ ገዟ መንግሥት ለጸጥታው ምክር ቤት ያስገባው አቤቱታ፣ በላስ አኖድ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት የአልሸባብ፣ የፑንትላንድና የሱማሊያ ፌደራል መንግሥት ታጣቂዎች በቀጥታ ተሳታፊ ናቸው በማለት የሚከስ መኾኑን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። የሱማሌላንድ መንግሥት ሦስቱ አካላት ወረራና ጥቃት ፈጽመውብኛል በማለት ሲከስ መክረሙ ይታወሳል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja