Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ዛሬ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ታንዛኒያ መግባታቸውን የመንግሥት ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ደመቀ ዛሬ በታንዛኒያ የወደብ ከተማ ዛንዚባር ከአገሪቷ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሳሉሁ ጋር በኹለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደተወያዩ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርን ጠቅሰው ዘግበዋል። ደመቀ ከፕሬዝዳንት ሳሉሁ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የታንዛኒያ መንግሥት በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር ሲሞክሩ ታንዛኒያ ላይ በቁጥጥር ስር ለዋሉ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ተገቢውን አያያዝ እንዲያደርግላቸው ፕሬዝዳንቷን ጠይቀዋል ተብሏል። ደመቀ ዛሬ ታንዛኒያ የገቡት፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥታቸው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በታንዛኒያ አስተናጋጅነት ነገ ማክሰኞ የሰላም ድርድር እንደሚጀምር በገለጡ ማግስት ነው። ደመቀ ከታንዛኒያ ቀጥሎ በኮሞሮስ፣ ቡሩንዲ እና ኡጋንዳ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገልጧል።

2፤ የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት ዛሬ ባዋለው ችሎት በ"ኡትዮ ንቃት" የዩትዩብ ጣቢያ ባለቤት መስከረም አበራ ላይ ተጨማሪ 10 የምርመራ ቀናት መፍቀዱን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። መርማሪ ፖሊስ ባለፉት 13 ቀናት ከተጠርጣሪዋ እጅ ያዝኳቸው ባላቸው የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ላይ ምርመራ እንዲደረግለት ለሚመለከተው አካል ልኮ የምርመራ ውጤቱን መቀበሉን፣ የተጠርጣሪዋን የገንዘብ ዝውውር ለማወቅ ለባንክ ደብዳቤ መጻፉን፣ ከመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ማስረጃ ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቡንና ሌሎች ቀሪ የምርመራ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ፖሊስ መስከረምን ከሁለት ሳምንት በፊት በቁጥጥር ስር ያዋላት፣ "ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት" ወንጀል ጠርጥሬያታለሁ በማለት ነበር።

3፤ የኬንያ መንግሥት ኬንያዊያን ዜጎችን ከሱዳን ማስወጣት መጀመሩን ደይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል። ኬንያ ዜጎቿን ማስወጣት የጀመረችው፣ በኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ግብጽና ሳዑዲ ዓረቢያ በኩል በየብስ እና በአውሮፕላን መኾኑን የጠቀሰው ዘገባው፣ 400 ያህል ኬንያዊያን ከሱዳን ለመውጣት መመዝገባቸውን አመልክቷል። 29 ኬንያዊያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ደሞ ከሱዳን ገዳሪፍ በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውንና በየብስ ወደ ጎንደር መጓጓዛቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

4፤ ከሱዳኑ ግጭት የሸሹ 27 የሱማሊያ ዜጎች ባለፈው ቅዳሜ በመተማ ከተማ በከል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ድንበር አቋርጠው ኢትዮጵያ ከገቡት መካከል፣ የቀድሞው የቢቢሲ ዘጋቢ አብዲሰላም ሄረሪ እንደሚገኝበት ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ሱማሊያዊያኑ መተማ የገቡት፣ ከካርቱም በገዳሪፍ በኩል ወደ ጠረፋማዋ ጋላባት በአውቶብስ በመጓዝ እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል። ከሱዳኑ ውጊያ ለሚሸሹ የውጭ አገር ዜጎች፣ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚወስደው መስመር እስካሁን ደኅንነቱ አስተማማኝ እንደኾነ ይነገራል።

5፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ1133 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ1956 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ2567 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ5418 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ3352 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ5219 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja