Get Mystery Box with random crypto!

ማንን ትቼ ማንን ልጥራ?! በደፈናው ሁላችሁንም እንኳን አደረሳችሁ ማለት አይከብደኝም። ግን እስቲ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ማንን ትቼ ማንን ልጥራ?! በደፈናው ሁላችሁንም እንኳን አደረሳችሁ ማለት አይከብደኝም። ግን እስቲ የተወሰኑትን ልሞክር። ከሁሉም በላይ የሮመዳንን ጾም አጠናቀህ፡ የዛሬዋ ዕለት ላይ ለመድረስ አምላክ ሳይፈቅድልህ አራት ቀናት ሲቀሩት በሞት መልዕክተኞች ከጎናችን የተነጠከው ውዱ ወንድሜ ተገኔ ኑርዬ ሁሌም አስታውስሃለሁ። ሀዋሳ አረብ ሰፈር ያላችሁ፡ የእምነት መስመር ሳታሰምሩ ላሳደጋችሁን፡ አብራችሁኝም ላደጋችሁ፡ ከሸምሳን ሱቅ እስከ ጎንደር ጠጅ ቤት፡ በዚህም ከቶታል እስከ ሞቢል ድረስ ላላችሁ የሙስሊም አባቶቼ እናቶቼ፡ ወንድምና እህቶቼ እንኳን ለጾም ፍቺው አደረሳችሁ። ኢድ ሙባረክ ብዬአችኋለሁ።የሸምሳን ልጆች፡ የሀሽም ልጆች፡ የአብደላ ልጆች፡ የሽኩሬ ልጆች፡ የጋሽ ከማል ልጆች፡ የጋሽ ሳህሉ ልጆች፡ አረ እንደምን ናችሁ? እንኳን አደረሳችሁ!

የካምፓስ ጓደኛዬ፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የስፖርት ጋዜጠኛ የነበርከው ወንድሜ ኢዘዲን ከድር ምነው አሜሪካ ስትመጣ ድምጽህ ጠፋብኝ? እንኳን አደረሰህ። የጋዜጠኝነት ሜንተሬ፡ ብዙ ነገሮችን የተማርኩብህ፡ እንደቅርብ ዘመድ የቀረብኩህ፡ አስተናጋጄ የዶቼቬሌው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ ባለቤትህ ሙና፡ ልጆችህ ሳምራና አዩብ ሁላችሁንም እንኳን አደረሳችሁ ብዬአለሁ። ለጊዜው ስምህን ዘነጋሁት። ከ20ዓመት በፊት በብሩንዲ የሰላም ማስከበር ዘመቻ በአስተርጓሚነት አብረኸኝ የነበርከው፥ የወባ ትንኝ እንዳይነድፈኝ አጎበርህን አውሰከኝ አንተ ግን ለታመምከው የትግራዩ ወዳጄ (ኑረዲን መሰለኝ ስምህ) ተግባርህንና መስዋዕትነትህን ዝንታለሜን የማስታውሰው መሆኔን ስገልጽልህ ካለህበት እንኳን አደረሰህ በማለት ነው። የኤርትራው በረሀ ጓዶቼ ኑርጀባ ሁሴን፡ የአየር ሃይሉ ሄሊኮፕተር አብራሪ ጠይብ ቃዲ፥ ኢድ ሙባረክ ብዬአችኋለሁ።

የምስራቁ በር ግድግዳ አጥርና ማገር ለሆንከው ውድ ውደጄ ሙስጠፌ መሀመድ፡ ለረጅም ዓመታት የትግል አጋሮቼ ሆናችሁ አሁን ድረስ በወዳጅነት ለዘለቃችሁት ጀማል ዲርዬና አብዱላሂ ሁሴን ቀናነታችሁ፡ ደግነታችሁ ሳይደበዝዝ ሁሌም አብሮአችሁ እንዲኖር እመኛለሁ። እንኳን አደረሳችሁ። የአብኑ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ውዱ ወንድሜ ጣሂር መሀመድ አንተንም በተለየ ሁኔታ እንኳን አደረሰህ ልልህ እጅጉን ወደድኩኝ። ወዲህ ወደአሜሪካ ስምጣ ብዙ ናችሁና ሁላችሁንም እንኳን ለዚህ ለተቀደሰ ቀን አደረሳችሁ እላለሁ። በፖለቲካ ምክንያት የተኳረፍነው ግን ደግሞ ብዙ ደግ ጊዚያትን አብረን ያሳለፍነው ወዳጄ ሳዲቅ አህመድ ከእነቤተሰቦችህ እንኳን አደረሰህ ስል መልካም ምኞቴን አቀርባለሁ። የአባይ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ኢትዮጵያዊ ወኔ ሰንቀህ እየሞገትክ ላለኸው ኡስታዝ ጀማል ረሽድ የእንኳን አደረሰህ መልዕክቴ ካለህበት ይድረስህ። የኢትዮ ቲዩብ ባልደረባና የቅርብ ወዳጄ ዩሱፍ ኢብራሂም አንተንም ከነቤተሰቦችህ መልካም በዓል እንዲሆንህ እመኛለሁ። እዚህ አጠገቤ አንድ ህንጻ ተጋርተን ለምንኖረው፡ ከሀዋሳ ጀምሮ ወዳጅነታችን ለዘለቀው አብደላና ቤተሰቦችህ እንኳን አደረሳችሁ ስል መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።

ስማችሁን ያልጠቀስኳችሁ ግን ደግሞ ልዩ ስፍራ በውስጤ ያላችሁ ሙስሊም ወዳጆቼ በሙሉ እንኳን ለኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ በሚል ጠቅልዬ መልካም ምኞቴ እንዲደርሳችሁ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በየትኛውም የዓለም ጥግ የምትገኙ፡ የዛሬዋ ዕለት የሰላም የፍቅር የደስታ ይሁንላችሁ ዘንድ እመኛለሁ። ክፉ አይንካችሁ። የኢትዮጵያ አድባር በያላችሁበት ይከተላችሁ። ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን። መልካም በዓል። ኢድ ሙባረክ! መልዕክቴ ከደረሳቸው #ሼር እንደምታደርጉልኝ ተስፋ አደርጋለው

@emsmereja

#mesaymekonnen