Get Mystery Box with random crypto!

ማክሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች 1፤ የተሃድሶ ኮሚሽ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ማክሰኞ ምሽት! ሚያዝያ 10/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች

1፤ የተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ትጥቅ የሚፈቱ የቀድሞ ተዋጊዎችንና ታጣቂዎችን የመመዝገብና ወደ ማዕከሎች የማስገባት ሥራ በቀጣዩ ሰኔ እንደሚጀምር ማስታወቃቸውን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል። ኮሚሽኑ የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ ፈትተው እንደጨረሱ ዋናውን ሥራውን እንደሚጀምር የገለጡት ኮሚሽነሩ፣ ኮሚሽኑ ተልዕኮውን ለመወጣት የኹለት ዓመት ዕቅድ አዘጋጅቷል ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል። ከ250 ሺህ እስከ 300 ሺህ የሚገመቱ የቀድሞ ተዋጊዎችንና ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም 550 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ኮሚሽነር ተሾመ ተናግረዋል ተብሏል።

2፤ አምነስቲ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአማራ ክልል በቅርቡ ከተቀሰቀሰው ሁከት ጋር በተያያዘ የታሠሩ ሰባት የመገናኛ ብዙኀን ሠራተኞችን ባስቸኳይ ከእስር እንዲለቁ አዲስ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። አምነስቲ፣ ባለሥልጣናቱ ባንዲት አንስት ጋዜጠኛ ላይ ተፈጸመ የተባለውን አካላዊ ጥቃትም እንዲያጣሩ ጠይቋል። መንግሥት "የኹሉንም ዜጎች ሃሳብን የመግለጽና ሰላማዊ ተቃውሞ የማድረግ መብት" እንዲያከብርም አምነስቲ ጥሪ አድርጓል። ድርጅቱ፣ በአማራ ክልል በቅርቡ የተደረጉ የተኩስ ልውውጦችና ሁለት ረድኤት ሠራተኞች በክልሉ ውስጥ መገደላቸውም እንዳሳሰበው ገልጧል።

3፤ የሱዳን ጦር ሠራዊትና ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል የ24 ሰዓት ተኩስ አቁም ለማድረግ በተናጥል ፍቃደኛነታቸውን መግለጣቸውን የዓረብ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የ24 ሰዓት ተኩስ አቁም እንዲያውጁ ጥሪ የቀረበላቸው፣ ቁስለኞችን ለማሸሽና ችግር ላይ ላሉ ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ እንዲቻል ነው። የ24 ተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ መኾኑን ቀድሞ ያሳወቀው፣ የጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ነበር። ኾኖም ተኩስ አቁሙ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚኾን ዘገባዎቹ አልገለጡም። የሱዳን ሐኪሞች ማኅበር፣ በግጭቱ እስከዛሬው ዕለት ድረስ 144 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ማለቱን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።

4፤ የተለያዩ አገራት ሱዳን የሚገኙ ዜጎቻቸው ደኅንነት እንዳሳሰባቸው በመግለጽ ላይ ናቸው። ኬንያ ግጭቱ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ከተባባሰ 30 ሺህ ዜጎቿን ከአገሪቱ የሚያስወጣ ግብረ ኃይል ማቋቋሟን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ግብረ ኃይሉ እስከዚያው ለኬንያዊያኑ የአስቸኳይ ዕርዳታ አቅርቦትን እንደሚያስተባብር የገለጡት ዘገባዎቹ፣ እስካሁን ባለው መረጃ በግጭቱ የተገደለ ኬንያዊ እንደሌለ ጠቅሰዋል። ባሁኑ ወቅት የሱዳን የአየር ክልል ዝግ ሲሆን፣ የካርቱም አውሮፕላን ማረፊያም የግጭት ቀጠና ኾኗል። በተመሳሳይ፣ የኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደዔታ ምስጋኑ አረጋ በኢትዮጵያ ከሱዳን አምባሳደር ጋር ትናንት ባደረጉት ውይይት፣ በአገሪቱ ስለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ደኅንነት እንዳነሱላቸው ሚንስቴሩ ገልጧል። አራተኛ ቀኑን በያዘው ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 እንዳለፈ መረጃዎች ያመለክታሉ።

5፤ የተመድ ረዳት ዋና ጸሃፊ አሚና ሞሐመድ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ "ጨካኝ" እና "እምነት የማልጥልባቸው ናቸው" በማለት ለተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ መናገራቸው ኬንያን እንዳስከፋ ሮይተርስ አንድ የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባለሥልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል። አሚና ይህን መናገራቸው ይፋ የኾነው፣ ሰሞኑን ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ካፈተለኩት ሚስጢራዊ የስለላ መረጃዎች ነው። ባለሥልጣኑ፣ አፈትልኮ የወጣው መረጃ ሩቶን ከቀጠናዊና ዓለማቀፋዊ ሥራቸው አያደናቅፋቸውም ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የተመድ ዋና ጸሃፊ ቃል አቀባይ ስቲፋኒ ዱጃሪች፣ የአሚናን አስተያየት "ከአውዱ ውጭ የተወሰደና ተዛብቶ የቀረበ" በማለት ተችተውታል ተብሏል። በተመድ የኬንያ ቋሚ መልዕክተኛ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ለማግኘት ጉተሬዝንና አሚናን አነጋግሬያለሁ ማለታቸውን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ0576 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ1388 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ0924 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ3742 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ብር ከ3174 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ5037 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja
ለማስታወቂያ ስራና ለመረጃ ጥቆማዎች @infoetrobot ይህን ይጠቀሙ