Get Mystery Box with random crypto!

ዓርብ ምሽት! ሚያዝያ 6/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ መንግሥ | Zemedkun Bekele (ዘመዴ)

ዓርብ ምሽት! ሚያዝያ 6/2015 ዓ.ም የEMS Mereja ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለማቀፉ ገንዘብ ድርጅት ቢያንስ 2 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር ከድርጅቱ ጋር ንግግር ላይ እንደኾነ ከምንጮች ሰምቻለሁ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል። ኢትዮጵያ በድርጅቱ ውስጥ ካላት ድርሻ ቢያንስ 500 ፐርሰንት ያህሉን ለመበደር መጠየቋን የጠቀሰው ዘገባው፣ ድርጅቱም የአገሪቱን ብድር የመበደር አቅም ገና እያጠናና ከመንግሥት ልዑካን ቡድን ጋር ዋሽንግተን ውስጥ ድርድር ላይ መኾኑን አመልክቷል። ድርጅቱ በደረሰበት ግምገማ፣ ኢትዮጵያ እስከ ቀጣዮቹ አራት ዓመታት በአማካይ የ6 ቢሊዮን ዶላር ክፍተት ይገጥማታል የሚል ስጋት መኖሩን ዜና ምንጩ ጨምሮ ጠቅሷል።

2፤ የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ማምሻውን አዲስ አበባ መግባታቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። ሜሎኒ ቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ ዐቢይ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ሜሎኒ፣ ጣሊያን ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ሰብዓዊና የልማት ድጋፍ ማጠናከር በምትችልባቸው ኹኔታዎችና በቀጠናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

3፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ መግባታቸውን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በትዊተር ገጹ አስታውቋል። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ በኢትዮጵያ የኹለት ቀናት የሥራ ቆይታ እንደሚኖራቸው ሚንስቴሩ የገለጠ ሲሆን፣ የጉብኝታቸው ዓላማ ምን እንደኾነ ግን አላብራራም። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ፕሬዝዳንቱን በጽሕፈት ቤታቸው መቀበላቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል። ለፕሬዝዳንት ሞሐመድ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ያደረጉላቸው የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ እንደኾኑ ተገልጧል።

4፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር "ያለምንም የሕግ አግባብ የታሠሩ ጋዜጠኞች" ባስቸኳይ እንዲፈቱ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የመንግሥት ጸጥታ አካላት ጋዜጠኞች ሥራቸውን በነጻነት እንዳይሠሩ እያሸማቀቋቸውና እንግልት እያደረሱባቸው መኾኑን ማኅበሩ ገልጧል። ማኅበሩ፣ የሥራ አሥፈጻሚ አባሉና የ"አራት ኪሎ ሜዲያ" ዩትዩብ ጣቢያ ባለቤትና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውን ጨምሮ ስድስት ጋዜጠኞች በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ በመግለጫው አውስቷል።

5፤ ቦይንግ ኩባንያ ደንበኞች ያዘዟቸውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ባቀደው ጊዜ ለማስረከብ እንዳልቻለ አስታውቋል። ትዕዛዞቹ የዘገዩት፣ በአውሮፕላኑ የኋላኛው ክፍል ላይ እንዲገጠሙ ሌሎች አምራች ኩባንያዎች ያመረቷቸው መገጣጠሚያዎች ተፈላጊውን ደረጃ ባለመሟላታቸው እንደኾነ ኩባንያው ገልጧል። ችግሩ አጣዳፊ የበረራ ደኅንነት ስጋት እንደማይደቅን የገለጠው ኩባንያው፣ በረራ ላይ ያሉ ማክስ አውሮፕላኖች በረራቸውን መቀጠል ይችላሉ ብሏል። የችግሩ ሰለባ የኾኑት፣ በመገጣጠም ሂደት ላይ ያሉና ተጠናቀው የተቀመጡ "ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው" አውሮፕላኖች መኾናቸውንም ኩባንያው ጠቅሷል።ባንያው ተጨማሪ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖችን እንዲያመርትላቸው ትዕዛዝ ሰጥተው ከሚጠባበቁት አየር መንገዶች መካከል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይገኝበታል።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ0117 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ0919 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ1360 ሳንቲም እና መሸጫው 65 ብር ከ4187 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ9106 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ0888 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። አንድ የቻይና ዩዋን ደሞ በ7 ብር ከ0980 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ7 ብር ከ2400 ሳንቲም እንደተሸጠ ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩን


ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

                                   @emsmereja