2022-02-25 21:23:38
መስቀል እና ማማተብ
ዛሬ ደሞ ከአቡነ ሽኖዳ" አንፃራዊ ትምህርተ መለኮት "መፅሀፉቸው ላይ ተነስተን እንማማራለን ።ጌታችን በአገልግሎቱ ወቅት /ከመሰቀሉ በፊት / ለመስቀል ታላቅ ትኩረት ሰጥቷል ። ይህንንም ሲገልፅ "መስቀሉንም የማይዝ በኀላዬም የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም ።/ማቴ10:38/ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ ። (ማር 834)
መስቀል የመላዕክት እና የሀዋሪያት የአገልግሎታቸው መሰረት ነው ። የጌታችንን መነሳት ለሴቶቹ ያበሰረው መልአክ " እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለውና " / ማቴ 28:5/ጌታ የተነሳ ቢሆንም መልአኩ "የተሰቀለው" ብሎ ጠራው ።ቅዱስ ጵጥሮስም አይሁድን ሲሰብክ "እንግዲህ እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን.. /ሀዋ ስራ 2:36/ ። መስቀል የሀዋሪያት ክብራቸው ነው ። ለዚ ነው ጳውሎስ "ከጌታችን ከኢየሱስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከኔ ይራቅ "(ገላ6:14)ያለው
በመስቀል አምሳያ ስናማትብ የተሰቀለው ገንዘቦች መሆናችንን እንገልፃለን ። በማማተብ ፣ መስቀልን በአንገታችን በማሰር ፣ በጌጣጌጦቻችን በመቅረፅ ፣ በእምነት ቦታዎቻችን ላይ ከፍ አድርገን በመስቀል ለእኛ ሲል የተሰቀለው መሆናችንን እንገልፃለን ።እኛ በቃላችን ሳንናገር ሰዎች እኛን በማየታቸው ብቻ ስለ እኛ እምነት የተሰበኩ ይሆናሉ ።ስናማትብ "በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሃዱ አምላክ " እንላለን እንጂ ዝም ብለን አናማትብም
ስለዚህ ባማተብን ቁጥር እስከ ዘለዓለም አንድ አምላክ በሆነ በቅድስት ስላሴ ማመናችንን እንገልፃለን ። ስናማትብ በስጋዌና በተደረገልን ካሳ ማመናችንን እንመሰክራለን ። ስናማትብ እጃችንን ከላይ ወደ ታች ከግራ ወደ ቀኝ በመውሰድ እናማትባለን ። በዚህም እግዚአብሔር ከሰማያት መውረዱንና ሰዎችን ከግራ ወደቀኝ ፡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ማሻገሩን እናስታውሳለን ።ሰይጣን ስለሚፈራው እናማትባለን ። ከአዳም ጀምሮ የተደረገው የሰይጣን ትግል በመስቀሉ ከንቱ ሆነ እግዚአብሔር ወልድ በደሙ ዋጋውን ከፍሎ የሰዎችን ኃጢያት አስተሰረየ
ለሚያምኑትና ለሚታዘዙት ሁሉ ህይወትን ሰጠ ። ስለዚህም ሰይጣን መስቀል ባየ ቁጥር በመስቀል የተደረገውን ታላቁን መዋረዱን ፣ መሸነፉንና ያጣውን ምርኮ በማስታወስ ይሸሻል ።በማማተብ ቡራኬ እንቀበላለን ። በመስቀሉ የአዲስ ህይወት በረከትና የአካሉ ክፍሎች የመሆን በረከትን ሰጠን ። ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ ኪዳን ፀጋዎች የተገኙት ከመስቀል ነው
ካህናትም ለመባረክ መስቀልን የሚጠቀሙት ቡራኬው ከእኛ ሳይሆን ከጌታ መስቀል ነው ለማለት ነው ። ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ወትረ ጊዜ ወበኩሉ ሰዓት አሜን
592 views.........., 18:23