Get Mystery Box with random crypto!

ዘወረደ ( የዐቢይ ጾም አንደኛ ሳምንት ) ዘወረደ ትርጕሙ ‹ከሰማየ ሰማያት የወረደ› ማለት ነ | መግቦተ እግዚአብሔር

ዘወረደ

( የዐቢይ ጾም አንደኛ ሳምንት )

ዘወረደ ትርጕሙ ‹ከሰማየ ሰማያት የወረደ› ማለት ነው፡፡ ከሰማየ ሰማያት የወረደውን፣ ከድንግል ማርያም የተወለደውን በጥንት ስሙ ወልድ፣ ቃል በኋላ ስሙ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አማኑኤል የተባለውን ሰው የኾነውን አምላክ ለማመስገን ርደቱን (ከሰማየ ሰማያት መውረዱን) ለመዘከር የሚጾም ጾም ነው፡፡ ጌታችን ጾመ ከማለት አስቀድሞ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም መወለዱን መናገር አስፈላጊ ነውና የመጀመሪያው ሳምንት ‹ዘወረደ› ተብሏል፡፡ ‹‹አንተ በሰማይ ወአንተ በምድር ወአንተ በባሕር ወአንተ በየብስ፤ አንተ በሰማይ አለህ፤ በምድር በባሕርም በየብስም አለህ፤››የተባለውን በሰማይ በምድር ምሉዕ የኾነውን አምላክ ‹ወረደ፤ መጣ› ብሎ መናገር ‹ሰው ኾነ› ማለት ነው

ሰው ኾኖ መገለጡን ለማስረዳት ነው እንጂ መውረድ መውጣት የሚባሉ ቃላት በዅሉ ምሉዕ ለኾነው መለኮት አይስማሙትም፡፡ ቃላቱ ሰውኛ አነጋገርን የሚያመለክቱ ናቸውና፡፡ መተርጕማን አበው ‹‹‹ዘወረደ› ማለት ‹ሰው የኾነ› ማለት ነው›› ብለው ይተረጕማሉ፡፡ አምላካችን ሰው ከኾነ በኋላ ‹መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ› የሚሉ ቃላት ይስማሙታል፡፡ ምልዓቱን ሳይለቅ በሰው አካል ተወስኖ ታይቷልና፡፡ ስለዚህ ‹ወረደ› እግዚአብሔር ሰው ኾኖ መገለጡን፤ ‹ዐረገ› ደግሞ የሰውነቱን ሥራ መፈጸሙን ያሳያል፡፡ ዐረገ ስንልም ቀድሞ በሰማይ የለም ለማለት አይደለም፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ በዓለሙ ዅሉ ምሉዕ ነውና፡፡

ጾሙን ሐዋርያት፣ ስያሜውንና የምስጋናውን ሥርዓት ቅዱስ ያሬድ አዘጋጅተዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ነቢያትን በንባብ፤ ሐዋርያትን በስብከት፤ ሊቃውንትን በትርጓሜ፤ መላእክትን በዜማ ይመስላቸዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የመላእክትን የምስጋና ሥርዓት ወደ ምድር አምጥቷል፡፡ የነቢያትን ትንቢት፣ የሐዋርያትን ትምህርት በሚገባ ተርጒሞ፣ አብራርቶ፣ አመሥጥሮ አዘጋጅቶታል

ሐዋርያት ጾሙን ጾመው የጾም ሕግ ደንግገዋል፤ ቅዱስ ያሬድም ለጾሙ ስያሜ ሰጥቶ ምስጋና ከነሥርዓቱ አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡ቤተ ክርስቲያናችንም የመጀመሪያው የዐቢይ ጾም ሳምንትን (ዘወረደን) ስያሜ እንደ ቅዱስ ያሬድ ከሐዋርያት ተቀብላ ታስተምራለች፡፡ ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹ጾመ ሕርቃል› እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ614 ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለት ነበር፡፡ ያላወቁ ‹ጾመ ሕርቃል› ብለው አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል፡፡ ጥንቱን የቅዱሳን ሐዋርያት መኾኑን ያወቁ ምእመናን ግን ዅልጊዜ በየዓመቱ ይጾሙት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ 15 ላይ ይገኛል