ሐምሌ 19 እንኳን ለመልአኩ ለቅዱስ ገብርኤል አመታዊ በዓል አደረሳችሁ:: ☞ በዚህ ዕለት ቅዱስ ገብርኤል ሕፃኑ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት እየሉጣን ከእሳት አድኗቸዋል:: ✞ ቅዱስ ቂርቆስ ሀገሩ ሮም/ጣሊያን/ አንጌቤን ሲሆን አባቱ ቆዝሞስ እናቱ ደግሞ ኢየሉጣ ትባላለች፡፡ በዘመነ ሰማዕታት በጨካኙና በአረመኔው በዲዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግሰት በ ፫፻፫ /303/ ዓ.ም አብያተክርስቲያናት ይውደሙ አብያተ ጣዖታት ይስፋፉ የሚል አዋጅ ታወጀ፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ ቅድስት ኢየሉጣም የ ፫ /3/ ዓመት ሕጻን ልጇን ቂርቆስን ይዛ ወደ ኢቆንዩን የምትባል ከተማ ሸሸች፡፡ ☞ መስፍነ ብሔሩ እለእስክንድሮስ ክርሰቶስን ካጂ ለጣዖት ስገጂ ቢላት "ዓይን እያለው ለማያይ ጆሮ እያለው ለማይሰማ በቃልህ አዘህ በእጅህ ሰርተህ ላቆምከው ምስል አልሰግድም" አለች:: አይሆንም ካልሽማ በሰይፍ ትቀጫለሽ ብሎ አስፈራራት እስኪ ይህን ሕፃን ጠይቀው አለችው አንተ ሕፃን ወርቅ እሰጥሀለሁ ለዚህ ጣዖት ስገድ አለው:: መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና "ራሳቸውን ማዳን ለማይችሉ ርኩሳን ጣዖታትህ አልሰግድም" አለው:: ተበሳጭቶም የብረት ጋን ውስጥ ውኃ አስፈላ የፍላቱም ድምፅ እንደ ክረምት ነጎድጓድ 24ምዕራፍ ድረስ ይሰማ ነበር:: ሊከቷቸው ሲወስዷቸው እየሉጣ ልቧ በፍርሀት ታወከ ሕፃኑ ቂርቆስም እናቴ ሆይ አትፍሪ አናንያን አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ እኛንስ ያድነን የለምን ? እያለ ልብሷን እየጎተተ ከእሳቱ ቀረቡ ወደ ጋን ውስጥም ከተቷቸው:: ✞ ያን ጊዜ ጌታ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ በበትረ መስቀሉ ውኃውን አቀዝቅዞ አውጥቷቸዋል::በወጡም ጊዜ ልብሳቸው ሳይበሰብስ ሰውነታቸው ሳይሸበሸብ ቢያዩ ከአሕዛብ ብዙዋቹ አምነው ሰማዕትነት ተቀብለዋል:: ✞የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ፈጥኖ ተራዳኢነት የቅዱስ ቂርቆስና የቅድስት እየሉጣ ረድኤት በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን:: 1.3K views19:55