Get Mystery Box with random crypto!

ከመስፍን አማን ትህነግ መጠነሰፊ የሆነ የጦርነት ዝግጅቱን አጠናቆ ዳግም የወረራ ጥቃት ምልክቶ | Zehabesha

ከመስፍን አማን

ትህነግ መጠነሰፊ የሆነ የጦርነት ዝግጅቱን አጠናቆ ዳግም የወረራ ጥቃት ምልክቶች በግልጽ እየታየ ይገኛል። በዚህ የወረራ ስጋት ደመና ባጠላበት ሁኔታ፣ባለፈው ዓመት የጦርነቱ ቀጥተኛ ሰለባ በሆነው የአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው መጠነሰፊ የአፈና ዘመቻ የሚያስከትለው አደጋ ከወዲሁ የታሰበበት አይመስልም። ከምንም ነገር ባላይ ወስጣዊ አንድነት አስፈላጊ በሆነበት፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ በማህበረሰቡ ዘንድ ተሰሚነት ያላችውን ጋዜጠኞች፣ፖለቲከኞች፣የጦር መሪዎች እና የፋኖ አባላት ላይ እየተወሰደ ያለው እመቃ ከትህነግ የጦርነት ዝግጅት አንጻር አማራን በመከፋፈል እና በማዳከም ለጥቃት አሳልፎ የመስጠት እርምጃ ነው። ከቅርብ ወራት ወዲህ እየተሰሙ ያሉ ቁርጥራጭ መረጃዎችን ስናገናኝ የምናገኘው ምስል በክህደት እና ሽፍጥ ቀለም የተቀባ ሆኖ እናገኘዋለን።

በፌደራሉ መንግስት እና አማጺው ትህነግ መሃከል ከወራት በፊት ድርድር መካሄድ ተጀመረ ከተባለ ወዲህ የሚስተዋሉ ነገሮችን አንድ በአንድ ስንመለከት የአብይ አህመድ መንግስት ለውጪ ጫና እጅ ስለመስጠቱ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያስችለናል።በዚህም የትህነግን አንዳንድ ፍላጎቶች የመፈጽም እርምጃዎች መጀመራቸውን ማረጋገጥ ይቻላል። ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ የመንግስትም እና ትህነግ መግለጫዎች ይዘት መለሳለስ መኖሩን ሲያመላክት፣ በትህነግ በኩል የሚሰጡ መግለጫዎች የፌደራሉን መንግስት ተወት ያደረጉ፣ የቃላት ጦርነቱን በኤርትራ መንግስት እና የአማራ ተስፋፊዎች ባሏቸው ሃይላት ላይ ማተኮሩ በራሱ የሚገልፀው ነገር አለ።

ይህ ጦርነት ከተጀመረ ለመጀመሪያ ግዜ ከአሜሪካን መንግስት ለመንግስት እየተቸረ ያለው ሙገሳ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ብዙ የሚጠቁመው ነገር አለ። ይህ ብቻ አይደለም የዓለም ባንክ ለመልሶ ግንባታ በሚል ብድር መስጠት መጀመሩ እንዲሁ ከሰማይ የወረደ የገንዘብ ሲሳይ ሶለመሆኑ ከብዙ ምንጮች ማረጋገጥ ተችሏል። ከሱዳን ወደ መቀሌ ከራዳር እይታ ውጭ ከሚደረጉ ምስጢራዊ በረራዎች፣ በአንድ የምስራቅ አፍሪካ ሃገር ተደረገ እስከተባለው የጀነራሎቹ ግንኙነት ውስጥ ለውስጥ እየተብላላ ስላለው ፖለቲካዊ ገቢር አስረጂ ነው።

በትህነግ መንደር እየታየ ያለው ኤርትራን አብዝቶ የመተንኮስ ዳርዳርታ፣ የፌደራሉ መንግስት ለሰላም እንቅፋት ናቸው ባላቸው አክራሪ የአማራ ልሂቃን ላይ እየወሰደ ያለው አፈና እየተካሄደ ያለው አደገኛ ቁማር አካል ነው። ለሰላም የሚከፈል ዋጋ እስከሆነ የሰብዓዊ ቀውስን የሚያስቀር ስምምነት ላይ መደረሱ ማንም ተቃወሞ የለውም። ችግሩ ሰላምን በሌሎች ኪሳራ ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ሽር ጉድ ላይ ነው።

ኤርትራ ውስጥ የስርዓት ለውጥ በማምጣት፣ ወልቃይትን አሳልፎ በመስጠት፣ የአማራ ሃይልን በማዳከም የሚገኝ ሰላም ዘላቂ እንደማይሆን በአስተማማኝነት መናገር ይቻላል። እንዲ ባለው የማምታታት ፖለቲካ ስልጣንን ማስቀጠል አይደለም ፣ ሃገርን እስከ መበታተን የሚያደርስ አደጋ ለመፍጠሩ በዚህ መንገድ የሄዱ መሪዎችን ታሪክ ብቻ መለስ ብሎ መመልከቱ በቂ ነው።