Get Mystery Box with random crypto!

'እኛ ሕገወጦችን እንጂ ፋኖዎችን የመንካት ዓላማ የለንም! ከክልሉ ውጭ ተይዘው ጠፉ የሚባሉት ትክክ | Zehabesha

"እኛ ሕገወጦችን እንጂ ፋኖዎችን የመንካት ዓላማ የለንም! ከክልሉ ውጭ ተይዘው ጠፉ የሚባሉት ትክክል አይደለም፤ መስተካከል አለበት!" ዶ/ር ይልቃል ከፋለ
~~~
የአማራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ወያኔና የወያኔ ፈረሶች ናቸው። በግንባር አካባቢ የወያኔ ፈረስ ኾነው የሚያገለግሉትን ኃይል አዘጋጅተን እየተፋለምን ነው።

የአማራ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት በዝርዝር አጥንቶ ክልሉን ለማዳከም የሚሠሩ ጠላቶች መኖራቸውን አረጋግጧል። የውስጥ ጠላቶችን ለመዋጋት የውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን።

የኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ የመግባት እንቅስቃሴ ችግር ውስጥ እየወደቀ ነው። ውስጡን እያዳከመና እየከፋፈለ የሚገኝ ኃይል እንዳለም አረጋግጠናል።

ሕገወጥ ተኩስ በአጭር ጊዜ ካልተቀጨ በስተቀር ለኅብረተሰቡ ስጋት ይኾናል። የልማት እንቅስቃሴዎች በሰላማዊ ሁኔታ እንዳይከናወኑ እየተደረገ መሆኑን ተገንዝበናል። የኮንትሮባንድ ንግድም ፈታኝ እየሆነ መጥቷል። አንዳንዱ ሕገ ወጥ ንግድ በጦር መሳሪያ ጭምር እየታገዘ የሚተገበር ነው።

በታጠቁ ኃይሎች ምክንያት የመንግሥት አቅጣጫዎች በታለመላቸው ጊዜ እንዳይተገበሩ የሚያደርጉ እየሆኑ ነው። ሃይማኖትን ሰበብ በማድረግ እርስ በርስ በማጋደል ክልሉ የፀጥታ ስጋት ውስጥ እንዲቆይ የሚያደርጉ አመላካች ሁኔታዎች አሉ። ይህም ለውጭ ጠላት ተገላጭ እንዲሆን የሚያደርግ ነው።

በየደረጃው ያለው አመራር እየተሳተፈበት የሕግ ማስከበር ሥራው እየተከናወነ ነው። እየተወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራ ጅማሮው አበረታች ነው። ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን በማስለቀቅ እና ሕጋዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው። የሕግ ማስከበር ሥራው አስፈላጊና ስኬታማ በሆነ መንገድ እየተከናወነ ነው። በቀጣይም ሕግ የማስከበር ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። የአማራን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እንሠራለን ነው።

እርስ በርሱ የተከፋፈለ ሕዝብ ለጠላት ተጋላጭ ነው። ሕግ የማስከበሩ ሥራ የመንግሥትን ኃላፊነት የሚያረጋግጥ እና ሕዝብን የመታደግ ነው። ወጣቶች ከመንግሥት ጋር በመሆን ለሕግ ማስከበሩ ሥራ እንዲተባበሩ ጥሪ አቀርባለሁ።

ተጠርጣሪዎችን እየያዙና በውይይት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ ይሰራል። ያለ አግባብ የተያዙ ሰዎች ካሉ አጣሪ ኮሚቴው እያጣራ አፋጣኝ መፍትሔ ይሰጣል። ጥፋተኞች ግን በሕግ አግባብ ሊቀጡ ይገባል።

ከክልሉ ውጭ ተይዘው ጠፉ የሚባሉት ትክክል አይደለም መስተካከል አለበትም። የተፈጠረ ስህተት ካለም መታረም አለበት ነው ያሉት። የክልሉ መንግሥት ሕግ ለማስከበርና ሙሉ አቅም አለው። ሕገወጦችንና ሥርዐት አልበኞችን የመቆጣጠር አቅም አለው። እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር ሥራ ኅብረተሰቡ ከአሉባልታ ተቆጥቦ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርበታል።

የጦር ነጋሪት እየጎሰመ ያለውን ጠላት በመከላከያ ሠራዊት፣ በልዩ ኃይል፣ በሚሊሻና በፋኖ ሕዝባችን ደጀን አድርገን እንመክታለን። ሕዝቡ እንዲከፋፈል ዘመቻ ተከፍቷል። ሕዝቡ ተከፋፍሎ እንዲዳከም እየተደረገ ነው፤ ሕዝቡ ይሄን መገንዘብ አለበት።

መንግሥት እያደረገ ያለው ሕገወጦችንና ሥርዐት አልበኞችን መቆጣጠር እንጂ ሌላ ዓላማ የለውምም። ሕገ ወጦች ተጠያቂ መኾን አለባቸው፤ ያላጠፋ ነጻ ይሆናሉ። በሕገወጦች ላይ ያለ ምኅረት እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይህ የመንግሥት ተግባር ነው።።

የአማራ ክልል መንግሥት የጦር መሳሪያ አያስፈታም፤ የክልሉ መንግሥት ፋኖን የሚያዋክብ አይደለም፣ ፋኖዎችን አመሰግነናል፣ ሸልመናል። ነገር ግን በፋኖ ስም የሚነግዱ አሉ፤ በነጻነት እና የአማራ የክብር ስም በሆነው ፋኖ እየተንጠላጠሉ ሕገ ወጥ ተግባር ለመፈጸም የሚፈልጉ አሉ። ሕግ ስናስከብር ፋኖ ነው የሚባለው ውሸት ነው። እኛ ሕገወጦችን እንጂ ፋኖዎችን የመንካት ዓላማ የለንምም። ዓላማችን የዜጎችን ሰላምና አንድነት ጠብቀን የጋራ ጠላታችን በጋራ መጠበቅ ነው።

የመንግሥትን ሥራ የሚገዳደር ኃይል ሊኖር አይችልምም። ሕዝቡ ከፀጥታ መዋቅር ጎን እንዲሰለፍም ጥሪ አቅርበዋል። ሰላምና ደኅንነታችን በራሳችን እንገባ፣ ይህን የማድረግ አቅም አለን። መሳሪያ ማርኮ የያዘ ሰው መሣሪያውን አይነጠቅም። ነገር ግን ማስመዝገብ አለበት።

መሳሪያውን ለችግር ጊዜ እንዲጠቀምበት የሚያደርግ ስልጠና እንሰጣለን። በዚህ አጋጣሚ መሳሪያ ያላቸው እንዲያስመዝግቡ ጥሪ እናቀርባለን።

በተጀመረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጥሩ ለውጥ ተገኝቷል። በቅርቡ ከተኩስ ድምፅ ነጻ የሆኑ ከተሞችን እንፈጥራለን። ከሕግ ማስከበሩ በተቃራኒ የቆሙት ሁሉ ለአማራ ሕዝብ የማያስቡ ናቸው።

ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ የኾነ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት መሥራት ይገበዋል። የተያዙ ግለሰቦችን በአግባቡ እንይዛለንም። ሰላምን ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ እንሠራለን፣ ከአቅም በላይ ሲሆን እርምጃ እንወስዳለንም። ኅብረተሰቡ ሕገወጦችን እያወጣ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
.
ዶ/ር ይልቃል ከፋለ
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር