Get Mystery Box with random crypto!

ሕወሓት የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በመቃወም ቅሬታውን ለአፍሪካ ኅብረት አስገባ | ዘ-ሐበሻ የዕለቱ ዜና - Zehabesha News

ሕወሓት የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በመቃወም ቅሬታውን ለአፍሪካ ኅብረት አስገባ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሕጋዊ ሰውነት ጥያቄ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም፣ ቅሬታውን ለአፍሪካ ኅብረት ማስገባቱን ሊቀመንበሩ ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ተናገሩ።

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በትግራይ ለሚገኙ የክልሉ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ከመንግሥት ጋር ተደራድሮ የፈረመው ሕወሓት እንደሆነና ስምምነቱን የመተግበር ኃላፊነትም ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻ የሚተው እንዳልሆነ ገልጸዋል።

‹‹የሁሉም ነገር መነሻ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ነው። የስምምነቱ ፈራሚ ደግሞ ሕወሓት ነው። በመሆኑም ሕወሓት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፤›› ብለዋል።

‹‹የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሁሉንም የሚያፈርስ ነው። የስምምነቱ ትግበራንም የሚያስር ነው›› ያሉት ደብረፂዮን (ዶ/ር)፣ ስለሆነም የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በመቃወም ለፌዴራል መንግሥትና ለአፍሪካ ኅብረት ቅሬታ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

የሕወሓት ቀዳሚ ተግባር የጊዜያዊ አስተዳደሩን ዓላማዎች ማሳካት መሆኑን የተናግሩት ደብረፂዮን (ዶ/ር)፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት፣ በስምምነቱ ላይ በተቀመጡት አንቀጾች መሠረት የሚተገበር እንጂ ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻ የሚተው እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በሰጡት በዚሁ መግለጫ፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በትግራይና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻሉንና ተቀራርቦ መሥራት መጀመሩን ተናግረዋል።

በሰላም ስምምነቱ መሠረትም በሕወሓት ላይ የተጣለው የአሸባሪነት ፍረጃ፣ በፌዴራል መንግሥት መነሳቱን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረቱን፣ የፌዴራል መንግሥት አቋርጦት የነበረውን በጀት በተወሰነ ደረጃ መልቀቅ መጀመሩን፣ በዚህም ባለፉት ወራቶች የትግራይ ሕዝብ ችግሮችን ማቅለል እንደተቻለ ተናግረዋል።

ነገር ግን በፕሪቶሪያው ስምምነት ውስጥ ያልተፈጸሙ ትልልቅ ጉዳዮች፣ ለአብነትም የኤርትራ ጦርና የአማራ ክልል ታጣቂዎች አሁንም ድረስ በኃይል ከያዟቸው የትግራይ ግዛቶች አልወጡም ብለዋል።

በዚህም ምክንያት የተፈናቀሉ የትግራይ ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው መመለስ እንዳልተቻለና ይህ ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚሻ አሳስበዋል።

ደብሪፂዮን መግለጫ በሰጡ በማግስቱ ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን በትግራይ በርካታ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ሰላማዊ ሠልፎች የተካሄዱ ሲሆን፣ በተካሄዱት ሠልፎችም በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ እንዲሁም የኤርትራና የአማራ ክልል ተዋጊዎች ከትግራይ ክልል ለቀው እንዲወጡና የፕሪቶሪያው ስምምነት፣ በስምምነቱ መሠረት ይፈጸም የሚሉ ጥያቄዎች ተስተጋብተዋል።

ሕወሓት ወደ ትጥቅ ፖለቲካ በመግባቱ ምክንያት በምርጫ አዋጁ ቁጥር 1162 መሠረት ከፖለቲካ ፓርቲነት እንደተሰረዘ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የገለጸ ሲሆን፣ ውሳኔው ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትም ሆነ ከሽብርተኝነት ፍረጃው ጋር እንደማይገናኝ አሳውቋል። ሕወሓትን ከተሰረዘ በኋላ ሕጋዊ ሰውነት የሚያገኝበት በሕግ የተቀመጠ አሠራር ባለመኖሩ ጥያቄውን ለመቀበል እንደተቸገረና ያለው ምርጫ እንደ አዲስ ምዝገባ ጥያቄ ማቅረብ ነው ሲል ቦርዱ ማሳወቁ ይታወሳል።