Get Mystery Box with random crypto!

አንዳንድ ሰው... ዳንኤል ክብረት በጻፈው 'ከእቴጌ ዕሌኒ እስከ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ' መጽሐፍ ዙ | ዳንኤል ገብረማርያም

አንዳንድ ሰው...
ዳንኤል ክብረት በጻፈው "ከእቴጌ ዕሌኒ እስከ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ" መጽሐፍ ዙሪያ ከአንድ ሰው ጋር እየተወያየን ነበር። እናም መጽሐፉ ከሌሎች መጻሕፍት ተቀነጫጭቦ ለገንዘብ ማግኛ ብቻ የተሰነደ ሳይሆን በብዙ ድካም ከብዙ ማስረጃዎች (ተጨባጭ የመረጃ ምንጮች) ጋር የታተመ መሆኑን ተስማምተን በአንድ ጉዳይ ላይ የነበረን ሐሳብ ግን የተለያየ ሆነ። ይኸውም "ግራኝ አሕመድ ወራሪ ነው ወይስ አይደለም" የሚለው ሐሳብ ላይ ብዙ ተነጋግረንም መግባባት አልቻልንም። ወዳጄ የዳንኤል ክብረትን (በዚሁ መጽሐፍ ላይ የተቀመጠ) ሐሳብ መነሻ አድርጎ "ግራኝ አሕመድ ወራሪ ሊባል አይገባውም" ብሎ ሲሞግተኝ እኔ ደግሞ ራሱ ዳንኤል ክብረት አስቀድሞ ባሳተማቸው መጻሕፍትና ሌሎች የታሪክ ማጣቀሻዎችን ዋቢ አድርጌ ሰውየው ወራሪ ስለመሆኑ ሞገትሁ። በመጨረሻም ሞጋቹ ወዳጄ ጸሐፊው ዳንኤል ክብረት በቀደምት መጻሕፍቶቹ ማስረጃ ጠቅሶ "ግራኝ አሕመድ ወራሪ ነው" ብሎ ያረጋገጠውን መረጃ አሁን ለምን ለመለወጥ ፈለገ? የሚለው ላይ ማብራሪያ ሲሰጠኝ እንዲህ አለኝ፦ "ዳንኤል ዛሬ ይህንን ያለው (የግራኝን ወራሪነት የካደው ወይም ወራሪ አይደለም ማለቱ) ያለምክንያት አይደለም። ይልቁንም ግራኝ አሕመድን ወራሪ ልንለው አይገባም ማለቱ ለቤተክርስቲያንና ለክርስቲያኖች በማሰብ ነው" አለኝ። አስከተልሁና "እንዴት?" ስል ጠየቅሁት። ወዳጄም ቀጠለና "አየህ! በዚህ ወቅት ግራኝን ወራሪ ከማለት ይልቅ ወራሪ አይደለም ማለቱ ለቤተክርስቲያን የተሻለ ይጠቅማታል። ይኸውም አሸባሪ ሙስሊሞች ግራኝን ስለሚወዱትና እንደአርኣያ ስለሚመለከቱት ወራሪ አይደለም ስንላቸው ለቤተክርስቲያን ያላቸው ጥላቻ ይቀንሳል፣ በዚህም በየቦታው ቤተክርስቲያን ማቃጠላቸውን፣ ክርስቲያኖችን መግደላቸውንና ማፈናቀላቸውን ያቆማሉ" ሲል ሊያስረዳኝ ሞከረ። እኔም ወዳጄ ባቀረበው አመክንዮ አዝኜ ሐሳቡንም እንደማይቀይር ተረድቼ ሙግቴን አቆምሁ። አንዳንድ ሰው የተራቀቀ እየመሰለው ከእውነቱ እጅጉን ይሸሻል። እንደው ሌላው ቢቀር በውኑ የቤተክርስቲያን ጠላቶች "ግራኝ ወራሪ አይደለም" በሚል ቃል ከጥፋት የሚመለሱ ናቸውን? አይደሉም። እንግዲህ እንዲህ የሞገተኝ ሰው ዛሬ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ የሚገኝ፣ ነገ ደግሞ አስተዳደራዊ መዋቅሯ ውስጥ ሊገባ የሚችል (እየገባ ያለ) ሰው ነው።

በእርግጥ የወዳጄ ሐሳብ በጉዳዩ ላይ ከመራቀቅ ሳይሆን ክግላዊ ጥቅም ጋር የተገናኜ ነበር። (እንደአስፈላጊነቱ ለወደፊት በዝርዝር እመለስበታለሁ።) ሰው ለግል ጥቅሙ ሲል እውነትን ደፍጥጦ ከሐሰት ጋር ሲያብር ግን እጅግ ያሳዝናል። በተለይም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በማይሆን አመክንዮ ቤተክርስቲያንን ሲጎዱ ማየት የሚያሳምም ነው። እንደዚህ ዓይነት የጥቅም ሰዎች ለቤተክርስቲያን ከሚያስገኙት ይልቅ ከቤተክርስቲያን የሚያገኙት ይበልጣል። እነዚህ ከደጇ እስካልሸሹ ድረስ የቤተክርስቲያን ስደት ውጫዊ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ መሠረቱ እንደጸና ይቀጥላል። ስለሆነም ወደ ውስጥም እንመልከት!