Get Mystery Box with random crypto!

+++‹‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም›› ሉቃ 6፡37+++ ብዙ ጊዜ ምንም ዓይነት የጥፋተኝነት ስሜ | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

+++‹‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም›› ሉቃ 6፡37+++

ብዙ ጊዜ ምንም ዓይነት የጥፋተኝነት ስሜት ሳይሰማን ከምንሠራቸው ኃጢአቶች መካከል አንዱ ‹‹በሌሎች ላይ መፍረድ›› ነው፡፡ ደግሞ ነገሩን ከባድ የሚያደርገው የምንፈርድባቸው የወንድሞቻችንን ውድቀት በዓይናችን ማየታችን በጆሯችን መስማታችን ነው፡፡ ያዩትን አይተው፣ የሰሙትን ሰምተው ሲጨርሱ ወዲያው አለመፍረድ እንደ ተራራ የረጋ ትልቅ ሰብዕናን ይፈልጋል፡፡ ትሑት የሆነ ሰው የሌሎች ሰዎችን ድክመት ለማየት የሚገለጥ ዓይን የለውም፡፡ ዘወትር ራሱን እየመረመረ ድክመቶቹን በመቁጠር ላይ ይጠመዳል፡፡ ዓይኖቹም እንደ አሸዋ በበዛው በገዛ ኃጢአቱ ላይ ብቻ ናቸው፡፡ ደግሞ ወደ ሌላው ከተመለከቱ ሊያመሰግኑ እና ሊራሩ እንጂ ሊንቁና ሊፈርዱ አይደለም፡፡

በወንድሞች ላይ መፍረድ የእግዚአብሔር የሆነውን የጌትነቱን ንብረት እንደ መስረቅ፣ በክርስቶስም የፍርድ ዙፋን ላይ ራስን እንደማስቀመጥ ይቆጠራል፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ድፍረት፣ ከዚህ የሚበልጥ ኃጢአትስ ከየት ይገኛል? አበው ‹ሌሎች ላይ መፍረድ› የትዕቢት ታማኝ ልጅ ሲሆን፣ መጋቢና አሳዳጊውም እርሱው (ትዕቢት) እንደ ሆነ ይናገራሉ፡፡ ራስን መውደድ እና በራስ አስተዋይነት ላይ መደገፍ ሌላው ላይ ጨክኖ ከመፍረድ እንደሚያደርስም ያስተምራሉ፡፡ በርግጥ በሌሎች መፍረድ የሚወድ ሰው ‹‹ክፉ ሲደረግ ተመልክቼ ማለፍ አልችልም!›› እያለ ለከሳሽነቱ ምክንያት ይደረድር ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ በሰዎች ላይ የመፍረድ ኃጢአት ምንጩ የሌሎች ደካማ ምግባር ሳይሆን የተመልካቹ (የፈራጁ) የልብ ክፋት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የልብ ቅንነቱ ቢኖርማ በተሳሳተ ወንድሙ ፊት ቆሞ ወይ የራሱን ድክመት እያሰበ የሚያለቅስ፣ አልያም ደግሞ ለወደቀው ወንድሙ እየራራ የሚመክርና የሚጸልይ ይሆን ነበር፡፡

በሌሎች መፍረድና አቃቂር ማውጣት የለመደ ሰው ዓለሙ ሁሉ በእርሱ ፊት ሞኝ ሆኖ ይታየዋል፡፡ ሰው ሁሉ አስተዋይነት በጠፋበት ሰፊ ጎዳና ሲርመሰመስ፣ እርሱ ግን ከፍ ካለው የብስለት ሰገነት ላይ እንደ ቆመ ስለሚሰማው፣ ቁልቁል እያየ የሚሰጠው እርማትና የትዝብት እይታው አይጣል ነው፡፡ ፈራጅ ‹እኔ ተሳስቼ ይሆን?› የሚል ትሑት ሕሊና የለውም፡፡ ልክ በአገጩ ላይ ያለው ሪዝ (ጽሕም) ከመቆሸሹ የተነሣ በፈጠረው መጥፎ ጠረን በሄደበት ሁሉ አፍንጫው ሲረበሽ (መጥፎ ጠረን ሲሸተው) ‹ዓለሙ ሁሉ ሸቷል› እንዳለው ሰው፣ በራሱ ድክመት ምክንያት በተፈጠረበት የእይታ መንሸዋረር ሁሉን ሲተች በሁሉ ሲፈርድ ይኖራል፡፡ የሥነ ልቡና ሳይንሱም እንደሚናገረው አንዳንድ ጊዜ በራስ ውስጥ ያለ የዕውቀት እና የልምድ ክምችት እያነሰ ሲመጣ፣ በሰው ፊት ዝቅ ብሎ ላለመታየት ሲባል በሁሉን ፈራጅና ነቃፊነት መጋረጃ ራሳችንን ልንከልል እንሞክራለን። ይህም አንዱ የሰብዕና መቃወስ (personality disorder) ምልክት ነው።

ቅዱስ አንስታስዮስ ዘሲና ‹‹ማንም ላይ አለመፍረድ››ን በተመለከተ በአንድ ወቅት በገዳሙ ይኖር ስለ ነበረ ደግ መነኩሴ ታሪክ የተናገረውን አንሥተን ጽሑፋችንን እንቋጭ፡፡ ይህም መነኩሴ እርሱ በሚኖርበት ገዳም እንዳሉት ሌሎች መነኮሳት ከፍ ያለ ትጋት አልነበረውም፡፡ ታዲያ የሚሞትበት ቀን ደርሶ በአልጋው ላይ ሳለ ከሞት ፍርሐት ይልቅ በፊቱ ላይ የሚነበበው ታላቅ ደስታ ነበር፡፡ በሁኔታው የተገረሙት በዙሪያው የተቀመጡ መነኮሳትም ‹‹ወንድማችን ሆይ! ሕይወትህን በስንፍና (ትጋት ሳታበዛ) እንዳሳለፍክ እናውቃለን፡፡ አንተስ ይህን ስታውቅ በዚህ በመጨረሻው ሰዓት ስለ ምን ደስተኛ ሆንክ? ምሥጢሩን ልናውቅ አልተቻለንም›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ ያም ደግ መነኩሴ ‹‹አዎን! ክቡራን አባቶቼ! ሕይወቴን ሁሉ በስንፍና እና በእንቅልፍ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ነገር ግን አሁን በዚህች ሰዓት መላእክት መነኩሴ ከሆንኩበት ጊዜ ጀምሮ የሠራኋቸው ሥራዎች ሁሉ የተመዘገቡበትን አንድ መጽሐፍ አምጥተውልኛል፡፡ ይህንንም መጽሐፍ ስመለከት በማንም ላይ እንዳልፈረድኩ፣ ማንንም እንዳልጠላኹ፣ በማንም እንዳልተቆጣኹ ተረዳኹ፡፡ ስለዚህም ‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም› የሚለው የጌታዬ ቃል በእኔ ላይ እንደሚፈጸም ተስፋ አደረኩ፡፡ በዚህም ቅጽበት ይህችን ትንሽ ሕግ ስለፈጸምኩ ሌላው ሁሉ የዕዳ ጽሕፈቶቼ ተቀደዱልኝ›› አላቸው፡፡ ይህንንም ከተናገረ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡ መነኮሳቱም በምክሩ ተምረው የእግዚአብሔርን ሥራ እያደነቁ በምሥጋና ቀበሩት፡፡

በእውነትም ‹‹አትፍረዱ አይፈረድባችሁም›› የሚለው የመድኃኒታችን ቃል በዚህ ታሪክ ውስጥ ትክክለኛ ትርጉሙን አግኝቷል፡፡ በወንድሞች ድክመት አለመሳለቅና በውድቀታቸው አለመፍረድ ወደ ዘላለማዊው እሳት ከመጣል ያድናል፡፡

+++እግዚአብሔር በሰው ያልፈረዱ ቅዱሳን ካሉበት ገነት በቸርነቱ ያግባን!+++

ዲያቆን አቤል ካሳሁን


https://t.me/akanim1wasen2