Get Mystery Box with random crypto!

† ታላቁ ነቢይ '#ቅዱስ_ኤልያስ † ታህሳስ 1 በዓለ ልደቱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያ | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

† ታላቁ ነቢይ "#ቅዱስ_ኤልያስ †
ታህሳስ 1 በዓለ ልደቱ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች:: "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች:: እርሱ ሰማይን የለጐመ: እሳትን ያዘነመ: ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ :-

ቅዱሱ ትውልዱ ነገዱ ኢዮርብዓም ነጥሎ ከወሰዳቸው እሥራኤል ፲ሩ ነገድ ሲሆን
አባቱ "#ኢያስኑዩ" :
እናቱ ደግሞ "ቶና [ቶናህ]" ይባላሉ::

በጐ አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማሕጸነ ቶናህን ቀድሶ ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ::

#ቅዱስ_ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል:: ብርሃን የለበሱ ፬ ሰዎች [መላእክት] መጥተውም በእሳት ሰፋድል [መጐናጸፊያ] ሲጠቀልሉት ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው::

ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእሥራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል:: ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮስታራ: ቁም ነገረኛ: ንጽሕናንም የሚወድ እሥራኤላዊ ነው::

ወቅቱ [ከክርስቶስ ልደት ፱ መቶ ዓመት በፊት] ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት: እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት ነበር:: ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት [ዳጐንና ቤል] በዚያ ዘመን ወደ እሥራኤል ገብተው ነበር::

#ቅዱስ_ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ: የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር::

በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው:: እርሱም "እሺ" ብሎ ታዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ::

ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል: ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ::

በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር:: በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ :-

፩. ለድንግልና [ድንግል ነበርና]
፪. ለብሕትውና [ብቸኛ ነበርና]
፫. ለምንኩስና [ተሐራሚ ነበርና] በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ ነቢይ ይባላል::

መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን: በዘመነ ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን: በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ አልነበረም:: በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ ክፉ ባልና ሚስት በእሥራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን ጣዖት አስመለኩት::

ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሃሰት ምስክር ደሙን አፈሰሱት:: ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም: አልለውጥም::" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል::

#ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም:: የአንቺንም ደም ውሻ ይልሰዋል" አላቸው:: በዚህ ምክንያትም ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም::

በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች:: ፱ መቶው ሲታረዱ አንድ መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ እየመገበ አተረፋቸው:: በእሥራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ:: የእግዚአብሔርን ስጦታ እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል [ለበዓል] ሰገደ::

ይህን ጊዜ ግን #ቅዱስ_ኤልያስ እንዲህ አለ :- "ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል: ዘቆምኩ ቅድሜሁ: ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ በቃለ አፉየ::" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ከለከለ::

ለ፫ ዓመታት ከ፮ ወራት ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር ከመስጠት ተከለከለ::

ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ:: እርሱን ቁራ ይመግበው: ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር:: ይሔው ቢቀርበት ጸለየ:: እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው:: በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ::

ልጇ ሕጻኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት:: ቀጥሎም ፯ ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለ፫ ዓመታት ከ፮ ወራት የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል:: ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ ቀምሰዋል::

ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል ፰ መቶ ፶ ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል:: መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ ፰ መቶ ፶ ውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል::

ይሕንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ አሳደደችው:: "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ! ብቻየን ቀርቻለሁና" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ: እርሱንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው::

ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ [ሚካኤል] ቀስቅሶ ታየው:: እንጐቻ ባገልግል: ውሃ በመንቀል አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው:: በላ: ጠጣ: ተኛ:: እንደ ገና ቀስቅሶ አበላው:: በ፫ኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና እስክትጠግብ ብላ" አለው::

ኤልያስም ለ፵ ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል:: ከዚያ በሁዋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም:: እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በሁዋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ ፪ ጊዜ እሳትን አዝንሟል::

የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን "የምትሻውን ለምነኝ" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን" አለው:: ፫ ጊዜ ሊያስመልሰው ሞከረ:: ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው:: ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በሁዋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ ነጠቀው:: ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት::

ዛሬ #ቅዱስ_ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሔኖክ ጋር ያርፋል::

/ ሥንክሳር ዘታህሳስ 1 /
( ከ፩ነገ.፲፯ - ፪ነገ.፪, እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ )


የታላቁ ነቢይ የቅዱስ ኤልያስ
ረድኤት በረከት አይለየን