Get Mystery Box with random crypto!

+• ኤፍታህ •+ አያድርገውና ጆሮዎቻችን ቢደነቁሩ እና ምላሳችን ቢተሳሰር ሰዎች በሦስት መንገድ | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

+• ኤፍታህ •+

አያድርገውና ጆሮዎቻችን ቢደነቁሩ እና ምላሳችን ቢተሳሰር ሰዎች በሦስት መንገድ ምላሽ ሊሰጡን ይችላሉ:: አንዱ ወገን "እንኳን እንዲህ ሆነበት" ብሎ መዘባበቻ የሚያደርገን ነው፡፡ ሌላው ወገን ደግሞ ክፉ ባይናገርም ለመርዳት ግን አይቀርበንም:: እንዲያው ከሩቅ ሆኖ "አይይ... የእገሌ ነገር እንዲህ ሆነ በቃ?" ብሎ ከንፈር የሚመጥ ይሆናል:: ሦስተኛው ወገን ግን ከደዌያችን የምንፈወስበት ቦታ ፈጥኖ ሊወስደን ይሞክራል:: በሁሉ ነገር ሊረዳንም ዝግጁ ነው፡፡ በወንጌል እንደምናነበው፤ በሦስተኛው ወገን የሚመደቡ መልካም ሰዎች አንድ ደንቆሮ እና ዲዳ የሆነን ሰው ወደ ጌታ ይፈውሰው ዘንድ አመጡት::

እነዚህ ሰዎች ወደ ጌታችን ያመጡትን ሰው ”እኛ አምጥተነዋል፤ ሌላውን እርሱ ይወጣው” ብለው ከፊት አሰልፈው ብቻ አልተውትም:: እንዲፈወስ ጥልቅ ፍላጎት ስለነበራቸው ጌታችን "እጁንም ይጭንበት ዘንድ ለመኑት" (ማር 7:33) ተብሎ ተጽፏል፡፡ እርሱም ይህንን ተመልክቶ ከሰዎች መካከል ለይቶ ወሰደው:: በቃሉ ብቻ መፈወስ የሚችል ጌታ ቢሆንም፤ እርሱ ግን "ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና፦ ኤፍታህ፡ አለው፥ እርሱም ተከፈት፡ ማለት ነው። ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ።" (ማር 7:33-35) ይህ ሰው በእውነት እድለኛ ሰው ነበር:: መታመሙን አይተው ወደ ባለ መድኃኒቱ የሚያመጡ፣ ከዚያም አልፎ ይፈወስ ዘንድ የሚለምኑለት ወዳጆች ነበሩት:: የእኛስ ነገር እንዴት ይሆን? ቅዱስ ቃሉን ለመስማት የተሳነፉ ጆሮዎቻችንን ዓይቶ፣ ለክፋት እንጂ መልካም ለመናገር አልፈታ ያለውን አንደበታችንን ተመልክቶስ ማን መታመማችንን ይወቅልን? ታማችኋል፤ ወደ ባለ መድኃኒቱ ሂዱ ብሎ ማን ወደ ፈዋሹ ዘንድስ ያምጣን?

ጌታ ሆይ፤ እኛስ በብርቱ ታምመናል:: በጥበብህ መስማትን ይሰሙ ዘንድ ያበጀሃቸው ጆሮዎቻችን ክቡር ወንጌልህ ለመስማት ሲሆን ይደነቁራሉ፤ ለከንቱ ወሬ ሲሆን ግን ያለ እክል ይሠራሉ፡፡ ሐሜትን ለመቅዳት ወለል ብለው ይከፈታሉ፤ ተግሳጽህን ለመስማት ግን ይከረቸማሉ:: መልካምን ይናገሩ ዘንድ በጥበብ የፈጠርካቸው ምላሶቻችንም በከንቱ ልፍለፋ ሁሌም ይጠመዳሉ፤ ቅዱስ ቃልህን ለማካፈል ግን ይኮላተፋሉ:: ምላሶቻችን አንተን እንዲያመሰግኑ፣ ሰዎችንም በመልካም ቃላት እንዲያክሙ ብትፈጥርልንም፤ እኛ ግን ሰዎችን በሐሜት እያቆሰልንበት፤ በስድብም እያደማንበት እናሳዝንሃለን:: በንግግራችን አጥንት ማለምለም እንቢ ቢለን፤ ቅስም እየሰበርንበት አለን፡፡

ክቡር መድኃኔዓለም፤ ደንቆሮና ኮልታፋውን ሰው ወዳጆቹ አስበውለት ወደ አንተ አመጡት:: አንተም ጣቶችህን ወደ ጆሮዎቹ አስገባህ:: እንትፍ ብለህም ምላሱን ዳሰስክ:: በዚህም ቸርና ሰውን ወዳጅ መሆንህን አሳየኸን:: ከደጅህ የቆምነውን እኛን ከንቱዎቹን እንደ እርሱ ትፈውሰን ዘንድ ወደ አንተ መጥተናል:: እባክህ፤ ከዓለም ግርግር ለይተህ ውሰደን:: ጆሮዎቻችንን እና ምላሶቻችንንም ዳስስልንና ዝንት ዓለም አንተን እያወደስንህ የምንኖር እንሁን:: ፈዋሽ ቃላቶችህ ከንቱ የሆኑ ጆሮዎቻችንን ዘልቀው ወደ ልባችን እንዲገቡ አድርግልን፡፡ የደነደነ ልቤን አረሰረሰ፣ የተዘጉ ጆሮዎቼን ከፈተ፣ የተቆለፈ አንደበቴንም ፈታ ብለን እንዘምር::

ቸርና ሰውን ወዳጅ ሆይ፤ ለደንቆሮውና ለዲዳው ሰው "ኤፍታህ" ብለህ የተዘጉ ጆሮዎቹን ከፈትክለት፤ የምላሱንም እስራት ፈታህለት፡፡ለቃልህና ለተግሳጽህ ዝግ ሆኖ የቆየውን የእኛን ጆሮ "ኤፍታህ" ብለህ የምትከፍትልን መቼ ይሆን? ለወሬ እንጂ ለንስሃ አልፈታ ያለውን ምላሳችንን፤ ለሐሜት እንጂ ሥጋና ደምህን ለመቀበል አልከፈት ያለው አፋችንንስ "ኤፍታህ" ብለህ የምትከፍትልን መቼ ነው?

ጌታችን ሆይ፤ እኛ ልጆችህ ትፈውሰን ዘንድ አንተን ብለን መጥተናልና ተመልከተን:: እኛንም እዘንልን እና "ኤፍታህ" ብለህ መልካምን ሁሉ ለመስማት የሰነፉ ጆሮዎቻችንን ክፈትልን፤ ክፉን ሁሉ ለመናገር የፈጠነ አንደበታችንንም ለመልካም ፍታልን::

Fresenbet G.Y Adhanom


https://t.me/akanim1wasen2