Get Mystery Box with random crypto!

+++ የጀማሪ ጠባይ +++ መንፈሳዊ ሕይወትን ገና ስትጀምረው ለፍጹምነት ጥቂት የቀረህ ያህል ይ | ዘማሪ ዲ/ን ፍፁም ከበደ

+++ የጀማሪ ጠባይ +++

መንፈሳዊ ሕይወትን ገና ስትጀምረው ለፍጹምነት ጥቂት የቀረህ ያህል ይሰማሃል። አንተ ጋር ያለው ደስታ እና ሰላም ሌሎች ጋር የሌለ ይመስልሃል። በዚህች ሁከት በሞላባት ዓለም አንተ ብቻ ክርስቶስን እንዳገኘኸው ታስባለህ። የቀረው ሕዝበ አዳም እንዲሁ በከንቱ ሲርመሰመስ የሚውል ባካና ሆኖ ይታይሃል። ታዝንለታለህ፣ አይይይ ይህ ኃጢአተኛ ሕዝብ ምን ይሻለዋል? ትላለህ።

የእውነተኛ መንፈሳዊ እድገት መገለጫ ግን ይህ አይደለም። ሰው ወደ እግዚአብሔር እየቀረበ ሲመጣ ከሌላው ሰው ይልቅ የራሱ ጉድለት ይታየዋል። መንፈሳዊነት የሚገልጥልህ ሰዎችን ተመልክተህ የምትፈርድበትን ውጫዊ ዓይንህን ሳይሆን ራስህን አይተህ የምትወቅስበት የውስጥ ዓይንህን ነው። መንፈሳዊ ሕይወትህ ሲጎመራ "አይ ሰው" ሳይሆን "አይ እኔ!" ያሰኝሃል። አባ ማቴዎስም እንዲህ ይላል "ሰው የበለጠ ወደ እግዚአብሔር ሲቀርብ ይበልጥ ኃጢአተኛ መሆኑ እየታየው ይመጣል። ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን ካየ በኋላ ከንፈሮቼ የረከሱብኝና የጠፋሁ ሰው ነኝ እንዳለ።"

ከብቃት ደርሰህ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ቢታዩህ እንኳን ሁሉ እንዳንተ ስለሚመስልህ እንደ ዮሐንስ ሐጺር "ሚካኤል ይበልጣል ወይስ ገብርኤል?" እያልህ ከአጠገብህ የቆመውን ትጠይቃለህ እንጂ "አይይ አንተ እንኳን ገና አልበቃህም። ብዙ ይቀርሃል" ብለህ ወዳጅህን አታናንቅም። ይልቅ "ለእኔ ብቻ ገልጦ ለሌላው እንዲሰውር የሚያደርገው ምንም ቁም ነገር የለኝም" በማለት ከወንድምህ የተሻልህ እንዳልሆንክ በፍጹም ልብህ ታምናለህ።

ለመንፈሳዊ ሕይወት አዲስ ስትሆን ገና ጥቂት ጸልየህ፣ ጥቂት ጾመህ፣ ጥቂት መጽውተህ ሳለ ግን ሩጫህን ወደ መጨረሱ የተቃረብህ ይመስልሃል። ጉዞህን በግማሽ እርምጃ ከመጀመርህ ከፍጻሜው ላይ የደረስህ ያህል ይሰማሃል። "እኔን ምሰሉ" ማለት ያምርሃል። ነገር ግን መንፈሳዊ ሕይወት የቱንም ያህል ብትሮጥበት ሁል ጊዜ እንደ ጀማሪ የሚያደርግ ረጅም ጎዳና ነው። ሰማንያ ዓመት በገዳም ሲጋደል የነበረው አባ ሲሶይ ነፍሱ ከሥጋው ልትለይ በቀረበች ጊዜ ብዙ መነኮሳት በአልጋው ዙሪያ ከበውት ሳለ ቅዱሱ "አምላኬ ሆይ፣ እባክህ ለንስሐ የሚሆን ጥቂት ጊዜን ስጠኝ?" እያለ በልቅሶ ሲማጸን ሰሙት። በዚህ የተገረሙት መነኮሳቱ አባ ሲሶይን "አባታችን አንተ እድሜ ልክህን በንስሐ የኖርህ መምህረ ንስሐ ሆነህ ሳለ እንዴት አሁን ጥቂት የንስሐ ጊዜን ትለምናለህ?" ቢሉት፣ ቅዱሱም "ልጆቼ ይህን መንፈሳዊ ጥበብ (ንስሐን) ገና አሁን መጀመሬ ነው" አላቸው።

ጌታ ሆይ መንፈሳዊ ሕይወት እኖር ዘንድ አስጀምረኝ፤ ገና ጀማሪ ሳለሁ ደርሻለሁ ከማለትም ሰውረኝ። እንድቆም አትፍቀድልኝ፤ ወደ አንተ ሳበኝ፣ አሳድገኝ።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ሰኔ 22፣ 2014 ዓ.ም.
አዲስ አበባ


https://t.me/zdfitsumkebede
https://t.me/zdfitsumkebede