Get Mystery Box with random crypto!

++ ንጉሥ በአህያ ላይ ++ (ሽራፊ ሃሳብ ከሆሳዕና ምንባብ) 'አህያ' ስምዋ ስድብ ከሆነ የቆየች | ሊቀ መዘምራን

++ ንጉሥ በአህያ ላይ ++
(ሽራፊ ሃሳብ ከሆሳዕና ምንባብ)

"አህያ" ስምዋ ስድብ ከሆነ የቆየች እንስሳ ናት። የዚህች በዓለም ሁሉ የምትገኝ እንስሳ የሕይወት ታሪክዋ በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው። በሚበዙት ሀገራት አህያ ከባድ ሸክም ስትሸከም ትውላለች ፣ ደክሟት ለማረፍ ብትፈልግና ሸብረክ ብትል እንኳን በዱላ የሚመታት እንጂ "እስቲ አረፍ በይ" የሚላት የለም። ጀርባዋ በሸክም ብዛት የቆሰለ ፣ እግርዋ በጭነት ብዛት የተብረከረከ ፣ ዱላ ያስመረራት ፣ ዕረፍት የናፈቃት እንስሳ ናት።
ይህችን የተዋረደች እንስሳ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጠው ሰማያዊው ንጉሥ ክርስቶስ በትሕትናው ዙፋኑ አደረጋት። ዱላ በለመደችው ፣ ዕረፍት በናፈቃት በዚህች ምስኪን ላይ "ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜ ቀሊል ነው" ያለው ንጉሥ ተቀመጠባት።

ኃያላን ነገሥታት ባማረ ሠረገላ ላይ ሆነው ፣ በሠራዊት ታጅበው ፣ ነጋሪት እያስመቱ ፣ መለከት እያስነፉ ፣ ሰይፍ በታጠቁ ጦረኞች እየተፎከረላቸው ወደሚገቡባት ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በአህያ ላይ ተጭኖ ፣ በዓሣ አጥማጆች ተከብቦ ፣ በሕፃናት ዝማሬና በዘንባባ ዝንጣፊ ታጅቦ ገባ።

ፈርተውት ሳይሆን ወደውት የሚዘምሩለት ንጉሥ ፣ ልብስ ገፍፎ የሚረግጥ ሳይሆን ልብሳቸውን አውልቀው ረግጠህ እለፍ የሚሉት ንጉሥ ፣ በቅንጦት ሠረገላ የሚሣፈር ሳይሆን "በአህያ ላይ ከተቀመጥኩ ይበቃኛል" የሚል ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።

"የጽዮን ልጅ ሆይ ደስ ይበልሽ ፣ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያና በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል" የተባለላት ኢየሩሳሌም ምንኛ የታደለች ናት? "የዋህና ትሑት ንጉሥ" ያላት ሀገር ፣ ከተማይቱን እያየ የሚያለቅስላት ንጉሥ ፣ መልካምነቱን ለመሸፈን የሚፈልጉ ሰዎች ስለ እሱ አትናገሩ ቢሉ እንኳን የቢታንያ ድንጋዮች አፍ አውጥተው የሚመሰከሩለት ንጉሥ ያላት ኢየሩሳሌም ምንኛ የታደለች ናት? የታሰሩትን አስታውሶ "ያስፈልጉኛል ፣ ፈትታችሁ አምጡልኝ" የሚል ንጉሥ የነገሠባት ፣ ዘንባባ ተይዞ ስለ ሰላም የተዘመረባት ፣ "ሰላምሽ ዛሬ ነው" የተባለላት ያቺ ከተማ ምንኛ የታደለች ናት?

ወደ አህያይቱ ነገር እንመለስ ያቺን "ሸክም ያቆሰላትን ፣ ዕረፍት የናፈቃትን አህያ ክርስቶስ ፈትታችሁ አምጡልኝ ብሎ ዙፋኑ አደረጋት" የሚለው ታሪክ ለአህያ ብቻ ክብር የተሠጠበት ቀን መሆኑን የሚያሳይ ከመሰለን የዋሆች ነን። አህዮች አንብበው የማይጽናኑበት ወንጌል ላይ ይህ ክስተት የተጻፈው ለእኛ እንጂ ለምንም አይደለም።

እንደ አህያ ዕቃ ባንሸከምም ፣ ጀርባችን ባይቆስልም የልባችን ጀርባ በኃጢአት ሸክም የጎበጠ ፣ በበደል ብዛት የቆሰለብን ብዙዎች ነን። "መቼ ነው ይህንን የኃጢአት ሸክም አራግፌ ዕርፍ የምለው?" እያልን የምንሠቃይ ሞልተናል። መድኃኔ ዓለም ያኔ የላካቸውን ካህናት ዛሬም ወደ እኛ ልኮ "ፈትታችሁ አምጡልኝ" ብሎ እኛንም ቢያስፈታን ምናለ? ለነገሩ የእኛ የኃጢአት ማሠሪያ እጅግ ትብትብ ያለ ስለሆነ ካህናቱም "ከኃጢአት ማሠሪያ እግዚአብሔር ይፍታ" ሲሉ እንሰማቸዋለን።

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች
                •➢ ሼር // SHARE

@Z_TEWODROS
@Z_TEWODROS
@Z_TEWODROS

Comment @Channel_admin09