Get Mystery Box with random crypto!

ሐሙስ የምሥጢር እና የነጻነት ቀን ይህ ዕለት ብዙ ምሥጢር እና ታሪክ የተፈጸመበት ዕለት ስለሆነ | ዘ-ተዋህዶ TUBE

ሐሙስ የምሥጢር እና የነጻነት ቀን

ይህ ዕለት ብዙ ምሥጢር እና ታሪክ የተፈጸመበት ዕለት ስለሆነ በብዙ ስሞች ይጠራል ጥቂቶቹን ከምክንያታቸው ጋር እንዲህ አቅርበናቸዋል

ጸሎተ ሐሙስ:- የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ቀን ነውና ‹ጸሎተ ሐሙስ› ይባላል (ማቴ. ፳፮፥፴፮-፶፮)፡፡

ሕጽበተ ሐሙስ:- ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ዅሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና፣ የቅድስና አምላክ መኾኑን ያጠይቃል፡፡ ስለዚህም ዕለቱ ‹ሕጽበተ ሐሙስ› ይባላል፡፡ ይህን

የምሥጢር ቀን:- ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባን በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ ‹የምሥጢር ቀን› ይባላል፡፡ ይኸውም ጌታችን ኅብስቱንና ጽዋውን አንሥቶ ‹‹ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ፤ ብሉ፡፡ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ፤›› በማለት እርሱ ከእኛ፤ እኛም ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምሥጢር ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመኾኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ:- መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመኾኑ ይህ ዕለት ‹የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ› ይባላል (ሉቃ. ፳፪፥፳)፡፡ ‹ኪዳን› ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ዅሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለ ኾነ ይህ ዕለት ‹የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ› ተባለ፡፡

የነጻነት ሐሙስ:- ይህ ዕለት ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ኾኖ መኖር ማብቃቱ የተገለጠበት፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለ ኾነ ‹የነጻነት ሐሙስ› ይባላል፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፡፡ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤›› በማለት ከባርነት የወጣንበትን፤ ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመኾኑ ሊቃውንቱ ‹የነጻነት ሐሙስ› አሉት (ዮሐ. ፲፭፥፲፭)፡፡
ስለዚህ ይህን ዕለት ከኃጢአት እና ከዲያቢሎስ ባርነት በእግዚአብሔር ቸርነት ነጻ መውጣታችንን የምናስብበት ስለሆነ የተከፈለልንን ዋጋ አስበን ዛሬ ከታሠርንበት የኃጢአት ሠንሰለት በንስሐ ነጻ ሆነን ልናስበው ይገባል፡፡

•➢ ሼር // SHARE

ዘ-ተዋሕዶ TUBE
https://www.youtube.com/@z-tewahido_tube1
    𝙎𝙐𝘽𝙎𝘾𝙍𝙄𝘽𝙀 𝙉𝙊𝙒

➮ከወደዱት ያጋሩ
share & join
   𝒔𝒖𝒃𝒔𝒄𝒓𝒊𝒃𝒆  
https://t.me/+VK34SmV504JkMjdk
   𝒔𝒖𝒃𝒔𝒄𝒓𝒊𝒃𝒆