2022-07-08 03:48:14
የድኩማኑ መልዕክት
- ምዕራፍ 0 -
እንግዲህ ምን እንላለን? ማንነታችን የተገለጠ አይደለምን?
ዛፍ ላይ እንደበቀለ ዱባ፣ እንደ ጣፋጭ ቅል፣ ወደተራራ አናት እንደሚፈስ ወንዝ፣ እንደበራሪ እባብ፣ አይነት ትርጉም-አይሰጤነት ሰፍሮብናል!
ነፍሳችንና ስጋችን ምን እና ምን ናቸው? ከስሱ ልብ እና ከደንዳና ቆዳ ለምን አዛንቆ ፈጠረን? ውስጣችን በእምባ ማዕበል ሲናጥ ለምን ዐይናችን ዘለላ እምባ ማዠት ያቅተዋል?
የሚገምቱንን ያህል ጠንካራ አለመሆናችንን ከኛ ሌላ ማን ያውቃል? ድኩም የነፍስያችን ገፅስ ለማን ተገልጧል?
ለእግዜር ምኖቹ ነን? ልጆቹ? አምሳሎቹ? ወይስ አንዳች ሌላ አይነት ማንነት አለን? እኛን ከሰው መሀል መርጦ ከምን ከምን አበጀን? አንዳች የጨመረብን ልዩ አክሻፊ ውህድ ላለመኖሩ ምን ማስረጃ አለን?
ዱኩምነታችንን አምነን ተቀብለን ያለመቻሎቻችን ደንገጡሮች ሆነናል።
የምንወዳቸውን ሰዎች ጉንጭ እየሳምን መውደዳችንን ብንነግራቸው እንወድ ነበር - ግን አንችልም!
እምባ ያቀረሩ ዐይኖችን ስናይ ተጠግተን ማፅናናት ያሰኘናል - ግን አንችልም!
"አልችልም" በየማለዳው የምንደግመው ዳዊት ሆኖልናል።
በሰዎች ዐይን የማንሞላ ደቂቅ ፍጥረታት እንደሆንን ለራሳችን ነግረናል። ቀና ብሎ መራመድ ነውር ይመስለናል።
ገና ሳንሞት መቃብራችንን በቀጭን ስንጥር እየጫርን መማስ ጀምረናል። ይህስ ከቅጣቶች ሁሉ የላቀው ቅጣት አይደለምን? ትንሽ ትንሽ ሞቶችን ዕለት ዕለት እንጎነጫለን።
መክሊታችንን በጭቃ ለውሰናል። ህብስታችንን ለውሾች ሰጥተናል። ወርቃችንን በመዳብ ለውጠናል። እንደውሻ ወደትፋትን በመመለስ አዙሪት ውስጥ ወድቀናል። እንደእሪያ ጭቃ ላይ መንደባለል የሰርክ ግብራችን ነው። ለክብር ሳይሆን ለውርደት፤ ለወርቅ ሳይሆን ለመዳብ የተገባን ሰዎች ነን ብለናልና!
መወደድ አንችልበትም። ሰዎች የዋሉልን ኢምንት ውለታ ከቋጥኝ ይልቅ ትከብደናለች። 'መልካም ነገር ሁሉ ለእኛ አይገባንም' ብለን በማመን በአንድያ ራሳችን ላይ እስክንጨክን ድረስ ራሳችንን እንዲሁ ጠልተናልና!
የምናብ ዓለም ሰዎች ነን። መሆን የምንፈልገውን ተቀምተናል። የማንን ኑሮ ይሆን አሁን እየኖርን ያለነው?
ጣታችን እንጂ ምላሳችን ትብ አይደለም። አንደበታችን በአንዳች በማይታይ ልጓም ተሸብቧል። ሰላላ ድምጻችን ለማንስ ይሰማል? "ዝምታችንን ያልሰማ ቃላችንን ሊሰማ አይገባውም" በሚሉት ስንኩል ብሂል ራሳችንን ብናፅናናም ንግግራችንም ከዝምታችን እንዳይለይ ሆኖ በባዶነት ተለብጧል።
ልዝብ ነን፤ ተሰብረን እንኳን ልክ እንደ ብርጭቆ ቆዳ የምንሸረክትበት ስለት የለንም። "ተዉን!" አንልም። ከወጊያችን ጋር ተደርበን ራሳችንን እናጠቃለን።
ልበሙሉነት ይጎድለናል። We are Cowards! ማንንም አንጋፈጥም። ዐይናችን ከዐይኖች ሲገጣጠሙ በቅፅበት እንሰብራቸዋለን። አንደበታችን ከእሺታ ሌላ አታውቅም። ትናጋችን ለእምቢታ ሩቅ ናት። ይሉኝታ ይሉት ጌታ ጨቁኖ የሚገዛን ባሪያዎቹ ነን።
ምን አይነት ድብርታሞች ኖረናል?! ይህ ፍዝ ኑሯችን ሰነፍ ጸሐፊ ከቀመረው ከአንድ አሰልቺ ድንቃይ ተውኔት በምን ይለያል? ተመልካቹ ሁሉ የጀመረውን ተውኔት ሳይጨርስ እያዛጋ ይወጣል። በመጨረሻም ተዋናዩ ብቻውን ይቀራል። እሱ ግን ፀንቶ ትወናውን ይቀጥላል። ይህ ያስመሰግነዋል ወይስ ያስወቅሰዋል?
We are boring!
Aren't we?
[Yeah, the dude in the photo is me ]
451 views00:48