Get Mystery Box with random crypto!

'አካሔድህን አስተካክል” “ከአፍቃሪያችን ክርስቶስ ያገኘነው ስጦታ እንዲህ ነው ተብሎ በቃላት መ | ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

"አካሔድህን አስተካክል”

“ከአፍቃሪያችን ክርስቶስ ያገኘነው ስጦታ እንዲህ ነው ተብሎ በቃላት መግለጥ የሚቻል አይደለም፡፡ እንዴት ያልን እንደሆነ እኛ በኀጢአት እየተንፏቀቅን ባለንበት ወራት እርሱ በምሕረቱ ጐብኝቶናልና፡፡ ኀጢአት ሸክም በሆነችብን ጊዜ እርሱ በእኛ ቦታ ተገብቶ ተሸክሞልናልና፡፡ በዚህ የማይለካ ፍቅሩ ከዲያብሎስ አገዛዝ ወደ መንግሥቱ አፈለሰን /ቈላ.1፡14/፡፡ እኛው ራሳችን ርቀን እርሱ ራሱ አቀረበን፡፡ እኛ ራሳችን በድለን እርሱ ካሠልን፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ይህን ሁልጊዜ ከልቡናችን አናውጣ፡፡ የተሠጠንን ነጻ ሥጦታ አንዘንጋ፡፡ ከምን እንደወጣን አንርሳ፡፡

ሰው ሆይ! የተጠራኸው ወደ ዘለዓለም ሕይወት ነው፡፡
የተጋበዝከው ወደ ልጁ መንግሥት ነው፡፡ ታድያ አንተ
እዚህ ስለምን ታንጠራራለህ? ስለምን እዚህ ትቀመጣለህ? ስለምን እዚህ ትንፏቀቃለህ? ስለ ሥጋህ ድሎት ብዙ ዋጋን ትከፍላለህ፡፡ ታድያ ስለ ነፍስህስ ትንሽ አይገድህምን? ወደ ሕይወት ተጠርተህ ሳለ ስለምን ወደ ሞት ትሮጣለህ? ቢያስፈለግ ይህ ያገኘኸው ስጦታ ላለማቆሸሽ ብዙ መሥዋዕትነትን መክፈል በተገባኽ ነበር፡፡ ብዙ ሰይፍን መታገሥ በተገባህ ነበር፡፡ ወደ እሳት እንኳ ብትጣል ስለ ድኅነተ ነፍስህ መቋቋም ይገባህ ነበር፡፡ ወዳጄ ሆይ! እስኪ ንገረኝ! የመንግሥተ ሰማያት ዜጋ ለመሆን ተጠርተህ ሳለ ራስህን የዚህ ዓለም ዜጋ ማድረግህ ስለምንድነው? እንደምን ያለ ስንፍና እንደያዘህስ ታስተውላለህን? ይህን ዓለም የመውደደህ ምስጢር ምቾትን መሻትህ ያሳያል፡፡ በዚህ ዓለም በምቾት መኖርን የሚሻ ሰው ደግሞ ክርስቲያን መሆን፣ ክርስቲያን ተብሎ መጠራት፣ ክርስቶስን መስሎ መመላለስ ምቾት ሳይሆን እስር ቤት መስሎ ይታየዋል፡፡ ሁላችንም ወደዚሁ ቈጥ ካስገባን ሰነባብተናል፡፡ ከዚህች ዓለም ጋር የተወዳጀ ግን ምንም ክርስቲያን ቢባልም ምንም በአርባና በሰማንያ ቀኑ የሥላሴን ልጅነት ቢያገኝም ክርስቲያን ክርስቲያን መሽተቱ እየጠፋ ይሔዳል፡፡በዚኽ ዓለም ወጥመድ ተቀፍድዶ ይያዛል፡፡

ወዳጄ ሆይ! ይህን አድምጥና ፍርሐትና ረዓድ ይያዝህ!!! ምንም በቤተ መንግሥት ብትኖርም፣ ምንም በተሽቆጠቆጠ መኖርያ ቤት ብትኖርም እንደተመቸህ አድርገህ አትንገረኝ፡፡ አንተ የምትኖርበት ኑሮ ለእኔ ወኅኒ ቤት ነው፤ ያውም ሊፈርስ የተቃረበ ቤት!!! ይኽ ቤትህ ክረምት ሲመጣ ይፈርሳል፡፡ ክረምት (የመጨረሻይቱ ቀን) ስትመጣ ቤትህ ይፈርሳል፡፡ ክረምት ስላልኩህ ደግሞ “ለሁሉም ሰው ክረምት ከሆነበት እኔ ከማን እለያለሁ” ብለህ አታስብ፤ ይህቺ ቀን ለሁሉም ክረምት አትሆንምና፡፡ ዳግመኛም እግዚአብሔር ሌሊትና ቀን ብሎ ጠርቷታልና፡፡ ሌሊት የምትሆንባቸው ለኀጥአን ነው፤ ቀን የምትሆንላቸው ደግሞ ለጻድቃን ነው፡፡ እኔም ክረምት ብዬ መናገሬ ከዚህ አንጻር ነው፡፡ ሁላችንም ክረምት ሲመጣ መብረር እንችል ዘንድ በበጋው ላይ ካላደግን የገዛ እናቶቻችን እንኳ ቢሆኑ ትተዉን ይሔዳሉ እንጂ በዚያ ሰዓት እኛን መሸከም (ማዳን) አይቻላቸውም፡፡ የገዛ እናቶቻችን እንኳ በረሃብ እንሞት ዘንድ ትተዉን ይሔዳሉ፡፡ ቈጡ (ቤቱ) በላያችን ላይ ሲፈርስ እኛን መታደግ አይቻላቸውም፡፡ እግዚአብሔር ቤቱን ሲያፈርሰው፣ አሮጌው እንደ አዲስ ሲያደርገው፣ እያንዳንዱ እንዳልነበረ ሲሆን እኛን መርዳት የሚችል አንድ ስንኳ አይገኝም፡፡ የዚያን ጊዜ ጌታን በአየር ላይ መገናኘት የማይችሉቱ፣ የመንፈስ ክንፍ ተሰጥቶአቸው መብረር የማይችሉቱ ቤቱ በላያቸው ላይ ይፈርስባቸዋል፡፡ ስቃይ የስቃይም ስቃይ ይሆንባቸዋል፡፡ ስቃዩ የስቃይ ስቃይ ነው ማለቴ ከ እስከ የሚባል ስለሌለው ነው፤ ለዘለዓለም ስቃይ ስለሆነ ነው፡፡ ክረምት ብዬ መጥራቴ ስለዚሁ ነው፤ ኧረ እንደውም ከክረምት የባሰ ነው፡፡ እንዴት ያልከኝ እንደሆነ በዚሁ፡ክረምት ላይ የሚዘንበው ውኃ አይደለምና፤ እሳት እንጂ፡፡ በዚሁ ክረምት ዙርያህ ጨለማ የሚሆነው ከደመና ብዛት የተነሣ አይደለምና፤ ጽኑ ጨለማ እንጂ፡፡ የብርሃን ጭላንጭል የሌለው ጨለማ እንጂ፡፡ እዚህ የሚገቡት ሰዎች ተድላ መንግሥትን ማየት አይቻላቸውም፤ ሰማያትን ማየት አይቻላቸውም፡፡ ከመቃብር ውስጥ የባሰ ጨለማ ይውጣቸዋል እንጂ፡፡

ወዳጄ ሆይ! አሁንስ አትርድምን? ወዴት እየሔድክ እንደሆነ አታስተውልምን? ፊትህንስ ወደ ልጁ መንግሥት አታደርግምን?”… አካሔድህን አስተካክል