Get Mystery Box with random crypto!

በአንተ ሙሉ ነኝ    ወዳጆቼ አንዳንዴ ወደላይ በሃብት፣ በዝና፣ በስልጣን፣ በእውቀት የሚበልጡን | የመስቀሉ ፍቅር ✞

በአንተ ሙሉ ነኝ


   ወዳጆቼ አንዳንዴ ወደላይ በሃብት፣ በዝና፣ በስልጣን፣ በእውቀት የሚበልጡንን እያተመለከትን እንጎመጅ ይሆናል። አሁን የኔ ኑሮ' ኑሮ ይባላል? ምናለ እንደነርሱ ኖሬ በሞትኩ እያልን ባላዋቂነታችን ሕይወታችንን እንረግማለን።

   ወዳጆቼ ድህነት ቆሻሻ ነው የማትፈልጉትን እንድትወስኑ፤ የማትወዱትን እንድታደርጉ ያደርጋችኋል። ነገር ግን በድህነት ውስጥ ጤና ካላችሁ በድህነት ውስጥ ሰላም ካላችሁ ተመስገን በሉ።

    እንደ ባለጠጎቹ ለመሆን የተመኛችሁት ጤና ስላላችሁ ነው። የአንድ ቀን ጤና ብታጡ ከፈውስ በቀር የምትመኙት ገንዘብና ሀብት የለም።

    ወዳጄ ወደምትማልሉባቸው ሰዎች ቤት ገብታችሁ ብታዩ ባለጠግነት ሊሞላላቸው ያልቻለው ትልቅ ጉድለት፣ የሚያስነባቸው ችግር አለ። ሀብት አላቸው መብላት ግን አልቻሉም። በሽታውም አብሮ መጥቶ ይሄንን አትብሉ፣ ይሄንን አትቅመሱ ተብለው ጾም በሐኪም ታዞላቸዋል። የሐብታቸው መጠን በዝቶ እንቅልፍ ነስቷቸዋል። ሃብታቸው ሌባ ጠርቶባቸው ሰላም እንቅልፍ አጥተዋል። ኑሯቸው የመባነን ሆኗል።

   አንተን ደግሞ ሲያዩ የሚቀኑበት በርካታ ነገር አላቸው። ወዳጄ ያለህ ነገር በቂ መስሎ ካልታየህ ድፍን አለምን ብትጨብጥ እንኳ ሀዘንተኛ እንጂ ደስተኛ አይደለህም። አዳም ያለውን ሳይሆን የተከለከለው ላይ ትኩረት አድርጎ ነው ጣጣ ውስጥ የገባው። ሁሉ እያለው ማመስገን ሲገባው በተከለከለው ማጉረምረሙ ያለውን ደስታ ነጠቀው።

እናም ወዳጄቼ ያላችሁን ተመስገን በሉ። ባላችሁ ነገር ደስ ይበላችሁ። አንዱን ክርስቶስን አጥታችሁ ሁሉ ቢኖራችሁ ጎደሎ ናችሁ። ሁሉ ቀርቶ ክርስቶስ ቢኖራችሁ እናንተ ሙሉ ናችሁ። እርሱ ብቻውን በቂ ነው።

    ተመስገን ስለሰጠኸኝ ተመስገን ስለነሳኸኝም መንሳትህም በረከት ነውና። ተመስገን ከነሳኸኝ የሚጠቅም ከሰጠኸኝ የሚጎዳ አንዳች የለም። እግዚአብሄርን ሆይ በነገር ሁሉ አንተ ቡሩክ ነህ!!

ምስጋና ለስላሴ !