Get Mystery Box with random crypto!

እቅፍህ ዋስትናችን ነው “እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፤ የእስራኤል ን | የመስቀሉ ፍቅር ✞

እቅፍህ ዋስትናችን ነው


“እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም።” — ሶፎንያስ 3፥15


     ቃላት የማይገልፃቸውን የደስታ፣ የፍቅር ስሜቶቻችንን ከምንገልፅበት መንገድ አንዱ ማቀፍ ነው። ለአንድ ህፃን ልጅ የእናቱ እቅፍ የደህንነቱ ከተማው፣ የለቅሶ መሻሪያው፣ የሰላሙ መናኻሪያው ነው። እቅፏ ውስጥ እረፍት ይሰማዋል ሁሉን እረስቶ ይተኛል።

     ለአንድ ሰው መታቀፍ ልብን ከልብ ጋር ነፍስን ከነፍስ ጋር የማነካካት ያህል ደስታን ይሰጣል። ጌታችን ሲያቅፈን እርግማንና ቅጣትን አይመጣብንም ዲያብሎስ በእኛና በቤተሰባችን ላይ ስልጣን አይኖረውም ምክንያቱም ዋስትና በሆኑ የጌታ ክንዶች ውስጥ ታቅፈናል።

      አባካኙ ልጅ ሲመለስ አባትዬው እስካሁን የት ነበርክ ብሎ ልምጭ ይዞ አልጠበቀውም። ይልቁንም እጆቹን ዘርግቶ አቀፈው። ያ የለመደው እቅፉ ዛሬም ይሞቃል ዛሬም ያ የለመደው ደረቱ ይመቻል። በዓለም ተንገላትተን ቆሳስለን ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ ይበልህ ማን ጎርምሰህ ውጣ አለህ ብሎ ጀርባ አይሰጠንም። እጆቹን ዘርግቶ ይቀበለናል። እቅፉ ያጽናናናል፣ የደረሰብንን የነበርንበትን ደስ የማይል ሁኔታና መከራ ለመርሳት ጸጋን ይሰጠናል። በዛው መጠን የጎዱንን ያሠቃዩንን ሰዎች ይቅር የማለት ሙሉ አቅም ይሰጠናል።

      ጌታችን ኢየሱስ ትላንት ስለኔና ስለናንተ በደልና ኃጢአት እርጥብ መስቀል፣ ጥርብ እንጨት ታቅፏል፣ ብዙ ቁስሎች ብዙ ሕመሞችን መከራዎችን ታቅፏል። ዛሬ ግን እኛን ከነአቧራችን ታቅፎናል ከነስህተታችን በፈገግታ ተቀብሎናል። ትኩስ በሆነ ፍቅሩ እግሮቹ ላይ አስቀምጦናል። ይህ ፍቅር የኃጢአት አቧራችንን ያራግፍልናል የበደል ሰንኮፍን ይነቅልልናል። የጌታ ፍቅር ሰዎች ሲረግሙን እንድንወድና እንድንባርክ ያደርገናል። 

    እዚህ የፍቅር እቅፍ ውስጥ ስንገባ ይህ ፍቅር ማንም ሰው እኛን ለመወንጀል ልብ አይኖረውም።  በጣም ጥበበኛ የክርስቶስ አምባሳደር ያደርገናል።


     አቤቱ ክፉን ጋርዶ ያሻገረን እቅፍህ ነውና እናመሰግንሃለን። ስብራታችንን የጠገነልን፣ ፀፀታችንን የሻረልን፣ ስህተታችንን ያረመልን፣ መጠውለጋችንን ያለመለመልን፣ ኪሳራችንን የካሰልን ምቹው ጉያህ ነውና ተመስገን። መልካምነትህን ገፍተን፣ ቸርነትህን ንቀን፣ ፍቅርህ ኮሰኮሰን ብለን ከእቅፍህ እንዳንወጣ በግድም ያዘን። አብዝተን እንድንወድህ አይናችንን አብራልን። አሜን!!

@ymeskelu_fiker