Get Mystery Box with random crypto!

በረመዳን ምን ይጠበቅብናል? (ክፍል 1) አላህ ለኛ ካለው እዝነትና ርህራሄ የተነሳ በዚህች ዱንያ | °♡•የረሱል ኡማ°♡•

በረመዳን ምን ይጠበቅብናል? (ክፍል 1)

አላህ ለኛ ካለው እዝነትና ርህራሄ የተነሳ በዚህች ዱንያ ውስጥ ኢማን እና ተቅዋ የምንሰንቅባቸው ማረፊያዎችን አዘጋጀልን። በኛ ላይ የተንጠለጠሉ የኃጢያትና የመዘንጋት እድፎችን የምናወልቅባቸው ጊዜያትን ፈጠረልን። ነፍሳችንን ከፍ የምናደርግባቸው፣ የመዝገባችንን ስህተቶች የምናርምባቸው፣ በአዲስ መንፈስ የምንቀዝፍባቸው፣ ወኔያችን የሚጠነክርባቸው፣ የህይወትን ዐቀበት የምንወጣባቸው፣ አደጋዎቿን የምንቋቋምባቸው፣ አላህ እኛን የፈጠረበትን አላማ እንድንወጣ የምንታገዝባቸው… አንዳንድ ውድ ጊዜያትን አደረገልን።

እነዚህን ጊዜያት በቁጥር ለመገደብ የሚሞክር ሰው ከአቅሙ በላይ ይሆንበታል።

በየቀኑ የሚመላለሱት የአምስት ወቅት ሶላቶች፣ በየሳምንቱ የሚናፈቀው ጁሙዓህ፣ በየአመቱ የሚመጣው ረመዳን፣ በእድሜ አንዴ የሚያጓጓው ሐጅ… ከእነዚህ መሀል የምንጠቅሳቸው ናቸው። እነዚህ ብቻ አይደሉም። በአመት ውስጥ ተበታትነው የምናገኛቸው፣ የአላህ እዝነት የሚንሰራፋባቸውና ብዙ ትሩፋቶች የሚገኙባቸው ጊዜያት አሉ።

እድለኛ ማለት የመልካም ሥራ መዝገቡን ያስተካከለ፣ ከእነዚህ የእዝነት ጊዜያት ለመጠቀም ራሱን ያዘጋጀ ሰው ነው። አትራፊ ማለት እድሉ ሳያመልጠው እጅጌውን ሰብስቦ በሥራ የተጠመደ ነው፤ ወደ አላህ ለሚያደርገው ጉዞ የሚያስፈልገውን ስንቅ ሳይሰንቅ እነዚህ ጊዜያት ያላመለጡት። አላህ እንዲህ አለ፡-

وَتَزَوَّدُوا فَإِنَّ خَيْرَ الزَّادِ التَّقْوَىٰ ۚ وَاتَّقُونِ يَا أُولِي الْأَلْبَابِ

“ተሰነቁም፤ ከስንቅም ሁሉ በላጩ ጥንቃቄ (አላህንመፍራት) ነው። የአእምሮዎችም ባለቤቶች ሆይ! ፍሩኝ።” (አል-በቀራህ 2፤ 197)

ለሙስሊሞች ከተከወኑ እነዚህ ማረፊያዎች መሀል በየአመቱ የሚከሰተው ረመዳን አንዱ ነው። ረመዳን የቀናት ጥርቅም ነው። በረከትን፣ ምህረትንና እዝነትን ይዞ የሚመጣ ወር። ነገር ግን በአግባቡ የተቀበሉትን እና ያስተናገዱትን ብቻ አክብሮ የሚከንፍ እንግዳ ነው። አላህ በመልካም ተግባሮች መሽቀዳደሚያ ያደረገው ወር።

ረመዳን ውስጥ የሚሰሩ ትርፍ ሥራዎች (ነዋፊሎች) ሌላ ጊዜ እንደሚሠራ አንድ ግዴታ (ፈርድ) ይታሰባል። እርሱ ውስጥ የሚሠራ አንድ ግዴታ (ፈርድ) ሌላ ጊዜ ከሚሠራ ሰባ ፈርድ ጋር ይስተካከላል።

ረመዳን – “ኸይር ፈላጊ ሆይ! ፍጠን!…” የሚል መፈክር አለው። በርሱ ውስጥ ሰይጣናት ይታሰራሉ። የእሳት ደጃፎች ይዘጋሉ። አየሩ በሙሉ ምህረትን፣ እዝነትን፣ ከእሳት ነፃ መባልን… ለማግኘት ምቹ ነው። ጀነት ትጣራለች። ወደኔ ዙሩ ፈጠን ብላችሁ ኑ! እያለች ናፋቂዎቿን ትጋብዛለች። ገበያው ክፍት ነው። ውድ እቃዎችም ተዘርግተዋል። ንጉሱም ቸር ነው።

እነሆ ረመዳንን ለመጠቀም እንቸኩል። ድንገት አልፎ እንዳንደነግጥ። ለዝግጅት የሚሆነን አንድ ቁም ነገር አለ። እነዚህን ጥያቄዎች መልሰን መገኘት። ከረመዳን ምን እንጠብቃለን? የእንግዳችንን ክብርስ ምን ያህል እናውቃለን? እንግዳችንን ለማስደሰትስ ምን እናድርግ?እነዚህ ፊታችን ያሉት ገፆች እነዚህ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይሞክራሉ።

አላህ ከፍላጎታችን በላይ ያለን የሚያሟላ ጌታ ነው። ወደ ቀጥታ መንገድ የሚመራም እርሱ ነው።

#ይቀጥላል

----------
{ምንጭ ↣ ethiomuslims.net }
——————————————————————
«በብዕርህ መጣራት ባትችል በሰዎች ብዕር ተጣራ»

Join us ☞ @worldmuslims