Get Mystery Box with random crypto!

ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረግ ድርድር እንደሌለና ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ስ | YeneTube

ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረግ ድርድር እንደሌለና ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ስጋት መሆኗን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ተናገሩ

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ “ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ስጋት” መሆኗን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረግ ድርድር እንደማይኖር እና ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን ለድርድር እንደማታቀርብም ተናግረዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼህ ሞሐመድ ይህንን ያሉት የኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ ትናንት ረቡዕ ሚያዝያ 2/2016 ዓ.ም. ለአገሪቱ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር ነው።

“የኢትዮጵያ መሪዎች ወደ ቀልባቸው መመለስ አለባቸው” ያሉትን ሐሴን ሼህ፤ ግጭት እየፈጠረች ያለችው ኢትዮጵያ እንጂ ሶማሊያ እንዳልሆነች ለዓለም እየተናገሩ መሆኑን ገልጸዋል።

“እኛ የኢትዮጵያን አካል እንፈልጋለን አላልንም። ለኢትዮጵያን መንግሥት እውቅና አንሰጥም [አላልንም]፤ ከክልል መንግሥት ጋር ስምምነት እንፈጽማለንም አላልንም” ሲሉ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት እየፈጠረች አይደለም የሚለውን ሀሳባቸውን አስረድተዋል።

ሁለቱ ጎረቤት አገራት በጋራ ፍላጎቶቻቸው ላይ መሥራት ያላቸው “ብቸኛ አማራጭ” መሆኑን በንግግራቸው ላይ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ “ሉዓላዊነታችንን፣ አንድነት እና ሙሉዕነታችንን ለድርድር የሚያቀርብ የጋራ ፍላጎት ሊኖረን አይችልም” ብለዋል።

ሐሰን ሼክ፤ “ለዓለም እየተናገርን ያለነው፤ እኛ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ስጋት እንዳልሆንን ነው። እነሱ ግን ናቸው። እናም ይህ እንዲፈጠር በፍፁም አንፈቅድም” ሲሉ ከኢትዮጵያ ተጋርጦብናል ያሉትን ስጋት ገልጸዋል።

ሶማሊያ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር ልታደርግ እንደማትችል እና ሉዓላዊነቷን ለድርድር እንደማታቀርብ የተናገሩት ሐሴን ሼክ፤ “ንግግርን ወይም ድርድርን እየተቃወምን አይደለም። ነገር ግን መሬታችን እንዲወሰድ ወይም ሉዐላዊነታችን ለድርድር እንዲቀርብ አንፈቅድም” ሲሉም ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ፤ የኢትዮጵያ መሪዎች እየተከተሉት ያለው አካሄድ “እንደማይሠራላቸው” እና “ከዚህ መንገድ እንዲመለሱ እየመከሯቸው” መሆኑንም አንስተዋል።

ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ይህንን ንግግር ያደረጉት አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማቋረጥ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና ዲፕሎማቶች ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ካስተላለፈች ከቀናት በኋላ ነው። በአዲስ አበባ የሚገኙት የሶማሊያ አምባሳደርም ወደ ሞቃዲሾ እንዲመለሱ መታዘዛቸው ይታወሳል።

ሁለቱ አካላት ጥር ላይ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚነት ወደሚኖረው ስምምነት ተቀይሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ሁለቱ አካላት በተፈራረሙበት ዕለት ተገልጾ ነበር። ይሁንና የመግባቢያ ስምምነቱ ከተፈረመ አራት ወራት ቢያልፍም እስካሁን ድረስ ተፈፃሚነቱ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ በይፋ የተነገረ ነገር የለም።

Via::- ዳጉ ጆርናል
@Yenetube @Fikerassefa