Get Mystery Box with random crypto!

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፒያሳ ለሚነሱ የግል አልሚዎች “ካሳ እና ምትክ መሬት” እንደሚሰጥ | YeneTube

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፒያሳ ለሚነሱ የግል አልሚዎች “ካሳ እና ምትክ መሬት” እንደሚሰጥ አስታወቀ!

በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ ከተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ጎን በሚገኘው ቦታ ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች፤ ከስፍራው እንደሚነሱ የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አበቤ ማረጋገጫ ሰጡ። ለእነዚህ የልማት ተነሺዎች የከተማው አስተዳደር “የጋራ መኖሪያ ቤት” አሊያም “አዲስ የሚገነባ የቀበሌ ቤት” እንደ የምርጫቸው እንደሚያቀርብ፤ በአካባቢው በተዘጋጀው ፕላን መሰረት ግንባታ ለማከናወን የገንዘብ አቅም ለሌላቸው የግል አልሚዎች ደግሞ “ካሳ እና ምትክ መሬት” እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

አዳነች ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኙ “የመንገድ ኮሪደር ልማት” ስራዎችን በተመለከተ በሰጡት ገለጻ ነው። በመንግስት እና ለመንግስት ቅርበት ባላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በትላንትናው ዕለት በተላለፈው በዚህ ገለጻ፤ የኮሪደር ልማቱን የተመለከተ ጥናት ሲከናወን የቆየው ከግንቦት 2015 ጀምሮ መሆኑ ተጠቅሷል።

ይህ የመንገድ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከጸደቀ ማግስት ጀምሮ “ወደ ስራ እንዲገባ እና ልዩ ክትትል እንዲደረግለት” ውሳኔ ተላልፎ ነበር። ከንቲባ አዳነች በትላንቱ ገለጻቸው ይህንኑ አረጋግጠዋል።

“ይሄንን በምንሰራበት ሰዓት ከመንገድ ላይ የሚነሱ፣ ከመንገድ ላይ ወደ ውስጥ ጠጋ የሚሉ አጥሮች ይኖራሉ። ከተለያየ ቦታ ላይ በእርጅና አሁን ያለንበትን ዘመን የማይመጥኑ ግንባታዎች አሉ። ከከተማው መዋቅራዊ ፕላን ውጪ የተገነቡ አሉ። የተለያዩ ጥፋቶች አሉ...እርሱን ለማስተካከል ሰዎችን ከቦታቸው ልናነሳ እንችላለን” ሲሉም አዳነች ተናግረዋል።

Via Ethiopia Insider
@YeneTube @FikerAssefa