Get Mystery Box with random crypto!

ተፈረደበት * 1 ዓመት ና * 2 ሺህ ብር ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) በ 1 ዓመ | YeneTube

ተፈረደበት

* 1 ዓመት ና
* 2 ሺህ ብር

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) በ 1 ዓመት ቀላል እስራትና በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወሰነ

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ህገመንግስታዊና በህገመንግስት ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ተከሳሹ ያቀረበውን አምስት የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን ይዟል።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም ላይ ሶስት ክሶችን አቅርቦበት ነበር።

ከቀረቡበት ክሶች መካከል በኮምፒዩተር የሚፈጸም ወንጀል ድንጋጌን መተላለፍ፣ የቤተክርስቲያንና የሰዎችን ክብርና መልካም ስም ማጉደፍ እንዲሁም የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት የሚሉ ተደራራቢ ክሶች ይገኙበታል።

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም የቀረበበት ክስ እንዲሻሻል የክስ መቃወሚያውን በጽሁፍ ያቀረበ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ በኩል ክሱ ሊሻሻል የሚችልበት የህግ አግባብ እንደሌለ ተጠቅሶ መልስ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሹ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ጥያቄ የህግ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን በመጥቀስ የዕምነት ክህደት ቃሉን በመስጠቱ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማምረጃውን አቅርቧል።

የቀረበውን ማስረጃ የመረመረው ችሎቱ ተከሳሹ የቀረቡበት ሶስት ክሶች ተጠቃለው በአዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4 እና 7 መሰረት እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።

ሶስቱም ክስ በአንድ እንዲጠቃለል የታዘዘው የወንጀል ድርጊቱ በሀሳብ፣ በጊዜና በቦታ ተመሳሳይ መሆኑን በምክንያትነት ተጠቅሶ ነበር።

ተከሳሹ የመከላከያ ማስረጃ አለኝ ማለቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያቀረባቸውን የሰው መከላከያ ማስረጃዎችን ቃል አዳምጧል።

ተከሳሹ የሰው የመከላከያ ማስረጃ ያቀረበ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል ባለመቻሉ እና በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸሙ በፍርድ ቤቱ በመረጋገጡ በዛሬው ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶበታል።

ዐቃቤ ሕግ ድርጊቱ ታስቦ የተፈጸመ መሆኑን ጠቅሶ ቅጣቱ ከብዶ እንዲጣል ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ለአካባቢ ጥበቃ ያበረከተውን አስተዋጾኦ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪና የቀደመ የወንጀል ሪከርድ እንደሌለው ገልጾ ያቀረበውን የቅጣት ማቅለያ ይዞለታል።

ፍርድ ቤቱ በድርጊቱ የእርስ በእርስ ግጭት አለመፈጠሩንና ጉዳት አለመድረሱን ከግምት ውስጥ በማስገባት በዕርከን 6 መሰረት በአንድ ዓመት ቀላል እስራትና በሁለት ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ከነሃሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ጊዜ ታሳቢ እንዲያደርግ ታዟል።

Via:- ታሪክ አዱኛ
@Yenetube @Fikerassefa