Get Mystery Box with random crypto!

የወልዲያ-አላማጣ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ! በሰሜን ኢት | YeneTube

የወልዲያ-አላማጣ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ጉዳት ደርሶበት ሲጠገን የሰነበተው የወልዲያ-አላማጣ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮች የቴክኒክ ድጋፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መንግስቴ እንዳስታወቁት ዛሬ ያለዕረፍት በተሠራው የጥገና ሥራ የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና እና የተሰበሩ ኢንሱሌተሮች ቅየራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ መስመሩን መፈተሽ ተጀምሯል።

በአንድ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ የደረሰው ጉዳት በቀጣይ እንደሚጠገን የገለፁት አቶ ተስፋዬ የምሰሶው ጉዳት ግን መስመሩን ኃይል ከመስጠት የሚያግደው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮች እና የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ ውቤ፣ በጥገና ሥራው ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ከሦስት ሳምንት ያላነሰ ጊዜ የሚፈልገውን ሥራ በአንድ ሳምንት በማጠናቀቃቸው አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ በበኩላቸው የተቋሙ ሠራተኞች ለሦስተኛ ጊዜ ጉዳት የደረሰበትን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በፍጥነት በመጠገን ከህዝብ ጎን መቆማቸውን በተግባር በማሳየታቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

@YeneTube @FikerAssefa