Get Mystery Box with random crypto!

† ሞትን ስላለመፍራት ! ' ሊፈራ የሚገባውንና ልክ እንደ እሳት አእምሮ የሚያሳጣውን ኃጢአትን | የቅድስት ሥላሴ ልጆች ማህበር






ሞትን ስላለመፍራት !


" ሊፈራ የሚገባውንና ልክ እንደ እሳት አእምሮ የሚያሳጣውን ኃጢአትን ግን አንፈራም ! "

▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬


" “ ወንድሞች ሆይ ! በአእምሮ ሕፃናት አትኹኑ ፣ ለክፋት ነገር ሕፃናት ኹኑ እንጂ” ብዬ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ [፩ኛ ቆሮ.፲፬፥፳]፡፡

ኃጢአትን ሳይኾን ሞትን የምንፈራ ከኾነ ፍርሐታችን የሕፃናት ፍርሐት ነውና፡፡ ጨቅላ ሕፃናት ጭምብል ያስፈራቸዋል ፤ እሳትን ግን አይፈሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ድንገት ወደ በራ ሻማ ብንወስዳቸው ምንም ሳይፈሩ እጃቸውን ወደ ሻማውና ወደ እሳቱ ይዘረጋሉ ፤ ፈጽሞ የተናቀ ጭምብል ግን ያስፈራቸዋል። እኛን ሊስፈራን የሚገባው እሳት እነርሱን ምንም አያስፈራቸውም፡፡

እኛም ልክ እንደ እነርሱ እጅግ ሊናቅ የሚገባውን ጭምብል - ይኸውም ሞትን - እንፈራለን ፤ ሊፈራ የሚገባውንና ልክ እንደ እሳት አእምሮ የሚያሳጣውን ኃጢአትን ግን አንፈራም! እንዲህ እንድንኾን የሚያደርገንም የነገሮቹ ተፈጥሮ አስፈሪ ስለ ኾነ ሳይኾን የራሳችን ስንፍና ነው ፤ ሞት ምን እንደ ኾነ ብናስተውል ኖሮ በየትኛውም ጊዜ ባልፈራነው ነበርና፡፡

እንግዲህ እስኪ ንገረኝ ! ሞት ምንድን ነው?

ሞት ማለት ልብስ እንደ ማውለቅ ነው፡፡ ሥጋ የነፍስ ልብሷ ነውና ፤ ይህን ልብሳችንን ለጥቂት ጊዜ ካወለቅን በኋላም እጅግ ደስ በሚያሰኝ ውበት መልሰን እንለብሰዋለን፡፡ የሞት ትልቁ ነገርስ ምንድን ነው? ለተወሰነ ጊዜ መጓዝና ከተለመደው ሰዓት በላይ መተኛት ነው! ስለዚህ ሞትን የምትፈራው ከኾነ እንቅልፍንም ልትፈራው ይገባሃል!

ለሚሞቱ ሰዎች የምታዝንላቸው ከኾነ ለሚበሉና ለሚጠጡ ሰዎችም እዘንላቸው ፤ መብላት መጠጣት ባሕርያዊ እንደ ኾነ ኹሉ ሞትም እንደዚህ ነውና! ነገር ግን ባሕርያዊ የኾኑ ነገሮች አያሳዝኑህ ፤ ከክፉ ምርጫ የተነሣ የሚመጡ ነገሮች ያስለቅሱህ እንጂ፡፡

በሚሞተው ሰው አትዘን ፤ በኃጢአት በሚኖረው እንጂ!"


እውነተኛ መከራ ማለት በእግዚአብሔር ላይ ማመጽና እርሱን ደስ የማያሰኘውን ሥራ መሥራት ነው ፡፡

እስኪ ንገረኝ! ሞት ውስጥ ምን የሚያስፈራ ነገር አለ? ወደ ሰላማዊ ማረፊያና ሁከት ወደ ሌለበት ሕይወት ፈጥነህ እንድትኼድ ስላደረገህ ነውን? ምንም እንኳን ሰው እንድትሞት ሊያደርግህ ባይገባም የተፈጥሮ ሕግ ግን በቆይታ ይሰርቅሃል ፤ ነፍስህን ከሥጋህ ይለየዋል ፤ ይህ አሁን እያስፈራን ያለው ሞት አሁን ባይመጣብን እንኳን ወደፊት የማይቀር ነው።

ይህንንም የምናገረው [እንደ አሁኑ ያለ ሌላ] ስጋት ወይም የሚያሳዝን ድርጊት እንዲመጣ በመጠበቅ አይደለም - እግዚአብሔር ይህን ያርቅልኝ! ነገር ግን ይህንን የምለው ሞትን በሚፈሩ ሰዎች እጅግ ስለማፍር ነው። አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ! “ዓይን ያላየው ፣ ጆሮ ያልሰማው ፣ የሰውም ልብ ያልሰማው” በጎ በጎ ነገሮችን እየጠበቅህ እያለ በዚህ ደስታ ትጠራጠራለህን? [፩ኛ ቆሮ.፪፥፱]፡፡ ተጠራጥረህስ ቸልተኛና ሰነፍ ትኾናለህን? ሰነፍ ብቻ ሳትኾንስ ትፈራለህን? ትንቀጠቀጣለህምን?

ቅዱስ ጳውሎስ በአሁኑ ሕይወት ሲቃትትና ለሮሜ ሰዎችም ፦ “ፍጥረት ኹሉ በአንድነት ይቃትታል ፤ የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችንም እንቃትታለን” ብሎ ሲጽፍ አንተ ሞትን ፈርተህ ስትጨነቅ አታፍርምን? [ሮሜ.፰፥፳፪]፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሲናገር ሊመጡ ያሉ ነገሮችን በመናፈቁ እንጂ የአሁኑ ዓለም ነገሮችን ሲናቅፍ አይደለም፡፡

እንዲህ ማለቱ ነውና ፦ “ከዚያ ጸጋ ቀምሻለሁና እኔ ፈቅጄ ወደዚያ መኼድን አልዘገይም፡፡ የመንፈስ በኵራት አለኝ ፤ ይህንንም ለኹሉም አስተላልፋለሁ። እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጥቂያለሁ ፤ ማንም ሊናገርለት የማይቻለውንም ክብር አይቻለሁ ፤ እነዚያ አንጸባራቂ ቤቶችን ተመልክቻለሁ ፤ እዚህ ስቆይ ከምን ያህል ደስታ የራቅሁ እንደ ኾነ ተምሬያለሁ ፤ ስለዚህም እቃትታለሁ።”

እንበልና አንድ ሰው እጅግ ያማሩ የተወደዱ ቤቶችን አስጎበኘህ ፤ ግድግዳው በወርቅ ቅብ የተቀባና ኹሉነገሩ እጅግ አንጸባራቂ የኾነን ቤት አሳየህ፡፡ ይህን ካደረገ በኋላም አንዲት ደሳሳ ጎጆ ወዳለው ሰው ወሰደህ ፡ ይህን ሲያደርግ ግን በቅርብ ጊዜ አስቀድሞ ወዳሳየህ ወደ እነዚያ ቤተ መንግሥት ወደ መሰሉ ቤቶች እንደሚመልስህና ከእነርሱ አንዱም ለዘለዓለም ለአንተ እንደሚሰጥህ ቃል በመግባት ነው።

እንግዲህ ንገረኝ ! ወደዚያ ቤትህ እስክትገባ ድረስ ባሉት በእነዚህ ጥቂት ቀናት ውስጥ “መቼ በደረሰ” እያልህ አትናፍቅምን? አትቸኩልምን? ስለዚህ ስለ መንግሥተ ሰማያትና ስለ ምድር አስብና ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ኾነህ ቃትት ፤ ሞትን ፈርተህ ሳይኾን አሁን ያለውን ሕይወት እያሰብህ ቃትት !"

▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬

[ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ]