Get Mystery Box with random crypto!

የተውጋ ልብ #ክፍል 1 ...ጠዋት ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ እጆ | 👑የፍቅር_ደብዳቤዎች 💏

የተውጋ ልብ


#ክፍል 1

...ጠዋት ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ እጆቼን ወደአምላኬ ዘረጋሁና
የተለመደ ፀሎቴን ጀመርኩ። ዛሬ ግን እጅግ አምርሬ ነበር።
እንደበፊቱ መልኩ እንዲህ… አቋሙ እንዲያ… አስተሳሰቡ
እንደዚህ የሆነውን፤ የሁልጊዜ ህልሜን… ስጠኝ ብዬ ጎንበስ

ቀና አላልኩም፤ እንደ ሌላው ቀንም ተለሳልሼ አምላኬን
አለመንኩትም…ይሁንልኝ አሜንም አላልኩም።ብቻ በፀሎቴ
ውስጥ ቀወጥኩት…ስጮህ …ስመናቀር
ይታወቀኛል"…

እንዴት እንዴት …ለኔ የሚሆን የአጥንቴ ፍላጭ… የስጋዬ
ቁራጭ… የፍቅሬ ዘማሪ… የነፍሴ አጣማሪ …እንዴት አንድ
ይጠፋል?…እረ በምን ሂሳብ …በምንስ ስሌት…እረ
ተመልከተኝ… እረ እየኝ…እረረረረረ… ኡኡ… "


እንደተመናቀርኩ ነበር ከቤቴ የወጣሁት።
በቅዳሜው ምድር ጠዋት ግን ረዥሟ ሰፈራችን በሙዚቃ
ደምቃለች። ሁለት ጊዜ አግብታ ሁለት ጊዜ የፈታችው ሳቤላ
"ብቸኝነቴን ነው እኔ የማስታውሰው… አልጀመርኩም ነበር ፍቅር
ከሌላ ሰው" የሚለውን ሙዚቃ እየዘነች አለፍኳት።
ከተዋወቁ
የነገው እሁድ ሳምንት የሚሞላቸው ሳራና ግርማ "እኛን ነው
ማየት" በሚለው ሙዚቃ ግርማ በተከራየው ቤት እየቀወጡት
ነው። ባለፈው የቀበሌ ፕሮግራም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘፍኖ
መብራት ሄዶበት ያቋረጠው ካሊዶ " ስንት ያየሁብሽ ሙዚቃ
ህይወቴ…" የሚለውን ዘፈን በተመስጦ እያንጎራጎረ ፀሐይ
ይሞቃል። ሚስቱ ወልዳ እራሱ የሚያርሳት ተመስገን የአራስ ልጁን
ጨርቅ እያጠበ" ተማር ልጄ፤ ወገን ዘመድ… ሀብት የለኝ ከእጄ"
ይላል።

…የ70 ዓመቱ አዛውንት ጋሽ አንዳርጌ ጋቢያቸውን ተከናንበው
በጥንት በጠዋቷ ራድዮናቸው የቅዳሜ ጠዋት የህፃናት ፕሮግራም
እያዳመጡ ነው።" ልጅነቴ ማርና ወተቴ" ትላለች ራዲዮኗ! ጋሽ
አንዳርጌ ደግሞ "እውነት" እያሉ ራሳቸውን ይወዘውዛሉ።

ከሰፈር ወጥቼ አምፒር ጋር የአራት ኪሎ ታክሲ ተገፋፍቼ ገባሁ።
ከጋቢናው ጀርባ የመጀመሪያው መቀመጫ ላይ በመስኮቱ በኩል
ተሰየምኩ። አሻግሬ በመስኮቱ የአምፒርን ፊልም ፖስተሮች
እያየሁ ነው።መኪናው ገና ጉዞ ከመጀመሩ ረዳቱ "ሂሳብ" አለ።
ቦርሳዬ ውስጥ ምንም ዝርዝር ስላጣሁ ለረዳቱ "ይቅርታ ዲጄው
ያለኝ ይሄ ብቻ ነው" ብዬ መቶ ብር ሰጠሁት…ረዳቱ ግን
ቀወጠው፤ እንዴት ለብር ከሀምሳ መንገድ መቶ ብር ትሰጭኛለሽ
ብሎ ወረደብኝ።…

"አይደብርሽም እንዴ?" እያለ ተወያየለብኝ።

እስካሁን ያለስተዋልኩት አጠገቤ የተቀመጠው ልጅ ረዳቱን…
"አቦ እራስህ ይደብርህ እንጂ …ይቅርታ ብላህም እንዲህ
ትሆናለህ እንዴ? ያልከፈለችክ አስመሰልከው እኮ" ብሎ ብር ከሀምሳ
ሰቶ ገላገለኝ። መቶ ብሬን ሊመልስና ሊናገረኝ ወደኔ
ሲዞር ግን ነፍሴ በአፌ ልትወጣ ምንም አልቀራትም

የፈጣሪ ያለህ…የጠዋት ማታ ልመናዬ፤ የዘወትር ጭቅጭቄ፤
የህልም አለሜ፤ የምኞቴ እውነት ራሱ... አዎ ራሱ የግራ ጎኔ

አጠገቤ ተቀምጦ ስለእኔ እየተከራከረ ነው። ክፉኛ ገረመኝ።
በየት በየት አድርጎ እንዳመጣልኝ እሱ ይወቅ… የጠዋት ምሬቴ
እንደሰራ ገባኝ።

ገና ቃል ሳልተነፍስ የባህር ዳር ልጅ እንደሆና … ስሙ ሚኪ
እንደሆነ… እዚህ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ አራት ኪሎ የተፈጥሮ
ሳይንስ ግቢ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ እንደሆነ ነግሮኝ የየት
ሰፈር ልጅ እንደሆንኩ ጠየቀኝ። የፒያሳ ልጅ እንደሆንኩ
ነገርኩት። በጣም ደስ ብሎት… የፒያሳን ዝና ሀረር እንደሰማችና
አሁን ደግሞ የበለጠ ማወቅ እንደሚፈልግ ነግሮኝ … ፍቃደኛ
ከሆንኩ ፒያሳን ባሳየው ደስ እንደሚለው በጣፈጠ አንደበቱ ጠየቀኝ ።

ሳይደገስ አይጣላም ይሏል እንዲህ ነው። ደስታው የኔ
እንደሆነ በደስታ ነገርኩት። ይሄኔ ረዳቱ በእኔ የተነሳ ይጠባበሳሉ
ብሎ የገላመጠን መሰለኝ። ገና ይሄ ይገርምሃል ብዬ በሃሳብ
ከነፍኩ።

እኔና የአምላክ ስጦታዬ ሚኪ ተጣምረን… ጎረቤቶቼ ግርማና
ሳራ 'እናንተን ነው ማየት' ሲሉልን… አብሮነታችንን ጋሽ
አንዳርጋቸው ከነሬድዮናቸው ሲመርቁት…ካሊዶ በሰርጋችን ላይ
ሲዘፍን…እንደ ተመስገን ልጄን "ተማር ልጄ …" ስለው…
ድንገት ረዳቱ "

"እህቴ መጨረሻው እኮ ነው ውረጂ እንጂ" አለኝ …ሽምጥ
ጋልቦ ይዞኝ ከሄደው ኃሳብ ደንብሬ ባነንኩ… ዞር ስል.. .....

#ይቀጥላል