Get Mystery Box with random crypto!

'በተለይ ሙስሊም ወንድም እህቶቼ ይህንን ጥያቄ ይጠይቁናል... ' 'እስኪ ኢየሱስ አምላክ ነኝ ያ | feker songs

"በተለይ ሙስሊም ወንድም እህቶቼ ይህንን ጥያቄ ይጠይቁናል... "

"እስኪ ኢየሱስ አምላክ ነኝ ያለበትን ከመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ አሳየኝ?"

ኢየሱስ ሰው እንጂ አምላክ አይደለም የአምላክ ባሪያ እንጂ ጌታ አይደለም ብለው የሚያምኑ አያሌ ሰዎችን ምድራችን አቅፋለች:: ይህ ብቻ ሳይሆን የእኛኑ የእምነት መሰረት አስተማሪያችንን መፅሃፍ ቅዱስን ጠቅሰው የሚሟገቱም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም:: እስኪ መፅሃፍ ቅዱ ስለ ኢየሱስ አምላክነት ምን ይላል? ብለን ስንመረምር ለቁጥር የሚያዳግቱ አያሌ ምንባባትን የምናገኝ ቢሆንም የተወሰኑትን ለመዘርዘር ልሞክር::

1. ኀያል አምላክ

“ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ ድንቅ መካር፣ #ኀያል_አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም ልዑል ይባላል።” ኢሳይያስ 9:6

ይህንን ቃለ እግዚአብሔር ያስተዋልን እንደሆነ ገና ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ወደዚህች ምድር ከመምጣቱ ከ700 ዓመታት በፊት የኖረው ነብዩ ኢሳያስ በትንቢት ከድንግል ስለሚወለደው አማኑኤል ሲናገር እርሱ ኀያል አምላክ ነው ይለዋል::

2. አንድ ነን

“እኔና አብ አንድ ነን።” ዮሐንስ 10:30
ይህ ቃል የነብያት ቃል ወይም የሐዋርያት ንግግር አይደለም:: ከራሱ ከኢየሱስ የተሰማ ራሱን እኔ አምላክ ብላችሁ ከምታምኑበት ከአብ ጋር እኩል ነኝ በማለት አምላክነቱን ያወጀበት ቃል ነው:: ከመፅሃፍ ቅዱስም ይሁን ከቁርአን እኔና እግዚአብሔር ወይም እኔና አላህ አንድ ነን ያለ ሰው ለማግኘት መሞከር ከንቱ ልፋት ነው ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ከሆነው ከኢየሱስ በቀር::

3. የተመሰገነ አምላክ

“አባቶችም የእነርሱ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የትውልድ ሐረጉ የሚቈጠረው ከእነርሱ ነው፤ እርሱም፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘላለም የተመሰገነ አምላክ ነው፤ አሜን።”
ሮሜ 9:5
ሐዋሪያው ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ በስፋትና በጥልቀት በማስተማር ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍትም አብዛኛውን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት በመጻፍ የሚታወቅ ሰው ነው:: ይህ ሐዋርያ ስለ ኢየሱስ አምላክነት ሲናገር እርሱ ከሁሉ በላይ እንደሆነና ለዘላለምም የተመሰገነ አምላክ ስለመሆኑ በአፅንኦት ያስተምራል:: ለዘላለም የተመሰገነ ከሰው መካከል ማን አለ??

4. እውነተኛ አምላክ

“የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።”
1 ዮሐንስ 5:20
ኢየሱስ በምድር በአገልግሎት በተመላለሰባቸው ዓመታት በቅርበት ከተከታተሉትና ረዘም ያሉ አመታትንም ካገለገሉ እድሜ ጠገብ ሐዋርያ ግንባር ቀደሙ ሐዋርያው ዮሐንስ ነው:: ይህ ሐዋርያ ኢየሱስን በአካል ያውቀዋል:: አብረው በልተዋል ሲገርፉትና ሲሰቅሉት በአይኑ ተመልክቷል:: ወንድም እህቶቹን እንዲሁም ያደገበትንም ሰፈር ያውቃል:: ታዲያ ኢየሱስ ማነው ብትሉት "እውነተኛ አምላክ ነው" የሚለው ኢየሱስን ለመግለጥ ከሚጠቀምባቸው አስተምህሮዎች አንዱ ነው:: ከሐዋርያው ዮሐንስ የተሻለ ምስክር ማግኘት አዳጋች ነው::

5. ጌታ አምላክ

““ያለውና የነበረው፣ የሚመጣውም፣ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ፣ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ” ይላል።”
ራእይ 1:8
ከዚህ ጥቅስ ውስጥ የትኛውን መርጦ ማስረዳት እንደሚቻል አላውቅም:: "ያለና የነበረው የሚመጣውም" የሚለው ቃል በራሱ ለሰው ሊሰጥ የማይችል ዘላለማዊነትን የሚገልፅ ሀሳብ የያዘ ቃል ነው::
ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሲል ደግሞ በዘላለም ውስጥ ለዘላለም የሚኖረው ኢየሱስ ጌታ መሆኑንና ደግሞ አምላክ መሆኑን አስረግጦ ያስረዳል:: ከአምላክ ውጪ መፍጠር የሚችል የለም:: ኢየሱስ ደግሞ የሁሉ መገኛ ሁሉን የፈጠረ አምላክ እንደሆነ እርሱ ከፈጠረው ውጪ የተፈጠረ እንደሌለ መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል::
“ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም።”
ዮሐንስ 1:3
እርሱ ከፈጠረው ውጪ የተፈጠረ ከሌለ እርሱ ራሱ ፍጡር ሊሆን አይችልም ማለት ነው::

# የኢየሱስን አምላክነት የሚገልጡ አያሌ የመፅሃፍ ቅዱስ ምንባባት እንዳሉ ሁሉ ቁርአንም ኢየሱስ የአላህ ቃል እንደሆነ የአላህ መንፈስ እንደሆነ ከድንግል መወለዱን ወፎችን ከጭቃ እየሰራ ህይወት ሰጥቶ ያበር እንደነበር እንዲሁም ሀጥያት እንደማያውቀውም ይናገራል::