Get Mystery Box with random crypto!

​​ .┏─━─━─━∞◆∞━─━─━─┓ .' ከራስ ሽሽት '. | የካምፓስ ህይወት_MAHIR

​​ .┏─━─━─━∞◆∞━─━─━─┓
." ከራስ ሽሽት ".
. ( ሶፊያ አህመድ ).
.╚─━━━━━━░★░━━━━━━─╝

በ @tibebislam_nw የቀረበ
ልብ አንጠልጣይ ታሪክ

ክፍል አንድ ( ⓵ )
❃•❃ ════ ❁

ሀዩ በትዝታ ማዕበል ውስጥ ሰምጣ በአሮጌው የእንጨት መስኮታቸው በኩል አሻግራ ወደውጪ ትመለከታለች። የእናቷ ነገር ትዝ ቢላት፣ የናፍቆት ጅራፍ ክፉኛ ቢወግራት ከነዛ ውብ ክብ አይኖቿ መሀል የእንባ ዘለላዎች መንጠባጠብ ጀመሩ። ትናንት ልክ እንደዛሬ ሳይሆን በፊት ጠዋት 12 ሰአት ላይ ከእናቷ ቀድማ ተነስታ ኩሽና ውስጥ ትንጎዳጎድ ነበር። ትናንት እናቷ በስራ እንዳትደክም በደንብ ታግዛት ነበር። ትናንት በዚ መስኮት አሻግራ ስትመለከት እናቷ ከኋላ መጥታ ትኮረኩራትና እየተሳሳቁ ይጫወቱ ነበር።

ግን ትናንት ነው። ነበር ተብሎ የሚወራ ከልብ እንጂ ከእይታ የጠፋ ታሪክ። የማይመለስ ትውስታ... ሀያት ገና 16 አመቷ እያለች ነበር እናቷ ወደአኼራ የሄደችው። ከ3 ታናናሽ ውንድምና እህቶቿ እንዲሁም ከአባቷ ጋር ጥላቸው ላትመለስ ካሸለበች ድፍን ሁለት አመት ተቆጠረ።

ይሀው ዛሬም የሱብሂ ሰላትን ለመስገድና በዛውም የቤት ውስጥ ስራዎችን በጊዜ ለመጀመር ስትነሳ የእናቷ ትዝታ ገረፍ አርጓት ነው ከዚ መስኮት የከተመችው። ድምፅዋ እንዳይሰማ እጇን በአፏ ይዛ ተነሰቀሰቀች!!

እናቷ ሰፈር ውስጥ በጣም ተግባቢ ፣ ሁሉም ሰው የሚወዳትና ለሰዎች በጣም አዛኝ ሴት ነበረች። በእናቷ ምክንያት ሀዩም ሰፈር ውስጥ ብዙ ሰው ያውቃታል። ታድያ እናቷን የሚያውቁ ሁላ እሷ ከሞተች ውዲ ትምህርት ቤት አለመሄዷና ቤት ውስጥ እንደሰራተኛ ሆኗ መቀመጧ ያሳሰባቸው ይመስላል። ለዚም ነው ሁሉም << አግቢ አግቢ >> እያሉ የሚጨቀጭቋት። << ሀብታም ወንድ አግብተሽ ታናናሾችሽንም ትረጃለሽ >> ይሏታል። እሷ ግን << እነሱን ጥዬ የትም አልሄድም።የኔ ህልም እናቴ የሰጠችኝን አማና ( አደራ ) መወጣት፣ ታናናሾቼን አስተምሬ ለወግ ለማዕረግ ማብቃት ነው! የኔ ቀስ ብሎ ይደርሳል።>> ብላ አሻፈረኝ ብላለች።

አባቷ አይደለም ዛሬ ሚስቱ ሞታ ድሮውንም ፀባዩ አስቸጋሪ ነበር። ግን ቢያንስ እሷ ስትኖር አደብ ይገዛ ነበር። አሁን ግን በሷ ሞት አሳቦ ቤተሰቡን ከረሳ ሰንበትበት ብሏል። አዎ ጠዋት ወጥቶ ማታ ከመመለስና አልፎ አልፎ ለአስቤዛ ብሎ ከሚሰጣቸው ጥቂት ገንዘብ ውጪ እንደድሮ ለነሱ መሳሳቱ ፣ አብሮ መጫወቱ ፣ ሁሉም ቀርቷል። የአባትነትን ፍቅር ያኔ እናታቸው ስትቀበር አብሮ ተቀብሯል።

ሀያትም ከቀን ወደ ቀን ውበቷ እየቀነሰ ፣ ሰውነቷ እየመነመነና ተስፋዋ እየተሟጠጠ መቷል። የሰዎች << አግቢ >> የሚለው ጭቅጨቃና የጓደኞቿ << ለምን ትምህርት ቤት አትመጪም? >> የሚሉ ጥያቄዎች ስለሰለቿት ከሰዎች እራቃ ከታናናሾቿ ጋር ብቻ ማሰላፍ ጀምራለች።

<< ሀዩ..ሀዩ...>> አለ የ7 አመቱና የቤቱ የመጨረሻው ልጅ አልይ... ከእንቅልፉ ቀድሞ መነሳት ልማዱ ነው። እጁንና እግሩን ለማፍታታት እየተንጠራራ ከታኛበት ፍራሽ ብድግ አለ።

ፊቷ ላይ እየተንሸራተተ ወደመሬት የሚወርደውን እንባ አይቶ እንዳይረበሽ በማለት እንባውን ከአይኗ ጠራርጋ ወደአልይ ጋር ዞረች። መሬት ላይ የተነጠፉ ሁለት ያረጁ ፍራሾች ይስተዋላሉ። በአንዱ አልይና በቅርቡ 11 አመቷን የያዘችው ታናሽ እህቷ መርየም ተኝተውበታል። በአንዱ ፍራሽ ላይ ደሞ እሷን በደንብ የምትቀርባት ፣ በእድሜም ከእሷ በ2 አመት ብቻ የምታንሰው ሌላኛዋ ትናሽ እህቷ ፈቲያ ተኝታለች።

<< አባቴ ተነሳህ እንዴ?? >> እያለች ወደ አልይ ጋር ሄደች። አጠገቡ ሄዳ እንደተቀመጠች አልይ ማልቀስ ጀመረ። ሀያት በጣም ደነገጠች። አሁን ሲጠራት እኮ ምንም አልሆነም ነበር። አልይ ሲያለቅስ የሷ ውስጥ አብሮ ያለቅሳል። ታናናሾቿ አንድ ቀንም ቢሆን እንዲከፉና እንዲያዝኑ አትፈልግም። ለዛ ነው ይሄን ሁላ መስዋትነት ከፍላ ፣ ከጓደኞቿ በታች ሆና እየኖረች ያለችው።

<< ምነው አባቴ ምን ሆንክብኝ? >> አለች ከአይኑ የሚፈሱትን የሚያሳሱ እንባዎችን በእጇ እየጠረገች።

#ክፍል_❷....ይቀጥላል....