Get Mystery Box with random crypto!

መነሻ ሃሳብ - አሌክስ አብረሃም 'አዳም ረታ በወዳጆቹ የታገተው ደራሲ' በማለት የፃፈው ፅሁፍ | የብርሃን መንገድ

መነሻ ሃሳብ - አሌክስ አብረሃም "አዳም ረታ በወዳጆቹ የታገተው ደራሲ" በማለት የፃፈው ፅሁፍ

(አልታየህ ኪዳኔ)

እንንደርደር ... የአዳም መጀመሪያ መፅሀፍ ማህሌት ነች። እንዳሁኑ ረዣዥም ልቦለዶች መፃፍ ከመጀመሩ በፊት ፅሁፍ የጀመረው በአጫጭር ታሪኮች ነው። ለብቻ ያሳተመው ማህሌት ሰማኒያዎቹ መጀመሪያ ነው የታተመችው። አዳም ለአሳታሚዎች ወስዶ ሲሰጥ አርእስቱ "ስዕል በብጥስጣሽ ጨርቆች ላይ" የሚል ነበር። በኋላ ላይ እዛ የሚሰሩት ሰዎች ናቸው ማህሌት ነው መሆን ያለበት አርእስቱ ብለው የለወጡት።

ከዛ በኋላ አዳም ሆላንድ ሄደ። አዳም ከማህሌት በኋላ በቀጥሉት አስራ ስድስት አመታት መፅሀፍ አላሳተመም። የህትመት ብርሃን አይዩ እንጂ በእነዚህ አመታት የበዙ አጫጭር ልቦለዶችን ፅፏል። አንዳንዶቹም በጋዜጣ ላይ ተነበዋል። ከግራጫ ቃጭሎች በኋላ በወጡት እቴሜቴ ፣ አለንጋና ምስር ፣ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ ፣ ህማማት እና በገና መፅሀፎች ውስጥ የተካተቱት አጫጭር ልቦለዶች የተፃፉት እንዳለ ሰባና ሰማኒያዎቹ ውስጥ ነው። አሁን መፅሀፎቹ እጄ ላይ ኑረው የእያንዳንዳቸውን አመቶች አልጥቀስ እንጂ ስራዎቹን ባነበብኩ ጊዜ ይሄንን የጊዜ Pattern እያጤንኩ ነበር። ምክንያቱም አዳም በየአጫጭር ታሪኮቹ መጨረሻና መጀመሪያ ላይ የሚያኖረው የግዜ ማስታወሻና ህዳግ አስረጂ ነው።
ቀጥሎም በ2007 ፣ 2008 እና 2010 መረቅ ፣ የስንብት ቀለማትና የመጨረሻው መፅሀፉ አፍ ላይ ደርሷል።

እስከዛሬ አዳም ረታ የመጣበትን የስነፅሁፍ መንገድ በ2 መክፈል የሚቻል ይመስለኛል።

ማህሌት ከወጣች በኋላ አዳም ግራጫ ቃጭሎችን እስኪያሳትም በነበረበት ጊዜ በርካታ አጫጭር ታሪኮችን እንደፃፈ ከላይ ጠቅሻለሁ። ሆኖም ግን በእነዚህ መፅሀፍ ባላሳተመባቸው አመታት አዳም ወደ ሌላ ስነፅሁፋዊ መንገድ እየሄደ እንደነበር ነው የሚሰማኝ።

አዳም የግራጫ ቃጭሎች መግቢያውን የፃፈው በ1983 ሆላንድ ሆኖ ነው። ይሁን እንጂ እስከማስታውሰው ድርሰቱ ስለተፃፈበት ጊዜ መፅሀፉ ላይ በውል አልተጠቀሰም። ይህንን ያነሳሁት ለምንድነው አጫጭር ታሪኮቹን ሰባና ሰማኒያዎቹ ውስጥ ይፃፍ እንጂ ግራጫ ቃጭሎችን ይዞ የመጣው አዳም ማህሌትን ከፃፈው አዳም እጅግ የተለየ ነው።

የግራጫ ቃጭሎቹ አዳም አከያየኑ ሌላ ነው ፣ ቋንቋ አጠቃቀሙ ሌላ ነው ፣ እንጀራን በሜታፎርነት የተጠቀመው አዳም ሌላ ነው ፣ አሁን ድረስ በሙክረት ላይ ያለውን ህፅናዊነት የሚለውን stylistic የፈጠረው አዳም ሌላ ነው። በአጠቃላይ አዳም በብዙ መልኩ የተለየ አዳም ሆኖ ነበር የመጣው።

ይህንን ይዘን የአዳምን ስራዎች በሁለት መመደብ የምንችል ይመስለኛል... [ ማህሌት ፣ ህማማት እና በገና ፣ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ፣ አለንጋና ምስር ] የመጀመሪያው ምድብ ውስጥ ሲገቡ ... ሁለተኛው ምድብ ውስጥ ደሞ [ግራጫ ቃጭሎች ፣ እቴሜቴ ሎሚ ሽታ ፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል ፣ መረቅ ፣ የስንብት ቀለማትና ፣ አፍ] ይገኛሉ።

እንግዲህ በምን መስፈርት ይህን ምድብ ሰራህ መባሉ አይቀርም።

አንደኛውና ዋነኛው አከያየን ነው። እዚህ አከያየን ውስጥ ደሞ ቅርፅ (form) ፣ ይዘት (content) ፣ እንጀራን ተከትሎ የመጣው የአፃፃፍ ስልት እንዲሁም ስነፅሁፉዊ ፍልስፍና (ህፅናዊነት) እና የተለያዩ ቴክኒኮችን መሰረት በማድረግ ይህን ምድብ መስራት የሚቻል ይመስለኛል።

እዚህ ጋር ሁሉም ሰው ሊገነዘበው የሚገባው ነገር የመጀመሪያ ምድብ ውስጥ ያሉት ማህሌት ፣ ህማማት እና በገና ፣ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ፣ አለንጋና ምስር ስራዎች ሁሉም የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ናቸው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ይህንን ምድብ ሳስቀምጥ ለምድብ አስቸጋሪ የሚሆኑ ስራዎቹ አሉ። ለምሳሌ እኔ የአዳም ልሂቅ ስራ ነው ብዬ የማስበው እቴሜቴ ታሪኮቹ አጫጭር ታሪኮች ሆነው እርስ በእርስ የተያያዙ መሆናቸው ለትርጉም አስቸጋሪ ያደርጋቸዋል። አጫጭር ልቦለዶች ወይስ ወጥ የሚል የትርጉም መቀናቀን ሊገጥመን ይችላል። ሆኖም የዚህ አይነት ቴክኒክ አንዱ አላማ አዳም እራሱ በአንድ ቃለመጠይቁ ላይ እንደገለፀው በአጫጭር ልቦለዶች እና በረዥም ልቦለድ መሃል የተቀመጠውን መበየኛ መስፈርት (Standard) አልያም ደሞ paradigm መቀናቀን ነው።

እንግዲህ የአዳም ስራዎች ከባድ ናቸው ወደ ሚለው እንምጣ። አንባቢ ከባድ ናቸው የሚባሉት ስራዎች ሁለተኛው ውስጥ ያሉትን ይመስለኛል። በተደጋጋሚ ሶሻል ሚዲያ ላይ ያየሁትም ይህንን ነው። [ግራጫ ቃጭሎች ፣ እቴሜቴ ሎሚ ሽታ ፣ ይወስዳል መንገድ ያመጣል ፣ መረቅ ፣ የስንብት ቀለማትና ፣ አፍ] ን ማለት ነው።

በተቃራኒው ደግሞ የመጀመሪያው ምድብ ውስጥ ያሉት . [ ማህሌት ፣ ህማማት እና በገና ፣ ከሰማይ የወረደ ፍርፍር ፣ አለንጋና ምስር ] ስራዎች ከባድ ሊሆኑ የሚችሉበት መንገድ አይታየኝም። ምክንያቱም ታሪኮቹ በአተራረክ መንገድ Linear የሆኑ ፣ በጭብጥ ረገድም በኋላ ላይ ከፃፋቸው ቀለል ያሉ ፣ የቋንቋ ትባታቸውም እንደኋለኛው ስራዎቹ ጠነን ያሉ አይደሉም።

የመጀመሪያዎቹ ምድብ ውስጥ ያሉት ስራዎች አንድ Story ለሚያነብ ሰው ምንም አይነት አባጣ ጎርባጣነት የሌላቸው ልሙጥ ታሪኮች ናቸው። ሁለተኛው ምድብ ውስጥ እንዳሉት የቅርፅ ፣ የቋንቋ እንግድነትም የሌላቸው ናቸው። ይህንን በድፍረት የምለው አዳም አይገባኝም ለሚል አንድ ወዳጄ አጫጭር ታሪኮቹን እንዲያነባቸው ሰጥቼው ያለምንም መደናገር መፅሀፉን ጨርሶ ሰጥቶኛል። ከዚህ ልምዴም በመነሳት ነው ይህንን የምለው።

እናም አሌክስ አብረሃም ያነሳው አዳምን የዚህ ሰፈር መበሻሸቂያ አድርገው ፣ አዳም የማይነካ አድርገው ሰቅለው ፣ አዳም ይከብዳችኋል እያሉ ሲንቦጣረሩ የነበሩ ወፈፍ የሚያደርጋቸው የፌስቡክ ሰዎች አንዳንድ አንባቢዎችን እንደገፉና እንዳራቁ ባምንም ከዛ ባሻገር ግን አዳም ያመጣው የአከያየን መንገድ (የቋንቋ ፣ የቅርፅ ፣ የይዘት...) እንግድነት ለአንባቢው ግርታን የፈጠረ ነው የሚመስለኝ። መክበዱም የመጣው ከዛ ጋ የተያያዘ ይመስለኛል። አከያየኑና ቴክኒኩ ሲቀየር ተያይዘው የመጡ ነገሮችም እንዳሉም እጠረጥራለሁ።

ሌላው የአይገባኝም ምክንያት ደግሞ የመቼት ጉዳይ ይመስለኛል። አንድን ልቦለድ ለመረዳት መፅሀፉ የተፃፈበት መቼት እና ስራው ከተሰራበት የዘመኑ መንፈስ ጋር ያለ ቅርበት ወሳኝ ነው። ይሄ ቅርበት በንባብ ፣ በመረጃ ፣ በይለፍ ይለፍ ወሬም ሊሆን ይችላል የሚኖረን ግንዛቤ ያንን ቴክስት ለመርዳት እጅጉን ይጠቅማል።

ለምሳሌ ጥቂትም ቢሆን የያ ትውልድ የዘመን መንፈስ መረዳቱ ለሌለው ሰው ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድን ፦ የ7 መንገዶች ወግ የሚለውን ታሪክ አልያም መረቅን እንዲያነብ ብታደርገው ስቶሪዎቹ Archetypal element ኖሮአቸው ሊነበቡ ቢችሉም አጠቃላይ ምስሉን ለማግኘት የሚቸገር ይመስለኛል። በተለይ በተለይ የአዳም አንዳንዶቹ ድርሰቶች ማጠንጠኛና መቼታቸውን የያ ትውልድ ላይ ስላደረጉ። እነዚህን ስራዎች ስናነብ የያን ትውልድ የዘመን መንፈስ ከግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ብናነባቸው ጣዕም ጨምረው ሊሰጡ ግርታም ላይኖራቸው እንደሚችል አስባለሁ።

ለንባቡ አለመሳለጥ ችግር ሊሆኑ ይችላሉ ካልኳቸው ነገሮች ተነስቼ አዳም አይገባንም ለሚሉ አንባቢዎች ሃሳብ ላቅርብ።