Get Mystery Box with random crypto!

መንታ መንገድ ክፍል ሶስት (ፉአድ ሙና) . . ዶርም እንደገባሁ አልጋዬ ላይ ተዘርሬ ሀያት አስቀም | የዳዕዋ ጎዳና

መንታ መንገድ
ክፍል ሶስት
(ፉአድ ሙና)
.
.
ዶርም እንደገባሁ አልጋዬ ላይ ተዘርሬ ሀያት አስቀምጬልሀለሁ ያለችኝን መልዕክት ለማንበብ ፌስቡክ ሚሴንጀሬን ከፈትኩ።
ሁለት መልዕክት አለኝ። አንዱ ከራሄል ነዉ። "አኩሻ የምወደዉን ልጅ እኮ ዛሬ አገኘሁት። ማታ እንገናኝና አሳይሀለሁ።" ይላል። መልስ ሳልፅፍ የሀያትን መልዕክት ከፈትኩት።
.
የሀያት መልዕክት ረዥም ነበር። ቀደም ብላ አዘጋጅታዉ አብረን የነበርን ጊዜ ኮፒ ፔስት አድርጋ እንደላከችልኝ ገባኝ።
"አክረሜ ጥቁር ሂጃብ የምትለብስ ሴት እንደምትወድ ከነገርከኝ በኋላ ከጥቁር ሂጃብ ዉጪ ለብሼ አላዉቅም። ሴት እንደማትጨብጥ ካየሁ በኋላ ወንድ ጨብጬ አላዉቅም። ሰዉነቴ ላይ የተጣበቀ ቀሚስ ለብሼ ከተቆጣኸኝ ወዲህ ቅርፄን የሚያሳይ ልብስ በፍፁም አለበስኩም። ሀይማኖትህ ላይ ያለህን ከፊል ጥንካሬ በጣም አደንቅልሀለሁ። ሁሌም እንደወንድም ስትመክረን እና ስትቆጣን በጣም ነበር ደስ የሚለኝ። ግን አኩዬ በነዚህ ሁሉ ወንድማዊ ቅርበቶችህ ምክንያት ልቤ ዉስጥ ካንተ ሌላ መድሀኒት ያጣሁለት ህመም ተፈጥሯል። ወድጄሀለሁ!!
በርግጥ ለወራት አፍኜዉ የነበረዉን ፍቅሬን ዛሬ ያለምክንያት አልነገርኩህም። ትናንት ማታ ከራሄል ጋር ለብቻችሁ እንዳመሻችሁ ሳዉቅ እንዳልቀደም በጣም ፈራሁ። የፈጣሪን ትዕዛዝ እጋፋለሁ ብለህ አትፍራ! እኔ ፈቃደኛ ከሆንክ ካንተ ጋር ዛሬ ኒካህ ለማሰር ፈቃደኛ ነኝ። አፈቅርሀለሁ!!" ይላል።
ኒካህ ማሰር ማለት በኢስላማዊ ስነ ስርዓት መጋባት ማለት ነዉ።
.
ሀያት ስለኔ እንደዚህ አይነት ምልከታ ይኖራታል ብዬ ገምቼ አላዉቅም። እኔ በፍፁም ከወንድምነት በዘለለ በሌላ እይታ ማናቸዉንም አላየሁም ነበር። ቆይ ሀዩ ምን አይነት ልጅ ነበረች? ቀይ ሁሌም ፈገግታ ከፊቷ ሳቅ ከንግግሯ መሀል የማይጠፋ ቆንጆ ልጅ ናት። ስትስቅ የሆነ ሁሉ ነገርህን የመቆጣጠር ሀይል አላት። ለምን እንደሳቀች ሳታዉቅ በሳቋ ሀይል ብቻ አብረሀት ትስቃለህ። ትንሽ ኩራት ተሰማኝ። በሀያት መፈቀር ደስ ይላል። ኤርሚያስ እና ዮናስ ወደዋት ቁም ስቅላቸዉን ሲያዩ ዞርም ብላ አላየቻቸዉም ነበር። ለካ መፈቀር በጣም ያኮራል። ያዉ በዚህ ዘመን አንበሳ መግደል ህገ ወጥ አደን ስለተባለ ፣ ጦርነትም ስለሌለ ማንንም ገድለን መኩራት አንችልምና ሴቶች አፈቀርናችሁ ሲሉን የአንበሳ መግደሉንም የመዝመቱንም አንድ ላይ ደርበን እንኮራለን።
.
ምን ልበላት? የሀያትን ጓደኝነት ማጣት አልፈልግም። ደግሞ አሁን ላይ ከማንም ጋር ኒካህ ለማሰር ዝግጁ አይደለሁም። ግራ ገባኝ። ኦ ሀዩ ምንድነዉ ያደረግሽዉ? ባትነግሪኝ ነበር የሚሻለዉ።
የፍቅር ጥያቄዋን አልቀበልም ካልኩ ጓደኝነታችን ሊጎዳ ነዉ። እሺ ካልኩ ደግሞ ሳልዘጋጅ ኒካህ ላስር ነዉ። ኒካህ ሳናስር ፎንቃ ፎንቃ እንጫወት ካልን ደሞ ዝሙት ላይ ልንወድቅ ነዉ። ሀዩ ምን አይነት አጣብቂኝ ዉስጥ ነዉ የከተተችኝ? ቢሆንም ጓደኝነታችንም ሳይጎዳ ፣የፍቅር ጥያቄዋንም ሳልቀበል ሀዩን አረጋግቼ ማቆየት ይኖርብኛል።
የሰዉን ልብ ከሰበርክ መልሶ መግጠሙ በጣም ከባድ ነዉ። አብረህ ስትሆን በመልካም እንደሆነዉ ሁሉ ስትለያይም በመልካም መሆን አለበት። አሁን የማደርጋቸዉ ነገሮች ሀያትን መካከለኛዉ የጓደኝነት ሜዳ ላይ ለማቆየት ወሳኝ ናቸዉ። ከሀያት ጋር በጓደኝነት ከተለያየን ግን ከሀጅራ እና ራሄል ጋር ያለንም ጓደኝነት ይበላሻል። ብቻዬን መቅረቴ ነዉ።
ከስልኬ ላይ አክሱም ሄደን የነበረ ጊዜ የተነሳነዉን ፎቶ አዉጥቼ ተመለከትኩት። መለያየት የለብንም አልኩ በልቤ። በነገራችን ላይ የምንማረዉ ትምህርት ከኢትዮጵያ የቱሪዝም መስህቦች ጋር የተያያዘ ስለሆነ ወደ ተለያዩ ክፍለ ሀገራት ጉዞ እናደርጋለን። የመጀመሪያ አመት ተማሪ ስለሆንን የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል በደንብ ጎብኝተናል።
.
የምሳ ሰዓት ሲደርስ ራሄል ደወለችልኝ። አነሳሁት
"ኧ ሰዉየዉ ለምሳ እየወጣን ነዉ። የት ነህ?" አለች ራሄል።
"ዶርም ነኝ በቃ መጣሁ እዘዙ!" አልኳት ከአልጋዬ ላይ እየተነሳሁ።
"ዛሬ ሀጅራም ከኛ ጋር ነዉ የምትበላዉ ምን እንዘዝ?" አለችኝ።
"አሪፍ ያላችሁትን እዘዙ!" ብዬ ስልኩን ዘግቼ ከግቢ ዉጪ ወዳለዉ ምግብ ቤት ሄድኩ።
.
ወደ ምግብ ቤቱ ስደርስ ሀያት እና ራሄል እየተከራከሩ ነዉ።
"የፔዳ በር ተገልብጦ ነዉ የተሰራዉ! ከዉስጥ ወደ ዉጪ ስትወጪ እየገባሽ እኮ ነዉ የሚመስለዉ!" ትላለች ራሄል
"ታዲያ ለምን የዘበኞቹ ቤት ከዉስጥ በኩል በሩ ላይ ተሰራ?" ትላለች ሀያት
ሀጅራ ዝም ብላ ታያቸዋለች።
እጄን ታጥቤ ስቀመጥ "አቦ አድቡ በቃ በማያከራክር አትከራከሩ!" አለች ሀጅራ።
ሀያት መምጣቴን ስታይ በሀፍረት አንገቷን አቀረቀረች። ምንም ያልተፈጠረ በማስመሰል ሀፍረቷን ዛሬ ካልገደልኩት ነገ እኔ ያለሁበት መምጣት ታፍራለች።
"ሀዩ ግን እንደ ኢንጂነሪንግ ተማሪ ስለበሩ አሰራር ስትከራከሩ አይደብራችሁም? ምን አገባችሁ?" አልኩ እየሳቅኩ። ሀያትን ከሀፍረቷ ለመገላገል ብዬ እንጂ ስለበሩ ማዉራት ፈልጌ አልነበረም።
ካቀረቀረችበት ቀና እያለች "ይሄ እኮ የትልቅ ዩኒቨርሲቲ በር ነዉ። ዛሬ ተራ በር ቢሆንም ሲቆይ ቅርስ መሆኑ አይቀርም። ስለዚህ ይመለከተናል!" አለችና ፈገግ ለማለት ሞከረች።
ራሄል እጇን ለሀያት እየዘረጋች "ቴክ ፋይቭ ካንቺ ጋር ቱሪዝም በማጥናቴ ኩራት ይሰማኛል!" ብላ እየሳቀች ምላሷን አወጣችብኝ።
.
ምግቡ ቀርቦ ከበላን በኋላ ሁሌም ምግብ እንደበላን ሻይ ለመጠጣት ወደምንሄድበት ሻይ ቤት ሄድን። ይሄ ቤት ግቢያችን በር ላይ ካሉት ሌሎች ቤቶች በጣም ይለያል። ዉስጥ ሲገባ መሬቱ ሙሉ ለሙሉ ጠጠር የለበሰ ነዉ።ጠጠሮቹን እያነሱ መጫወት ይቻላል። እንደወንበርነት የሚያገለግሉት ከቤቱ ጠርዝ ላይ ዙሪያዉን ተደርድረዉ የተለሰኑት ቦለኬቶች ናቸዉ። እንደ ጠረጴዛ ደግሞ የእንጀራ ምጣድ በሚያምር መልኩ ተሰናድቷል። ምጣዶቹ ላይ አንድ ሁለት መፅሀፍ ይቀመጣል። እንግዲህ ይሄን ቤት ለየት የሚያደርገዉ የባህላዊነት ስሜት ስላለዉ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ባልተለመደ መልኩ መፅሀፍ በመኖሩ ነዉ።
.
ወደ ሻይ ቤቱ ገብተን አራት ሻይ ካዘዝን በኋላ ሀጅራ "አቦ ራሄል እና አክረሜ ምነዉ ፈዘዛችሁ ግጥም አንብቡልን እንጂ! እኛ መች ሻዩ አማረን" አለች።
እዉነቷን ነዉ እዚህ ቤት የምንመጣዉ አብረን አሪፍ ጊዜ ለማሳለፍ በሚል ነዉ እንጂ ሻይ የመጠጣት ፍቅሩ ኖሮን አይደለም።
"ሪቾ ቀጥይ" አልኩ ለመዳመጥ እራሴን እያመቻቸሁ። ትናንት ማታ ያነበበችልኝን ግጥም አነበበችዉ። ሀያት ፊቷ ተቀያየረ። ግራ ገባኝ። ዉጥረቱን ለማርገብ በቃሌ የያዝኳትን የራሴን አንድ ግጥም ለማንበብ ስዘጋጅ ሀያት ፈገግ ብላ ትኩረቷን ሙሉ ወደኔ አደረገች። ፈገግ አልኩላትና ማነብነብ ጀመርኩ።
"ደራሽ ፍቅርሽ መሀል፣ ፈራሽ ቤት ገንብቼ፣
ሙሉ አንቺነትሽ ዉስጥ ፣ ግማሽ እኔን ይዤ፣
ሙሉ የሆንኩ መስሎኝ ፣ ሁሉ ጎደሎዬ ተሸፍኖ ባንቺ፣
አልፈልግሽም ስል አምነሽኝ ብትሄጂ፣
ፈገግታዬ የለም ፣ ሳቄን የት ወሰድሽዉ?
ኩራቴ ከሰመ ፣ ልቤን የት አኖርሽዉ?
ዛሬ ትንሽ ሳስብ ፣ ቆሜ ለብቻዬ፣
የመሳቄ ሚስጥር ፣ የኩራት ካዝናዬ ፣
አንቺ ነሽ ገብቶኛል ፣ ተመለሽ በአምላክሽ፣
ከእቅፌ አልለይሽም እንኳን ላስቀይምሽ፣
እንኳን በቃኝ ልልሽ!
ተመለሽ በፍቅርሽ! ነይልኝ ልካስሽ።" ብዬ ስጨርስ ሶስቱም አጨበጨቡልኝ።
ራሄል ፈገግ ብላ "ሌላ ጊዜ አንብብልን ለማለት እንዲመቸን ርዕሱን ንገረን!" አለችኝ።
"ርዕስ እንኳ አልነበረዉም ደስ ያላችሁን አዉጡለት" አልኩ ራሄልን እያየሁ።
ሀያት ፈጠን ብላ "ህይወት ብላችሁ አስታዉ