Get Mystery Box with random crypto!

መንታ መንገድ ክፍል ሁለት (ፉአድ ሙና) . . ከዶርም ወጥቼ በቢዝነስናኢኮኖሚክስ ላይብረሪ በኩል | የዳዕዋ ጎዳና

መንታ መንገድ
ክፍል ሁለት
(ፉአድ ሙና)
.
.
ከዶርም ወጥቼ በቢዝነስናኢኮኖሚክስ ላይብረሪ በኩል ወደ ላቭ ስትሪት አቀናሁ። ራሄል መግቢያዉ ጋር ቆማለች። የለበሰችዉ አጭር ቀሚስ ከባቶቿ አልዘለለም። ከላይ ባለኮፍያ ሸሚዝ ለብሳለች። ሸሚዙን አልቆለፈችዉም። ከዉስጥ የለበሰችዉ ቦዲ ይታያል። በርግጥ ባህርዳር ምሽቷም ብርዳማ አይደለም። ራሄል አንድ ፒንክ ደብተር ይዛለች።
አጠገቧ እንደደረስኩ "አንተ ብዙ አስቆምከኝ እኮ!" አለች እየተሟዘዘች።
የሷ ዶርም ለላቭ ስትሪት ትንሽ ስለሚቀርብ ቀደመችኝ እንጂ እንደደወለችልኝ ነበር የወጣሁት። በላቭ ስትሪት በኩል ዎክ ማድረግ እንደጀመርን "ሪቾ እንዴት ከነሀዩ ጋር አልመጣሽም? ማለቴ እንዴት ብቻሽን?" አልኳት።
በአይኖቿ ሰረቅ አድርጋ ተመለከተችኝና "በርግጥ እነሱም ነበሩ ግን ሰሞኑን የሚሰማኝ ስሜት የተለየ ስለሆነ ነዉ ካንተ ጋር መሆን የፈለግኩት!" አለችኝ።
"ደሞ ምን ተሰማሽ መችስ ያንቺ ከራስምታት አይዘልም!" አልኩ እየሳቅኩ።
"ሂ የሆንክ ሞዛዛ .. አሁን ራስ ምታት ስሜት ነዉ? ባክህ የፍቅር ግጥሞችን መፃፍ ጀምሬ ነዉ። እና ላንተ ላነብልህ ፈልጌያለሁ። ያንተንም ግጥሞች ባዳመጥ ደስ ይለኛል።" አለችኝ ፒንኩን ደብተር እየከፈተች።
ሰዓቴን አየሁት ሶስት ሰዓት ከሩብ ይላል። እኛ ግቢ ከአራት ሰዓት በኋላ ወንድናሴት አብረዉ ግቢ ዉስጥ ከተገኙ በሜትሮዎች መታወቂያ ይቀማሉ። ሜትሮ የምንላቸዉ በሌሎች ግቢዎች የካምፓስ ፖሊስ የሚባሉትን ነዉ።
"እሺ ለአራት ሩብ ጉዳይ እስኪሆን አንብቢልኝና እንለያያለን!" አልኳት።
እዉነት ለመናገር ራሄል ዛሬ በጣም አምሮባታል። የሆነ ስሜቴን እየተፈታተነችኝ እንደሆነ እየተሰማኝ ነዉ። ሴት ልጅ ምንም ብትሆን የሆነ ከፈጣሪ የተቸራት ዉበት አለ። ሪቾ ደግሞ ሲጀመርም በጣም ቆንጆ ናት። ዛሬ ደግሞ ዉበቷ ሀይሉን ጨምሮ እየተንፎለፎለ ነዉ። እስከዛሬ ግን ለምን እንዲህ አልተመለከትኳትም? አዎ ለብቻችን ተገናኝተን አናዉቅም።
አሀ አንድ ወንድና ሴት ብቻቸዉን ከተገናኙ ሶስተኛዉ ሰይጣን ነዉ የሚባለዉ እዉነት ነዉ ማለት ነዉ።
.
"አኩ ተመለስ እንጂ!" ብላ ጣቶቿን ስታጮሀቸዉ ከገባሁበት የሀሳብ ሰመመን ወጣሁ። ሪቾ ከፊቴ መንገዱን ዘግታ ቆማለች። በጣም ቀርባኛለች። ሽቶዋ መላ ሰዉነቴን ሲወረዉ ተሰማኝ። ፈገግ አለችና "ባይተዋር" ብላ ቀና ብላ አየችኝ። የግጥሙ ርዕስ መሆኑ ነዉ። እያዳመጥኳት እንደሆነ ካረጋገጠች በኋላ ግጥሙን ማንበብ ጀመረች።
"አንተ ሌት ስግደት ላይ ፣ሰማይ ስትጠራ፣
እኔ መዝሙር ጥናት ፣ ፌሎ ልጆች ጋራ
ማሸብሸብ ማወደስ ፣ ሸብረክ ከጉልበቴ
እሱን የኔ አርግልኝ፣ የዘዉትር ፀሎቴ
አንተ የለህም እዚህ
መስጊድ ሄድክ መሰለኝ ፣ አዛን ተባለ እንዴ?
ንገረዉ ለጌታህ የኔ እንዲያደርግህ ፣ ሳይገለኝ መዉደዴ።
በመዝሙር ጥናት ዉስጥ ፣በሽብሸባዉ ሁላ ፣
ልቤን ሰርቀኸዋል ያሰብኩት ሰዉ የለም እኔ ካንተ ሌላ።
ማፍቀር አንተን ብቻ ፣ ዉድድ እንደ ጣና
ፍቅሬን ተቀበለኝ ፣ በደስታ ልታጀብ ዳግም እንደገና።"
ብላ አይኔን እያየች "በፍቅር ጎዳና!" አለች።
አጨበጨብኩላት እሷም እየሳቀች ሁለት እጆቿን ከፍ አድርጋ ተሽከረከረች። ያለንበት ቦታ ጨለማ ነዉ። እብድነቷ ምሽቱን ብርሀን አልብሶታል።
ተሽከርክራ ስትጨርስ "ሪቾ ግን ፎንቃ ገባልሽ እንዴ?" አልኳት።
"ምነዉ?" አለችኝ እየሳቀች
"የሆነ ለየት ያሉ ነገሮችን እያየሁብሽ ነዉ። የፍቅር ግጥም መፃፍ መጀመርሽ፣ ቅድም ደሞ ለየት ያለ ስሜት እየተሰማኝ ነዉ ብለሽኝ ነበር ሲቀጥል ከሀጁናሀዩ ጋር ተለይተሽ የማታዉቂዉን ዛሬ እንቅልፍ እንቢ አለኝ ብለሽ ብቻሽን አገኘሽኝ። እና ምንድነዉ ይሄ አዲሱ ፀባይ?" አልኩ አይኖቿ ዉስጥ መልስ እየፈለግኩ።
ራሄል ዙሪያዬን እየተሽከረከረች "አንተ የፍቅር ግጥም ትፅፋለህ! ግን አላፈቀርክም አይደል? ሲቀጥል ባታፈቅርም ለየት ያለ ስሜት ሊሰማህ ይችላል እኮ!" አለች።
"እንቅልፍ እንቢ ማለቱስ? ከነሀዩ ተለይቶ መምጣቱስ?" አልኳት።
"አኩሻ በቃ አታጨናንቀኝ! እኔ እኮ" ስትል ስልኬ ጠራ።
.
ራሄል ዙሪያዬን መሽከርከሯን ትታ ፊትለፊቴ እየቆመች "ማነዉ?" አለችኝ።
"ሀጅራ ናት!" አልኩ ስልኬን እያየሁ
"አክረም ፕሊስ አብረን እንደሆንን አትንገራት። ሳልነግራቸዉ ስለወጣሁ ሊደብራቸዉ ይችላል።" አለች በአይኖቿ እየተለማመጠችኝ።
ስልኩን አነሳሁት "አሰላሙአለይኩም አኩሻ አፍወን ተኝተህ ነበር እንዴ?" አለችኝ ሀጅራ እንደተለመደዉ ረጋ ብላ
"ወአለይኩሙሰላም ኧረ አልተኛሁም በሰላም ነዉ በዚህ ሰዓት?" አልኳት ስለ ራሄል ከጠየቀችኝ ለመዋሸት ራሴን እያዘጋጀሁ።
"አቦ እንደዉ ባክህ ራሄል ጠፋችብን። ሳትነግረን ወጥታ ቀረች። ስልኳን ደሞ አልያዘችዉም። አይተሀት እንደሆን ብዬ ነዉ።" አለችኝ።
የሀጅራ ሚስኪንነት መዋሸት እንዳልችል አደረገኝ። "ኧረ አብረን ነን።" አልኳት።
ራሄል ደንግጣ አፏን ይዛ ደርቃ ቀረች።
"ኡፎይ በአላህ እኔ ደሞ ምን ሆነች ብዬ በቃ ቶሎ ላካት!" አለች ሀጅራ።
ስልኩን እንደዘጋሁት "ሶሪ ሪቾ አልቻልኩም። በጣም ተጨንቀዉ ነበር።" አልኳት።
"አይ በቃ ችግር የለዉም! ስንት ደቂቃ ቀረን?" አለችኝ በፈገግታዋ ውስጥ ይቅርታዋን እንድረዳ ፍልቅልቅ እያለችልኝ።
"ሩብ ጉዳይ ሊሆን አምስት ደቂቃ ይቀረዋል።" አልኳት እንደሁሌዉ ሳቋ እየተጋባብኝ።
"እሺ እየተመለስን!" አለች ፊቷን ወደመጣንበት አቅጣጫ እያዞረች።
"ባይ ዘዌይ ስለ ግጥሙ ሳስብ ነበር። አንቺ ያዉ ሀዋርያት ነሽ። የፃፍሽለት ልጅ ደግሞ ሙስሊም መሰለኝ። እንዴት ልትፅፊዉ ቻልሽ?" አልኳት።
ቆም አለች፤ስትቆም ቆምኩኝ። በጣም ተጠጋችኝ። አተነፋፈሴ ተዘበራረቀ። አይኔን ሰበርኩት።
"አንድ ሙስሊም ቆንጆ አፍቅሬያለሁ።" አለችኝና መራመዷን ቀጠለች። ተነፈስኩ ትንሽ ቆማ ቢሆን ኖሮ እሳሳትባት ነበር።
በፍፁም ከዚህ በኋላ አንድን ሴት ብቻዋን ላላገኝ ለራሴ ቃል ገባሁ። ከሴትም ራሄልን!
"ሪቾ ማነዉ ልጁ?" አልኩ ክፍላችን ዉስጥ ያሉትን ሁለት ሙስሊም ወንዶች እያሰብኩ። ሪድዋን እና ኡስማን ይባላሉ። ራሄል ከሪድዋን ጋር ስታወራ አይቻት አላዉቅም። ከኡስማን ጋር ደሞ ሁሌም እንደተጨቃጨቁ ነዉ። ስለዚህ ኡስማን ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ።
"አሁን አልነግርህም ግን በቅርቡ ማወቅህ አይቀርም!" አለችኝ።
"ካልሽ ይሁን አላስጨንቅሽም!" አልኳት።
.
እኔ ሁሌም ሰዎች አፈቀርን ሲሉ ይገርመኛል። በፍቅር እና በስሜት መካከል ያለዉ ልዩነት አይታየኝም። አንድ ሴት አንድን ወንድ አፈቀርኩ ስትል ከሱ ጋር የስጋ ጥማቴን ማርካት ፈለግኩ እያለች እንደሆነ ነዉ የሚሰማኝ። እንጂማ ሰዉ በአይን ተያይቶ እንዴት አፈቀርኩ ይላል? እዉነተኛ ፍቅርም ሆነ ጥላቻ ያለዉ ትዳር ዉስጥ ነዉ። የአንድ ሰዉ ትክክለኛ ማንነት የሚታወቀዉ አብሮ በመኖር ነዉ። አንድ ሴት ባሏን ስታፈቅር እዉነተኛ ፍቅር ነዉ ምክንያቱም አብራዉ እየኖረች ሁሉንም ጉዱን እያወቀች ነዉና የወደደችዉ። እንጂማ አንድ ወንድ በሳምንት ሶስት ቀን ከሁለትናሶስት ሰዓት ላልበዛ ጊዜ ለሚያገኛት ፍቅረኛዉ መልዐክ መስሎ መቅረብ በፍፁም አይከብደዉም። ሴቷም በተመሳሳዩ! ለዚህም ይመስለኛል በፍቅረኛነት ከሰባት አመት በላይ የቆዩ ጥንዶች በተጋቡ በወራት ዉስጥ ባሌ በፍፁም የማላዉቀዉ ሰዉ ሆነብኝ፣ ሚስቴ እንደዚህ አይነት ሴት ነበረች እንዴ? ተባብለዉ ለፍቺ የሚዳረጉት።
.
ራሄል ልንለያይ ስንል እጇን ዘረጋችልኝ። ደነገጥኩ።
"ከመቼ ጀምሮ?" አልኳት ልትጨብጠኝ እጇን መዘርጋቷ ገርሞኝ።
"ኦ ዞሮብኛል አኩዬ ይቅርታ!" አለችኝ እጇን እየሰበሰበች።
.
በነ