Get Mystery Box with random crypto!

ለጀኔራሉ ይህን መልዕክት አድርሱልኝ! የርስዎ ጎልያድነት ዛሬ ከናቁት እና ከደነፉበት ህዝብ በታች | Yalelet Wondye

ለጀኔራሉ ይህን መልዕክት አድርሱልኝ!
የርስዎ ጎልያድነት ዛሬ ከናቁት እና ከደነፉበት ህዝብ በታች ነው
******
ትላንት ምሽት በብሄራዊ ጣቢያዎች ላይ የተላለፈው የጀኔራል አበባው ሃይል የተቀላቀለበትን ቃለ መጠይቅ አይቼ እጅግ አዘንኩ፤ አፈርኩም። ከብዙ ጥያቄና መልስ በኋላ የቃለመጠይቁን መዝጊያ "እኔ ሰው ነኝ ፤ ሲቀጥል የኢትዮጵያ ጀኔራል ነኝ ። እኔ የአንድ ብሄር አገልጋይ ልሆን አልችልም" እኔ የህዝብ ልጅ ነኝ ሲሉ ቃለመጠይቃቸውን ደምድመዋል።

መደምደሚያቸውን ተቀብለን እንደ ሰውም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ጀኔራል ሰውኛ የሆኑ የሞራል ጥያቄዎችን ልናነሳላቸው ተገደናል።

እንዴው ለመሆኑ እርስዎ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ዘብ የቆሙለት ውሽልሽሉ መንግስት ጥገናዊ ለውጥ አደረኩ ባለበት ማግስት በቤኒሻንጉል እና በወለጋ ለተከታታይ 5 አመታት የአማራ ህዝብ ታርዶ በጅምላ ሲቀበርና ሲፈናቀል እርስዎ የሚመሩት ተቋም ምን እየሰራ ነበር?

በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ የሚኖረው የአማራ ህዝብ በብሄሩ ተለይቶ ለዘመናት ያካበተው ሃብት በአንድ ጀንበር ሲወድምበትና ሲፈናቀል በርስዎ የሚመራው የማህበራዊ ፍትህ አስጠባቂ የበላይ ተቋም ምን ሰራ?

እርስዎስ ቢሆኑ እንደ አንድ ትልቅ ተቋም መሪ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የህዝብ ልጅ በሚዲያ ወጥተው ስለምን ድርጊቱን አላወገዙም? ነው ወይስ በርስዎ ስሌት የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይደለም ማለት ነው?

ሌላው ይቅር ለሃገርና ለህዝብ ደህንነት ስጋት የሆነው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሃይሎች ከመከላከያ ሰራዊቱ በላይ ዘመናዊ መሳሪያዎችንና ወታደራዊ ኮንቮዮችን ታጥቆ ሳለ እርሶም ሆኑ ተቋምዎ አንድም ቀን ጉዳዩን ሊያስተባብል አልቻል። ለምን?

ዛሬ የአገር ህልውና አስጠባቂው፣ የመከላከያ ሰራዊቱ መከታና ደጀን የሆነው የአማራ ልዩ ሃይል እና ፋኖ በታጠቀው ክላሽ ስለምን አይንዎ ቀላ? ለምንስ በዚህ ልክ ሚዲያ ላይ ወጥተው በዕብሪት ሊደነፉ ቻሉ? ከህወሃት ጋር በነበረው ጦርነት እንኳ ይሄን ያህል አልደነፉም ነበር እኮ ክቡር ጄኔራል? ለማንኛውም ሃይል በተሞላበት ቃለ መጠይቅዎ ውስጥ አድር ባይነትዎ ጎልቶ ታይቷል።

እንደው ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ጀኔራልነትዎ እርስዎ የወጡበትን ህዝብ እንዲጠየፉ ያደረገዎት መንፈስ ምን ይሆን?

በአንድ ወቅት የእርስዎ አለቃ ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ በስረአቱ ውስጥ ስለሚታየው የተረኝነት ድርጊት ተጠይቀው በድፍረትና በልበ ሙሉነት "አዎ ተራው የኛ ነው፤ ተረኞች ነን" ብለው እንደነበር ክቡር ጀኔራል አበባው ሊረሱት አይችሉም ብለን እናምናለን።

ሲጠቃለል:- ክቡር ጄኔራል ሆይ የሞራል ሚዛንዎን ስተዋል። ምናልባት የእርስዎን አላውቅም እንጂ በርስዎ የሚመራው ሰራዊት ከህዝብ ነው የወጣው። ዛሬ እርስዎ የተማመኑበት ሃይል ሁሉ ከህዝብ በታች ነው።

አዎ የርስዎ ጎልያድነትም ዛሬ ከናቁት እና ከደነፉበት ህዝብ በታች ነው