Get Mystery Box with random crypto!

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነሐሴ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን የከ | ውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት



አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነሐሴ ሃያ ስድስት በዚህች ቀን የከበረ አባ ሞይስስና እኅቱ ሣራ በሰማዕትነት አረፉ።



የእሊህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው ደጎች እጅግም ባለጸጎች ናቸው። የከበረ ሞይስስ ነሓሲ ወላጆቹ ከአረፉ በኋላ እኅቱ ሣራን ሊያጋባትና ወላጆቹ የተዉትን ገንዘብም ሊሰጣት እርሱም ወደ ግዳም ሒዶ ሊመነኩስ አሰበ። ይህን አሳቡንም በነገራት ጊዜ እንዲህ ብላ መለሰችለት እኔን ልታጋባኝ ከወደድክ አስቀድሞ አንተ አግባ እርሱም እንዲህ አላት እኔ ብዙ ኃጢአት ሠርቻለሁ ስለዚህ ኃጢአቴን ለመደምሰስ እመነኵስ ዘንድ እሻለሁ ማግባት አይቻለኝም የነፍሴን መዳኛ አስባለሁ እንጂ። ሁለተኛም እንዲህ ብላ መለሰችለት አንተ ነፍስህን ስታድን እኔን በዓለም ወጥመድ ውስጥ እንዴት ትጥለኛለህ። እርሱም እንዲህ አላት ምንኵስና ከፈለግሽ ስለ ራስሽ የምታውቂ አንቺ ነሽ እኔም የወደድሽውን አደርግልሻለሁ። እንዲህም አለችው ለነፍስህ የምታደርገውን ለኔም እንዲሁ አድርግ እኛ ሁለችን ከአንድ ባሕርይ፣ ከአንድ አባት ከአንዲት እናት የተገኘን ነንና፤ የልቧንም ቆራጥነት አይቶ ወዲያውኑ ከእርሷ ጋራ ተነሣ ገንዘባቸውንም ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተኑ። ከዚህም በኋላ እኅቱ ሣራን ወሰዳት ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ወዳለ የደናግል ገዳም ውስጥ አስገባት እርሱም ከወንዶች ገዳም ገብቶ በዚያ ተጋድሎን ተጋደለ። እንዲሁ እኅቱም ጽኑዕ በሆነ ገድል ተጠምዳ እየተጋደለች ሁለቱም ሳይገናኙ ዐሥር ዓመት ኖሩ። በሊቀ ጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ የሹመት ዘመን ሳዊርያኖስ የሚባል ከሀዲ ተነሥቶ የክርስቲያንን ወገኖች ማሠቃየት ጀመረ። ከመነኰሳት ገዳማውያም ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ። አባ ሞይስስም ተነሣ ሊሰናበታትም ወደ እኅቱ ሣራ ላከ በሰማዕትነት መሞት እንደሚሻም ነገራት። እኅቱም በሰማች ጊዜ ወዲያውኑ ተነሣች፣ ሄዳ፣ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ እንድታሰናብታት እመ ምኔቷን ለመነቻት እመምኔቷም ጸለየችላት ሰላምታም ሰጥታ አሰናበተቻት እርሷም ደናግሉን ሁሉ ተሰናበተቻቸው። ከዚህም በኋላ ወደ ወንድሟ ሄደች በጐዳናም አገኘችውና እርስ በርሳቸው ሰላም ተባባሉ ወደ እስክንድርያ ከተማም ገብተው በመኰንኑ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ከዚህም በኋላ ራሳቸውን በሰይፍ አስቆረጠ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።



በዚህችም ቀን የከበሩ መነኰሳት አጋቦስና ቴክላ በሰማዕትነት አረፉ።



እሊህም ቅዱሳን በከሀዲው ዮልያኖስ ዘመን መከራ በመቀበል ተጋደሉ። ከመኳንቶቹም አንዱ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው። ሥቃያቸውም ባሰለቸው ጊዜ ለአንበሶች ጣላቸውና ገድላቸውን ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።



በዚችም ቀን ለአብርሃም ሚስት ለተመሰገነች ሣራ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶች አዘዙ።



ይህቺንም ክብርተ ማሕፀን የሆነች ጡቶቿም የተባረኩ ክብርት ሣራን የጌራራ ንጉሥ አቤሜሌክ ባል እንዳላት ሳያውቅ በወሰዳት ጊዜ እንዳይቀርባት እግ ዚአብሔር ገሠጸው በደዌም ቀሠፈው ባሏ አብርሃምም በጸለየለት ጊዜ ከደዌው ተፈወሰ ከዚህም በኋላ ከብዙ ገንዘብ ጋራ ወደ ባሏ መለሳት። ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር በሦስትነቱ ተገልጦ ወደ ቤቱ እንግድነት በመጣ ጊዜ ለአብርሃምም የይስሐቅን መወለድ በነገረው ጊዜ ሣራም በድንኳኑ ውስጥ ሳቀች እንዲህ ስትል እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል። እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው ሣራን ለብቻዋ ምን አሳቃት እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል እኔም አሁን አርጅቻለሁ ብላ በውኑ ለእግ ዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን ከዚህም በኋላ ፀንሳ እግዚአብሔር ባለው ወራት በርጅናዋ ለአብርሃም ወንድ ልጅን ወለደች። ይስሐቅም በአደገ ጊዜ ልጅዋ ይስሐቅን ከእስማኤል ጋራ ሲጫወት አየችው። አብርሃምንም ሣራ እንዲህ አለችው ያቺን ባሪያ ከነልጅዋ አባራት የባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋራ አይወርስምና። ይህም ነገር ለአብርሃም ስለ ልጁ እስማኤል፣እጅግ ጭንቅ ሆነበት። እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው የዚህ ልጅ የዚችም ባሪያ ነገር በፊትህ ጭንቅ አይሁንብህ የምትልህን ሁሉ ሣራን ስማት ከይስሐቅ ዘር ይተካልሃልና። ይህም ነገር ታላቅ ምሥጢር አለው የተመሰገነ ጳውሎስ ቅድስት ሣራን የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ አድርጓታልና። ከዚህም በኋላ በበጎ እርጅና በአረፈች ጊዜ ከኬጢያዊ ኤሞር ልጆች በገዛው ቦታ ቀበራት።

ለእግዚአብሔርም ፤ ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረች እናታችን ሣራ በጸሎቷ ይማረን ፣ በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

አሜን።

"ጽዮንን የሚወዳት አይደክምም"
ቅዱስ ያሬድ