Get Mystery Box with random crypto!

† ምን ብዬ ልጥራችሁ? † በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ … ከሌሎ | ውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት

† ምን ብዬ ልጥራችሁ? †
በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

… ከሌሎች ከማያምኑት ብልጫ ኖሯችሁ እንዳየው በምፈልገው ሕይወት፥ በኹሉም ረገድ ተቃራኒ ኾናችሁ አያችኋለሁ፡፡

ለምሳሌ

ከቦታ አንጻር፥ ቀኑን ኹሉ የፈረስ እሽቅድምድምንና ተውኔትን፣ ነውርን የተሞሉ ትርኢቶችንና የክፉዎችን ማኅበር፣ ርኵሰትንም የተሞሉ ሰዎችን ስትመለከቱ እንደምትውሉ አያችኋለሁ፡፡

ከፊታችሁ አንጻር፥ ዘወትር ያለ ልክና እንደ አመንዝራ ሴት ስትስቁ እመለከታችኋለሁ፡፡

ከአለባበሳችሁ አንጻር፥ ከተዋንያንና ጠቢባን ነን ከሚሉ ሰዎች ምንም እንደማትለዩ አስተውላችኋለሁ፡፡

ከሚከተሏችሁ ሰዎች አንጻር፥ ብዙ ውዳሴ ከንቱን እንደምትሹ አያችኋለሁ፡፡

ከንግግራችሁ አንጻር፥ ምንም ደኅና ነገር፣ በቁዔት ያለው ቃል፣ ለሕይወታችን የሚረባ ንግግር እንደሌለባችሁ እገነዘባለሁ፡፡

ከማዕዳችሁ አንጻርም ከዚያ ጽኑዕ የኾነ ወቀሳ የሚያመጣባችሁ እንደ ኾነ አያለሁ፡፡

ታዲያ እስኪ ንገሩኝ! ክርስቲያንን ክርስቲያን ከሚያስብሉት ነገሮች እጅግ የራቃችሁ ኾናችሁ እያለ፥ ክርስቲያኖች መኾናችሁን መለየት የምችለው በምንድን ነው? ክርስቲያኖች መባላችሁስ ይቅርና፥ ሰዎች ብዬ ልጠራችሁ የምችለው እንዴት ነው?

ምክንያቱም እንደ አህያ ትራገጣላችሁ፡፡
እንደ ኮርማ ትሴስናላችሁ፡፡
እንደ ፈረስ ከሴቶች ኋላ ኾናችሁ ታሽካካላችሁ፡፡
እንደ ድብ ሆዳሞች ናችሁ፡፡
ሥጋችሁን እንደ በቅሎ ሥጋ ትሰገስጋላችሁ፡፡
እንደ ግመልም ቂም ትይዛላችሁ፡፡
እንደ ተኵላ ትነጥቃላችሁ፡፡
እንደ እባብ ትቈጣላችሁ፡፡
እንደ ጊንጥ ትናደፋላችሁ፡፡
እንደ ቀበሮ ተንኰለኞች ናችሁ፡፡
እንደ እባብ ወይም እንደ እፉኝት በጕረሮአችሁ መርዝ አለ፡፡
እንደ ክፉ ጋኔን ከወንድማችሁ ጋር ትጣላላችሁ፡፡



ታዲያ ክርስቲያኖች የሚለውስ ይቅርና፥ በምናችሁ ሰዎች ብዬ ልጥራችሁ?

ሰው የሚያስብል ምልክት ሳይኖራችሁ እንዴት ብዬ ከሰው ዘንድ ልቊጠራችሁ?

የንዑሰ ክርስቲያኖችና የክርስቲያኖች ልዩነት ባሰብኩ ጊዜ ልዩነቱ የሰውና የበረኻ አውሬ ያህል ይኾንብኛል፡፡

ታዲያ ምን ብዬ ልጥራችሁ? የበረኻ አውሬ ብዬ ልጥራችሁን? እንዲህስ አልላችሁም፤ የበረኻ አውሬዎች እንደዚያ የኾኑት ከተፈጥሮአቸው የተነሣ እንጂ እንደ እናንተ ወደውና ፈቅደው አይደለምና፡፡

ታዲያ ምን ብዬ ልጥራችሁ? አጋንንት ልበላችሁን? እንዲህስ አልላችሁም፤ አጋንንት የሆድ ባሪያዎች አይደሉምና፤ ፍቅረ ንዋይም የለባቸውምና፡፡

ታዲያ ከበረኻ አውሬዎችም ከአጋንንትም የሚብስ ክፉ ግብር ከያዛችሁ፥ ንገሩኝ - ሰዎች ብዬ እጠራችሁ ዘንድ ይገባኛልን?

ሰዎች ለመባል እንኳን የሚበቃ ምግባር ከሌላችሁስ፥ ክርስቲያኖች ብዬ ልጠራችሁ የምችለው እንዴት ነው?

አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ እኛን ልጆችህን ሰዎች ታደርገን ዘንድ እንማጸንሃለን።

አሜን።

"ጽዮንን የሚወዳት አይደክምም"
ቅዱስ ያሬድ